የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምክር ለሰሚው/12

ወዳጄ ሆይ !

ክርስቲያኖች በኅብረት እግዚአብሔርን የሚያመልኩት ለመንፈሳቸው እርካታ ብቻ ሳይሆን በግላቸው ላለው የስብከተ ወንጌል ዘመቻ ኃይል ለማግኘትም ነው ። ማስተማር የመምህራን ድርሻ ሲሆን መመስከር ግን የክርስቲያን ሁሉ ተግባር መሆኑን እወቅ ። በዚህ ዓለም ላይ የሚመስሉህን ብቻ አትውደድ ፣ የሚቃወሙህንም በቅንነት ተመልከት ። የሰው ልጅ በፋብሪካ እንደ ተሠራ ዕቃ አንድ ዓይነት ሳይሆን እግዚአብሔርን በማምለክ አንድነት ያለው ፍጡር ነው ። የተለያየን መሆናችን ሕይወትን ምሥጢር አድርጓታል ። እግዚአብሔርን ስትጠብቅ ቀኔ መሸ ፣ ዘመኔ አለቀ ብለህ አትስጋ ። እግዚአብሔር ብርሃን ነውና ምሽት ፣ ሕይወት ነውና ሞት አያሰጋውም ። ልትሄድበት የሚገባው ነገር ብትጠብቀው አይመጣም ። እግዚአብሔር “ጠብቅ” በማለት ትዕግሥትን ፣ “ሂድ” በማለት ተልእኮን ይሰጣል ።

ወዳጄ ሆይ !

በዕድሜህ መጨረሻ ላይ ልታደርገው የምትሻውን ዛሬ አድርገው ። በዕድሜ መጨረሻ እንደ ሄኖክ ሁሉን ትተህ መኖር የምትፈልግ ከሆነ ዛሬ እንደ ኤልያስ ነቢይ የምናኔን ሕይወት መኖር ትችላለህ ። የሰው መጨረሻ ሰባና ሰማንያ ዓመት ሳይሆን ዛሬ ማታ ሊሆን ይችላል ። ዛሬ የጨበጥኸው ትላንት ሕልምህ ነበረ ፤ የዛሬ ሕልምህ ነገ እውን ይሆናል ። የልጅነት ወዳጆችህን ስታጣ የሽምግልና ዘመዶች ይሰጥሃልና በማያልቅበት እግዚአብሔር ደስ ይበልህ ። የተከፈቱ በሮች ከተዘጉ በማንኳኳት አይከፈቱምና ዕድሎችህን አክብር ። በየቀኑ የሚገጥሙህ መልካም ነገሮች ለትልቅ ኃላፊነት እንድትሾም የመጡ ፈተናዎች ሊሆኑ ይችላሉና አክብረህ ያዛቸው ። ነገር ካለፈ በኋላ መንቃት ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ መሰማራት ነው ።

ወዳጄ ሆይ !

እግዚአብሔርን በዓይኖችህ ባታየውም እርሱ ግን ያይሃልና ጸሎትህ ለማስፈቀድ እንጂ ለማስረዳት አይሁን ። ሰፊውንና የጠራውን ሰዓትህን የምታሳልፈው ከሥራ ጓዶችህ ጋር ነውና የሥራ ቦታህን ንጹሕና ሰላማዊ አድርግ ። ዓይን ያለ ብርሃን ፣ አእምሮ ያለ እውቀት ሊያዩ አይችሉም ። እውቀት ለቅን ፍርድ ያስፈልጋልና ከእውቀት አትስነፍ ። ለመኖር ምግብ አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ ዕድሜንም የሚያሳጥር ምግብ ነውና አመጋገብህን ሥርዓት አስይዘው ። ካላስተዋልህ መጠንቀቅ ፣ ካልተጠነቀቅህ ማስተዋል አትችልምና ማስተዋልና ጥንቃቄን ይኑርህ ። የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንደ ዐውዱ ውጊያው መንፈሳዊ ነውና በጸሎት ያዘው ። እጅግ የከፉ ሰዎችን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብታገኝ ሌላ የሚቀበላቸው ባለመኖሩ እዚህ እንደ ተገኙ አስተውል ።

ወዳጄ ሆይ !

የማኅበራዊ መገናኛዎች አሳብህን እያስጣሉ አሳብ የሚጭኑብህ ፣ የራስህን ኑሮ ስለ ሰው በማውራት የሚያስረሱህ ፣ በማይመለከትህ ነገር አእምሮህን የሚያውኩ ናቸውና በጥንቃቄ ልትይዛቸው ይገባሃል ። አድማስ የሌለውን እግዚአብሔር እያመለክህ ዘረኛ አትሁን ። የሚችለውን ጌታ ይዘህ ቀኑ አያስፈራህ ። መልካም አጋጣሚዎች የምትጠብቃቸው ብቻ ሳይሆኑ የምትፈጥራቸውም እንደሆኑ አትዘንጋ ። እውነተኛ መነቃቃት ንስሐ መግባትና በምሕረተ ሥላሴ መደሰት ነው ። የምታምነውን ለመግለጥ የማያምኑትን ማውገዝ አያስፈልግህም ። እንደ ወረርሽኝ እየተዛመተ ካለው የሐሰት ፈውስና ትንቢት ራስህን ጠብቅ ። ሙት ሳቢ ፣ ሞራ ገላጭ ፣ ጠንቋይ የተከለከለው ስለማያውቁ ወይም ሙሉ በሙሉ ሐሰት ስለሚናገሩ አይደለም ፣ የማይረባህን እውቀት ከማይረባ አምልኮ አትፈልግ ተብሎ ነው ።

ወዳጄ ሆይ !

የተሰጠውን የፈጸመ ትጉ ፣ የተሰጠውን ፈጽሞ ያልተሠሩትን የሚሠራ የእግዚአብሔር ሰው ይባላል ። ያልተገራ ፍላጎት ካላቸው ሰዎች ጋር ወዳጅ ስትሆን ሕይወትህ እንደ ተበጠበጠ ይኖራል ። በድህነት ያደገ እንደገና ላለማጣት ገዳይና አጥፊ ሊሆን ይችላልና ድህነትን ከድህነት አእምሮ ጋር ጣለው ። የዘላለሙን ኢየሱስ ሰበር ዜና አድርገው ከሚያወሩት ይልቅ እርሱን ለብሰውት በፍቅርና በርኅራኄ የኖሩትን አባቶች አስብ ። ክርስቶስ የሚሰብኩት ብቻ ሳይሆን የሚኖሩትም ነው ። ለራሳቸው ሳይረዱት እናስተምራለን ከሚሉ ሞኞች ራቅ ። የደንቆሮ መምህር መድረሻው ገደል ነው ። ውሸት የሚጮኸው ስለማይተማመን ነው ። እውነት ዝም የሚለው የጸና ስለሆነ ነው ። ውጤቶችህና ስኬቶችህ የመነሻህን ትክክለኛነት ላይገልጡ ይችላሉ ። በትክክል ተነሥተው ስኬት ያላገኙ ብዙ ጻድቃን ሊኖሩ ይችላሉ ። ሰይጣን ወድቀው ለሚሰግዱለት ብርና ወርቅ ፣ የዓለምን ክብር የመደበ ነውና በማግኘትህ ያጡትን አትናቅ ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ