ወዳጄ ሆይ !
መነሻ ቦታዎችህን አትርሳ ። ንጹሕ ፍቅር ያሳለፍህባቸውንና የልጅነት ሩጫ የሮጥህባቸውን መንደሮች በየጊዜው ጎብኝ ። ያደግህበትን ደሳሳ ጎጆ ለማሳየት ፣ ከኑሮ የተነሣ የጠወለገች እናትህን ለማስተዋወቅ ድፈር ። ሕፃንነትህ መነሻ ነውና ባትወልድም ለሕፃናት ራራ ። ራቁትነት ስትወለድ የነበረህ ድህነት ነውና የተራቆቱትን አልብስ ። በኮልታፋነት ቋንቋን ጀምረሃልና አላዋቂዎችን ታግሠህ አስተምር ። ተሣሥተህ የለመድከውን ሙያ ሰዎች ሳይሳሳቱ መፈጸም አለባቸው ብለህ ግብዝ አትሁን ።
ወዳጄ ሆይ !
የተሰወረ ኃጢአት ይዘህ የተገለጠ በደል ያለባቸውን አታዋርድ ። ፊደል መቍጠር መነሻህ ነውና ዛሬ ምንም ሊቅ ብትሆን ፊደል ያስቆጠሩህን አክብር ። መስበክ ስትጀምር ፈርተህ ነበርና አዳዲስ ሰባኪዎችን አበረታታ ። ከዓለም ጥልፍልፍ በጸጋው ወጥተሃልና ኃጢአተኞችን ዋጋ የላችሁም አትበል ። ፍቅርን በመስጠት ወላጆችህ ቀዳሚ ነበሩና አንተም ቀድመህ ሰውን ውደድ ። የሰው አገር ስትሄድ ልብህ ፈርቶ ነበርና እንግዶችን በርኅራኄ አስተናግድ ። መጀመሪያ ቀን ንግግር ለማድረግ እንቅልፍ አጥተህ ነበርና ሰዎች ሲፈሩ አበረታታ ። ከዚህ በፊት የማታውቀው ሞት ይጠብቅሃልና ለሚሞቱት በልክ እዘን ። ኖረህ ሳትጨርስ በማንም አትፍረድ ።
ወዳጄ ሆይ !
ተክል የሚያድገው በተተከለበት ስፍራ ነውና በተተከልህበት ቤተ ክርስቲያንህ ፍሬ አፍራ እንጂ የሃይማኖት ለዋጮችን ክፉ ግብር አትከተል ። ወዳጅ ስትቀይር ወላጅ አልቀየርህምና በእግዚአብሔር ቃል የወለዱህን አትካድ ። ከሰው ተምሬአለሁ ለማለት አፍረህ በቀጥታ ከእግዚአብሔር ሰማሁ ብለህ አትገበዝ ።
ወዳጄ ሆይ !
በአጠቃላይ የሰውን ዘር እወዳለሁ ማለት ቀላል ነው ። አንድን ሰው መውደድ ግን ዋጋ ያስከፍላልና ብርቱ ነው ። እውነትን ጠብቅ ትጠብቅሃለች ። የዕረፍት ሰዓትና ቀን ከሌለህ የምትቆየው ለጥቂት ዘመን ነው ። በጎ እውቀትን ለመስማት ናፍቆት ከሌለህ ለሆድህ ያደርህ ከንቱ ሰው ነህ ። እስካገኝ ምንም መስጠት አልችልም አትበል ፤ ከመልካም ቃል የበለጠ ምጽዋት የለምና ። ለገላህ ውኃን ፣ ለነፍስህ ንስሐን አትንሣቸው ። ሥራ ፈትነት የዲያብሎስ ነጻ ቅጥረኛ ያደርጋልና ራስህን በሥራ ጥመድ ። ልምምድ ጥራትን ያመጣልና ንግግርና ሥራን ተለማመድ ። በጥረቶችህ ተስፋ አትቍረጥ ፣ ጥረቶችህ ባካናውን አእምሮህን ይዘውልሃልና ተሳክቶልሃል ። መልካም ነገርን ተቀባይ ብቻ አትሁን ፣ አንተም ስጥ እንጂ ። ለማወቅ የማይፈልጉ በመኖራቸው ተስፋ የቆረጡ ናቸው ።
ወዳጄ ሆይ !
የነገርን መሠረቱን ሳታውቅ ውሳኔ ለመስጠት አትቸኩል ። የሁለቱንም አቤቱታ ሳታደምጥ በአንዱ ንግግር ፍርድ አትስጥ ። ፍርድ የሰጠኸው በደለኛ አታለልሁት ሲልህ ፣ ፍርድ ያጓደልህበት ለሞት ያስብሃል ። ለወዳጅ መናገር ፣ ለእግዚአብሔር በጸሎት ማወጅ ነጻ አእምሮና ዕድሜን ይሰጣል ። እኔ የሚል ንግግር አታብዛ ። በደልህን እኔ ብለህ ተናገር ፣ መልካምነትህ በአፍህ አታውራ ። በትልቅ ስብስብ ፣ ትንሽ ስብሰባ አታድርግ ። ቤተ ክርስቲያንህን በማኅበር ፣ አገርህን በፓርቲ አትለውጥ ። የአገርህ ሕዝብ ካንተ የሚፈልገው እንድታለቅስለት ሳይሆን እንዳታስለቅሰው ነው ። ለሰዎች ካንተ የተለየ አሳብ እንዲያስቡ ፍቀድላቸው ። የፈጠረህን ክደህ ፣ የሚያከብርህን ልጅ አትጠብቅ ።