የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምክር ለሰሚው /26

ወዳጄ ሆይ !

እኔ እንጂ እነርሱ ምን አለባቸው ? አትበል ። ብዙ ባለበት ዓለም ምንም የሌለበት ፍጡር የለም ። ሕፃናትም በረሀብ ፣ ልጆችም በበሽታ ይሰቃያሉ ። እንስሳትም በሰው የመጣውን ሐሣር ይካፈላሉ ። አንተ ስላለህ ሁሉ ያለው አይምሰልህ ። አንተ ስላጣህም ሁሉ ያጣ ሁኖ አይሰማህ ። እየጠፉ ስላሉ እንስሳትና እጽዋት ስትቆጭ ፣ በየቀኑ ደብዛቸው ስለሚጠፋ የሰው ልጆችም አስብ ። ብርታት ሌላውን ከማበርታት ይገኛል ። ሌላውን ስታበረታ አንተም በርትተህ ትገኛለህ ። ፎካሪ ባያበረታ ወታደር አያሸንፍም ነበር ። ዕድል እግዚአብሔር የሰጠህ ነገር እንጂ ገና ከመሬት ወድቆ የምታገኘው የዳቦ እንቅፋት አይደለም ።

ወዳጄ ሆይ !

እልህ ከራስ ጋር ገመድ መጓተት ነው ። የማይቀጥሉ ነገሮችን መሬት ላይ አስቀምጣቸው ፤ አየር ላይ ከተበተኑ ጉዳት ያመጣሉ ። “የጨዋ ልጅ ሲፋታ የሚጋባ ይመስላል” እንዲሉ ። የሃያ ዓመቱም የሰማንያ ዓመቱም ሁለቱም የዕድሜ ስስት አለባቸው ። በምናልባት መኖር ጉልበት ይጨርሳል ። ውሳኔ ማጣትም ዕድሜን ይፈጃል ። መኖርህ አለመኖር እንዳይሆን ከጠበኛ ሰው ጋር አትዋል ። እንዳትዋረድ ክፉ ጠባይህን አርቅ እንጂ እንዳያዋርዱኝ ብለህ እግርህን አታሳቅቅ ። ተአምር ወደ ቤተ ክርስቲያን ይስብ ይሆናል ፣ በቤተ ክርስቲያን ግን አይተክልም ።

ወዳጄ ሆይ !

አእምሮአቸው ለከዳቸው እዘንላቸው ፣ ብቻቸውን አይሞቱምና ። ለሚለምንህ እንደምትሰጥ ለሚጥር ሠራተኛም ስጥ ። ከልመና ሌሎችን ለማውጣት ወደ ልመና የሚሄዱትን መገደብ ይገባል ። ለመስጠት ግዳጅህ ከእግዚአብሔር የተቀበልህ መሆንህ ነው ። ለመስጠት መስፈርትህ ጉድለቱንና የነገ ተስፋውን ማየትህ ነው ። የመስጠት ምክንያትህ አንተ ጋ የተቀመጠ የመለኮት አደራ ስላለ ነው ።

ያጋሩ