የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምክር ለሰሚው/17

ጠንካራ ሁን

ወዳጄ ሆይ !

ጠንካራነት ብዙ የመገፋትና ተራራን የመግፋት ውጤት ነው ። ጠንካራነት ለፈተና ከማልቀስ ፣ ለችግር ብሶተኛ ከመሆን ለማሸነፍ በሚደረግ ትግል የሚገኝ ነው ። ጠንካራነት ታሪክን በማወቅ ፣ “ብዙ አልፌ እዚህ ደርሻለሁ ፣ ይህም ያልፋል” ከሚል ተስፋ የሚገኝ ነው ። ጠንካራነት ሥራ ሁሉ ተግዳሮት እንዳለው አውቆ በፎካሪዎች አለመደናገር ነው ። ጠንካራነት ሁሉም የሚሆነው እግዚአብሔር ሲፈቅድ ነው ብሎ ፍርሃትን ድል መንሣት ነው ። ጠንካራነት በችግር ከማደግ ፣ እጅ ከማይሰጡ ወላጆች የመማር ውጤት ሊሆን ይችላል ።

ወዳጄ ሆይ !

ጠንካራነት ሌሎች ሲሠሩ “እንግዲያስ እኔ ልተኛ” ከሚል ጕንድሽ መንፈስ ሳይሆን “ለዚህች ዓለም እኔም ድርሻ አለኝ” ከሚል ልብ የሚወጣ ነው ። ጠንካራነት ስንፍናን የማሸነፍ ፣ ፍቅርን የማንገሥ ውጤት ነው ። ጠንካራነት “እኔ ለእኔ አላንስም” ብሎ ከግለሰቦችና ከመንግሥት ጥገኝነት መላቀቅ ፣ ለራስ ክብር መስጠት ነው ። ጠንካራነት “እኔም ለዓለም የምሰጠው አለኝ” ከሚል ባለ ራእይነት የሚመጣ ነው ። ጠንካራነት የሚደክመው ጉልበት ሳይሆን ልብ መሆኑን አውቆ ልብን በእግዚአብሔር ማበርታት ነው ። ጠንካራነት የሚኖሩበት ከተማ ፈርሶ ፣ ትዳር ተበትኖ ፣ ትላንት ያስቀመጡት ሁሉ ዱካው ጠፍቶ ፣ ለማልቀስም አቅም ጠፍቶ ሳለ እንደ ነቢዩ ዳዊት በእግዚአብሔር አምላክ ልብን አበርትቶ ለድል መውጣት ነው ።

ወዳጄ ሆይ !

ጠንካራነት ያመኑበት ነገር በሚያስገኘው ስኬት ሳይሆን በእውነትነቱ ብቻ ደስታዬ ነው ብሎ መቀበል ነው ። ጠንካራነት “ነብር እንኳ ሲሞት ቆዳውን ትቶ ይሞታል ፣ እኔ ምን ትቼ እሞታለሁ ?” ከሚል ቁጭት የሚመነጭ ነው ። ጠንካራነት እውቀት አለው ፣ በጥበብ ይናገራል ፤ ተግባር አለው ። ጠንካራነት ስሜት ሳይሆን ተግባር ፣ ፉከራ ሳይሆን ድርጊት ነው ። ጠንካራነት እንኳን ወኅኒ መቃብርም በር አለው ብሎ ማመን ነው ። ጠንካራነት ሞራል ነው ፣ ምግባር ነው ፣ ለአሳማሚዎች ታምሞ አለመጠበቅ ነው ። ታመህ ካልጠበቅኸው የሚያሳምምህ የለምና ።

ወዳጄ ሆይ !

ጠንካራነት ጨካኝነት አይደለም ። ጨካኝነት የፈሪዎች መገለጫ ነው ። ጠንካራነት ለድሀ ጆሮን መደፈን ፣ በሬሳ ላይ እየተራመዱ መኖር አይደለም ። ጠንካራነት ከቂም ጋር መርፌና ክር ሁኖ መጓዝ አይደለም ። ጠንካራነት ዝናብ እንዳይዘንብ መፈለግ ሳይሆን ዶፉን እንዴት አመልጣለሁ? ብሎ ማለም ነው ። ጠንካራነት ለመቀበል ሳይሆን ለመስጠት የመነሣሣት ብፅዕና ነው ። ጠንካራነት አድርጉልኝ ሳይሆን ላድርግላችሁ የሚል መንፈስ ነው ። ጠንካራነት የመብልን ያህል ሥራን የሚወድድ ነው ። ጠንካራነት የመንፈስ ልዕልናና ልመናን መጠየፍ ነው ። ጠንካራነት በድሮ ዝናና በትላንት ታሪክ ሳይሆን በዛሬ ሩጫ የሚያምን ነው ። ጠንካራነት ከወላጆች ፣ ከመምህራን ፣ ከመሪዎች ሊወረስ የሚችል መልካም ሀብት ነው ። ስንወጣ ስንገባ ዓይናችን ከሚያያቸው የኑሮ ታጋዮች ፣ የካቡት ሲናድ እንደ ገና ለመካብ ከሚፈልጉ ጽኑዓን የምንማረው ነው ።

ወዳጄ ሆይ !

ኑሮ ዳገት ሲሆን ፣ ሩጫህ ነቍጥ ትርፍ ሲያጣ ፣ ማስተማርህ የጨለማውን መንግሥት አልገስስ ሲልህ ፣ ልብስህ አካሉን ፣ ቤትህ ትዳሩን አልሸፍን ሲል ፣ ለኩራት የሚበቃ አገር ስታጣ ፣ ለመኖር የማይመች ዘመን ሲመጣ ፣ የለፋህበት ባልለፉ ሰዎች እጅ ላይ ስታየው ፣ ሌባ እየተሸለመ ሐቀኛ ሲደፋ ጠንካራ ሁን ! ጠንካሮች ይሻገራሉ ፣ ሊያልፍ ቀን ራሳቸውን የሚያሳልፉ ግን በምድር በሰማይ ይከሰሳሉ ። ጠንካራነት የድሆች ፣ ጠንካራነት የባለጠጎች ሳይሆን ጠንካራነት ነገን ያዩ ተስፈኞች ነው ።

እኮ ጠንካራ ሁን !!!

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ