የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምክር ለሰሚው/14

ወዳጄ ሆይ !

ሥራ ከደመወዝ ባሻገር ደመወዝ አለው ። በማለዳ የሚያነቃህ ፣ ንጹሕና ውብ እንድትሆን የሚያተጋህ ፣ የክት ልብስህን የሚያስለብስህ ፣ ቁርስህን በሰዓቱ የሚያስቀምስህ ፣ ከቤትህ እንድትወጣ የሚያደርግህ ፣ ከሰዎች ጋር የሚቀላቅልህ ፣ ማኅበራዊ ኑሮ የሚሰጥህ ፣ የገሀዱን ዓለም እውነት የሚያሳውቅህ ፣ ብዙዎችን እንድትረዳና እንድታስደስት ዕድል የሚሰጥህ ፣ ታዛዥነትን የሚያስተምርህ ፣ እውቀት የሚጨምርልህ ፣ በተስፋ የሚያኖርህ ፣ ስለ ጡረታ የሚያሳስብህ ፣ ደመወዝ አለኝ ብለህ እንድትበደር የሚያደርግህ ፣ ሰዎችም አምነውህ የሚያበድሩህ ፣ ይሠራል ተብለህ የሚያስከብርህ ፤ አእምሮህን በእውቀት ፣ ጉልበትን በኃይል የሚሞላልህ ፣ የጤንነትህና የጉብዝናህ ምስክር ፣ ለማግባት ሽማግሌ ስትልክ “ምንድነው ሥራው?” ስትባል ዋስ የሚሆንልህ ፣ ሥራህ ነው ።

ሌተቀን በቤትህ ብትኖር ትሰለቻለህ ፣ ከትዳር ጓድህ ጋር ታጋጫለህ ፣ የልጆችህን ልግመኛነት መቀበል ይከብድሃል ። ሰውነትህ እንቅስቃሴ ስለማያደርግ ይተሳሰራል ፣ ለበሽታ ትጋለጣለህ ። ሥራህ ያልተነገረለት ደመወዝ አለው ። ሥራህን በማይለካ ጸጋው እንጂ በሚቆጠረው ብር አትለካው ። እሰይ ሰኞ መጣ በል ። ቤተሰብህም የሚያከብርህ ስትሠራ ነውና ። እግዚአብሔርም የሚባርከው የእጅህን ሥራ ነው ። ሥራ የኋላ እርግማን ሳይሆን የተፈጠርህበት ምክንያት ነው ። ሥራን ስትጠላ መብልን አብረህ ጥላ ።

አባቶች ሁሉ እንደ ተናገሩት ክፉ አሳብ በሥራና በጸሎት ይርቃል ። ሥራ ብታጣ እግዚአብሔር የገዛ አካልህን ሥራ አድርጎ ሰጥቶሃል ። “እኔ ለእኔ ሥራ ነኝ” በል ። ፀጉር ማበጠር ፣ ፊትን መታጠብ ፣ ጥርስን መፋቅ .. የገዛ ገላህ ሥራ ሁኖ ተሰጥቶሃል ። ሥራ ብታጣ ንጹሕ ልብስህን እንደገና እጠበው ። አካባቢህን ተንከባከብ ፣ አበቦችን ውኃ አጠጣ ። ሥራ ጭንቀትን ያቀላል ፣ የአእምሮ መወጠርን ያፍታታል ። አዲስነትን ያጎናጽፋል ። የምታዝዛቸው ሠራተኞች ሲበረቱ ያንተ ጉልበት ግን መላሸቁን ተመልክተህ ሥራ መሥራትን ውደድ ። ሠራተኞችህ ጤነኞች አንተ ግን በብዙ የኪኒን ጉቦ እንደምትኖር እያሰብህ አኗኗርህን አስተካክል ። ጌትነት መሥራት እንጂ በቁም መሞትና የሰው ሸክም መሆን አይደለም ። እግዚአብሔርን ለምነህ ያገኘኸውን ሥራ ሰውን ማስለቀሻ አታድርግ ፣ ቅጣቱን አትችለውም ። ዘመናዊነት ጌትነት ሳይሆን አገልጋይነት ነው ። ነገሥታት መንገድ ሲያጸዱ በሚታይበት ዘመን ሥራ ክቡር መሆኑን ተረዳ ። ሳትሠራ የሚከፍሉህ ሞትህን እያፋጠኑ ነውና በግድ መሥራትን ጠይቅ ። ሥራ አለኝ ብሎ ከቤት መውጣት ጸጋ መሆኑን ተረዳ ።

ወዳጄ ሆይ !

የምሠራው የማይሠሩ ወንድሜንና እኅቴን ለመርዳት ፣ ለእነርሱ የተሻለ አገር ለመፍጠር ነው ብለህ አስብ ። ጎበዝ ሁኖ ሥራ ያጣ ፣ ሰነፍ ሁኖ በሥራ የሚቀልድ ፣ ወሬ እያቀባበለ ፣ የአለቃውን ያልቆሸሸ ቀሚስ እያራገፈ የሚኖር አድር ባይ አለ ። አገራችን የሚሠራውን ንቃ ፣ የሚያወራውን የምታከብር ፣ የሙያ ሳትሆን የቡድን አገር ከሆነች ሰንብታለች ። ባዶ ወረቀትና አድር ባይ አንድ ነው ። ሁለቱም መልእክት የለሽ ናቸው ። ሐውልት እንኳ ይናገራል ። አድር ባይ ግን ባዶ ነው ። ከሥራህ ላይ ቤተ ክርስቲያን ሳትጠይቅህ አሥራት አውጣ ፣ ጉዳተኛው ወገንህ ሳይለምንህ መባውን ስጠው ። ይህ ውለታ ሳይሆን አንተ ጋ የተቀመጠ መብቱ ነው ። የውሸት ምክንያት ፈጥሮ የሚለምንህን እዘንለት ። እንዲዋሽ ያደረገው ያንተ ጨካኝነት ነው ።

ወዳጄ ሆይ !

ከመምራት መመራት ፣ ከማዘዝ መታዘዝ ይሻላል ። መሪ ያልሠራውን መልካም ነገር የራሱ አድርጎ በሌላው ጉልበት ይዘመርለታል ፣ ባልሠራውም ክፉ ሥራ ሲወቀስ ይኖራል ። ሙሴ የራሱን መቃብር እንደ ቆፈረ መሪ ስትሆን ጉድጓድ ቆፍሮ የሚቀብርህ የለምና መቃብርህን እየቆፈርህ እንደሆነ አስተውል ፤ ስትጨርስ ትወድቃለህ ። ማዘዝም በልግመኛ ትውልድ መካከል በሽተኛ ያደርጋልና አትምረጠው ። ስለ ነገሩ እውቀት በሌለህ ነገር ተቋም አትክፈት ። አለማወቅህን ካወቀ ሠራተኛም ይንቅሃል ።

ወዳጄ ሆይ !

ከአፈርነት የተነሣህ ሰው ፣ ወደ አፈር የምትመለስ ትቢያ መሆንህን አስበህ ለቆመው ክብር ፣ ለሚሞተው የሰውነት ሽኝት አትንሣ ። ማድረግ ባትችል በአሳብ እርዳ ። መርዳት እየቻልህ አሳብ አታብዛ ። አንተም ሞት አለብህና በሞተው ደስ አይበልህ ። የሚያረፍድ እንጂ በዓለም የሚቀር ሰው የለም ። ልጆችህ የአባቴ ልጅ ፣ የእናቴ ልጅ እያሉ እንዳይከፋፈሉ ሥራ ቀናልኝ ብለህ ሁለት ትዳር አትያዝ ። ደስታህን ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም መሻት አዳምጥ ። ላትፈጽም እሺ ብለህ ሰውን አታደንዝዝ ፣ በጊዜው የሆነ እንቢታ የውለታ ያህል ነው ።

መጻፍ የማይቻልበት ዘመን አለና እጽፋለሁ ፣ ማንበብ የማይቻልበት ዘመን አለና አንብቡ !!!

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ