የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምክር ለሰሚው /2

ወዳጄ ሆይ !

ስድስት ቀን ሮጠህ ያልሞላኸውን ኑሮ ሰባተኛውን ቀን በመሮጥ ሰንበትን ለሥጋ ሩጫ በማዋል አትሞላውምና የእግዚአብሔርን ቀን ለእግዚአብሔር ስጥ ። የእጅህ ሥራ እንዲባረክ የገንዘብ አሥራት ፣ ዘመንህ እንዲባረክ የቀን መባ ለእግዚአብሔር ያስፈልገዋል ። በምድር ላይ በረከትና ጤና የጠፋው የሰንበት ሥራና ትምህርት ከመጣ በኋላ ነው ። አባቶችህ የእግዚአብሔርን ቀን ላለመንካት በሰንበት ሳይሆን ማክሰኞና ሐሙስ ሰርግ ይደግሱ ነበር ። ስድስቱ ቃላተ ወንጌልን ተምረህ የምትፈጽመው በሰንበት ነው ። እሑድ በጥንቱ የፍጥረት መጀመሪያ ፣ በአዲስ ኪዳን የሞት መደምደሚያ ነው ። ፍጡር ነህና ግብርህን የምትከፍልበት የአምልኮ ቀንህ ሰንበት ናት ፣ ሞት እንደ ሕፃን የተገሠጸልህ የታደልህ አማኝ ነህና የጌታህን ቀን አክብር ። የንጉሥ ቀጠሮ ቢተዉት ያስቀጣል ፣ ቢረሱት ያስቀስፋል ። ዘመንህ እየፈጠነ በከንቱ እንዳያልቅብህ ፣ ቀንህ ያለ ሕሊና ትርፍ እንዳይጋልብብህ የጌታህን ቀን አትዳፈር ። ሰንበት ማለት ትርጉሙ ሰባተኛ ቀን ፣ ካህን ማለትም አገልጋይ ማለት መሆኑን የረሱ አላዋቂዎች በአዲስ ኪዳን ሰንበትም ካህንም አይባልም ይሉሃልና ከአላዋቂ ሳሚዎች ራቅ ።

ወዳጄ ሆይ !

ከመንደርህ የተለየ ሰው ለመሆን የአረማመድ ቄንጥህን ፣ ከከተማህ የተለየ ሽቅርቅር ለመባል አለባበስህን ፣ ከአገርህ የተለየ ለመሆን አነጋገርህን ፣ ከዓለም የተለየህ ለመባል ራእይህን አታብለጭልጭ ። የአካሄድ ቄንጥህ ዱላ ስትይዝ ፣ ባለ ሦስት እግር ስትሆን ያበቃል ። የምትበላው ሲዝረከረክ ነጩ ልብስህ ያድፋል ። ንግግር አሳማሪም ሞቱን ያከፋል ። ራእዩን የሚነግድበት በነፍሱ ይከስራል ።

ወዳጄ ሆይ !

ያደረግኸውን ክፉ ያደረግኸው ከዘመኑ ላለመለየት እንጂ አምነህበት አይደለም ። ያደረግኸውን ደግ የከወንከው ለሰው አዝነህ ሳይሆን ደግ ለመባል ነው ። ሳታምንበት ያደረከውን ክፉ እግዚአብሔርን ፈርተህ አቁመው ። ለስምህ ግንባታ ያደረከውን መልካም ነገር ሕሊናህን አፍረህ አርመው ።

ወዳጄ ሆይ !

ያለ ሥራ ያለ አእምሮ ይቅር ያለውን በደል ያስታውሳል ። የተወውን ኃጢአት ይከልሳል ። ገሸሽ ያሉትን ሰዎች ይፈልጋል ። እልህ ውስጥ ገብቶ ከታናናሾቹ ጋር ይጋፋል ። ምንም ቢቸግርህ አስተሳሰቡ አነስተኛ ከሆነ ሰው ጋር አትጣላ ። ለእርሱ ክብር ፣ ላንተ ውርደት ነውና ።

ወዳጄ ሆይ !

ቀኑ ሲያስፈራህ ፣ ቀኑ የእግዚአብሔር ባሪያ መሆኑን አትዘንጋ ። ሰዎች ሲያስፈራሩህ የተወለዱበትን እንጂ የሚሞቱበትን ቀን እንደማያውቁ አስተውል ። ሁኔታዎች ሲያስደነግጡህ የማይለወጠውን ጌታ ተጠጋ ። ራስህ ሊያመልጥህ ሲታገልህ “ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ፣ ትዕግሥትን ስጠኝ” እያልህ ያለ ማቋረጥ ጸልይ ።

ወዳጄ ሆይ !

ከሠራኸው ቤትህ ያከራየሃቸው ተቀምጠው ያንተ ሬሳ ይወጣል ። የሰሰትህለትን ንብረት ወይ መንግሥት ወይ የጠላኸው ይወርሰዋል ። የኖርህለትን ዓለም ወደ ኋላህ ጥለህ ትሄዳለህ ። እነዚያ እንደ ሄዱ አንተም ትሄዳለህ ። ሄዱ ብለህ አትዘን ፣ ቀረሁ ብለህ አትመካ ። ለሞቱት ማዘንህ ሙት ለሙት ማልቀሱ ነው ። መታበይህ ሞትን መዘንጋትህ ነው ። መንገደኛ ፊትና ኋላ ነው ። ዛሬ ማታ የሰማይ መንገድ ልትጀምር ትችላለህና ከአፍህ ክፉ አይውጣ ። ከቀሪ ጋር አትቃቃር ። እጆችህ በደካማው ፈትል ይገነዛሉና በእጆችህ ሰው አትግፋ ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ሚያዝያ 7 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ