ወዳጄ ሆይ !
በውስጥህ ያለውን ሁሉ ለሰዎች ለማስረዳት አትጨነቅ ። በውስጥህ ያለውን ሁሉ አንተ ራስህም አልተረዳኸውም ። እንደሌለህ እያወቅህ በምኞት ትቸራለህ ። አቅምህን መረዳት አቅቶህ በይሉኝታ ትማቅቃለህ ። የልብን የሚረዳ የልብ አምላክ ብቻ ነው ። ሰዎች እንዲያገኙ ተመኝ ፣ ካላቸው ያንተን አያዩም ። የሚመስል ነገር እስከ ጊዜው ፣ የሆነ ነገር ግን ለዘለቄታው ነውና የሚመስል ነገርን ከሆነ ነገር ለይ ። ግልጽነትህ በሚያስንቅህ ስፍራ በርህን ገርበብ አድርግ ፣ በእግዚአብሔርና በመንፈሳዊ አባቶች ዘንድ ግልጽነትህ ያስከብርሃል ። መጨረሻ የሌለው ግንኙነት ጸጸቱ ለዕድሜ ልክ እንዳይሆን አልመህ ግንኙነትን ጀምር ። ሲሄድ ያየኸው ዕድልህ አንድ ቀን ይመጣል ። የሄደው የሚመጣውን እንዳይጋርድብህ ንቁ ሁን ።
ወዳጄ ሆይ !
ቋሚ ሥራ እግዚአብሔርን ማምለክ ፣ ቋሚ ወዳጅም መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነውና ሸምበቆ ተደግፈህ እንዳትወድቅ ተጠንቀቅ ። የጥንት ትዳር ከዛሬው ይሻል ነበር ብለህ የያዝኸውን አታቃልለው ። ትዳር መካሰስ የጀመረው በአዳምና በሔዋን ፣ ስርቆሽ የጀመረው በአብርሃምና በሣራ ፣ ልጆችን ተከፋፍሎ እርስ በርስ ማባላት የተጀመረው በይስሐቅና በርብቃ ነው ።
ወዳጄ ሆይ !
ዛሬ በሙሉ ልብህ ሩጥ ፣ መጨረሻ እንዳለህ ግን አስብ ። ትላንት የራቀህን ዛሬ ደርሰህበታል ፣ በእጅህ ያለውም ከእጅህ ሊያመልጥ ይንፈራገጣል ። መንፈሳዊ ስጦታህን በጸሎት እንጂ በጉልበት እጠብቃለሁ ብለህ አትነሣ ። አገልጋይ የሚል መጠሪያ ይዘህ እንደ ጌታ አትኑር ። ንጹሕነትህን ለመናገር ጊዜ አትፍጅ ፤ የሚያጸድቅና የሚኰንን እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ከምታስተምራቸው ተማሪዎች ተማር ። ለምታዛቸውም ታዘዝ ። ይህ ዘመን እያልህ አትማረር ፣ የባሰ እንጂ የጀመረ ክፋት የለምና ። ብዙዎች ካንተ ጋር ከሚኖሩ አንዱ አምላክ ካንተ ጋር ቢኖር ይሻላል ። ደጋፊዎች ሞትን አያግዱልህም ። ተቀምጠህ በጭንቀት አትቁም ፣ ተኝተህ በአሳብ አትሩጥ ። እግዚአበሔር ካልሞላው የሰው አሳብ ከንቱ ነው ።
ወዳጄ ሆይ !
ከሚያሞግሱህ አዋቂዎች የምሁራን ዱላ ይሻልሃል ። በአንተ መምጣት ብዙዎች ሲንጫጩ ደስ አይበልህ ። አንበሳም ቢመጣ ብዙዎች ይጮኻሉ ። ወርቃማው ቀንህ በጽሞና የሆንህበት ፣ የማምለጫው መንገድህ የተረሳህበት መሆኑን አትዘንጋ ። ሰዎች ማመስገን ሲፈልጉ አንተ ብቻ ያለህ ከመሰላቸው መልአክ ያደርጉሃል ፣ የመሳደብ አምሮታቸው ሲመጣ አንተ ብቻ አለህና ሰይጣን አድርገው ያረክሱሃል ። አንተ ያልሠራኸውን መልክህንና ቁመናህን እንዲያደንቁት ፎቶህን አትናኝ ፣ ይህ ጣኦት አምልኮ ነው ። በጸጋ የተሰጠህን ነገር በጥረት እንዳገኘህ እንዳይቆጥሩት አገልግለህ ዞር በል ።
ወዳጄ ሆይ !
የአደባባይ አገልግሎት ያለው የግል ሕይወትም እንዳለው አትዘንጋ ። መድረክ ላይ ቢያገለግል መድረክ ላይ አይኖርምና የሚበላው ምግብ ፣ የሚያግዘው ወዳጅ እንደሚያስፈልገው አትርሳ ። ዘመኑ ከቅዱስ ጳውሎስ ይልቅ ያንተ ዘመን ነውና በዘመንህ ጳውሎስን ለመሆን ጣር ። ሰይጣን ጌታን ሲፈትነው ተአምር ጠይቆታል ። መደበኛውን ኑሮ ትተህ ተአምር የምትፈልግ ከሆነ በሰይጣን እየተፈተንህ ሊሆን ይችላል ። ድንጋይ ዳቦ አንዲሆን ብትመኝ ተፈጥሮ ይባክናል ። ዘሪ ገበሬ ፣ የሚዘራባት ምድር ፣ ክረምትና በጋ አላስፈላጊ ይሆናሉ ። ምንም ብትዋረድ ፣ ጠባይህ ቢረክስ ያሳደገህን አታሳንስ ፣ ያስተማረህን አትክሰስ ፣ የገነባኸውን አታፍርስ ፣ ለወዳጅህ ሞትን አትደግስ ፣ ያጎረሰህን አትንከስ ፣ ሁለት ሁናችሁ ያደረጋችሁትን በአደባባይ አትነስንስ ። የጋሪ ፈረስ አይደለህምና ግራና ቀኝህን ደግሞም የኋላህን ተመልከት ።
በምክሩ ግሩም ለሆነው እግዚአብሔር ምስጋና እናቀርባለን ! ለዘላለሙ አሜን ።