የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምክር ለሰሚው /27

ወዳጄ ሆይ !

አዲስ ግኝት የመሰለህ እውቀት ከራስህ የመነጨ ሳይሆን እግዚአብሔር ከሰጠህ አእምሮና መብራት የተገኘ ነው ። እግዚአብሔር በሰዎች በኩል አያስተምረኝም አትበል ። እግዚአብሔር ብሉያትን በነቢያት ፣ ሐዲሳትን በሐዋርያት አስተምሯል ። እነማን እንዳዋለዱህ አስበህም ጠይቀህም ፣ አመሰግናለሁ ብለህም አታውቅ ይሆናል ። አንተ እግዚአብሔርን እንድታውቅ የደከሙልህ ቅኖች ፣ የወለዱህ አስተማሪዎች ትልቅ ዋጋ አላቸው ።

ወዳጄ ሆይ !

እውቀትን የጣለ እምነት ፣ እምነትን የጣለ እውቀት አይኑርህ ። እውቀት የሌለው እምነት ራስን ማደንቆር ነው ። የሚታወቅ ነገር ሳለ ፣ ማወቂያ መሣሪያው አእምሮ ከተሰጠ የማወቅ ግዳጅ አለብህ ። ሰውን ሰው የሚያደርገው በእውቀት የተፈጠረና በእውቀት የሚያድግ መሆኑ ነው ። እምነት የሌለው እውቀት ማለስለሻ እንደሌለው ተሽከርካሪ እርስ በርሱ የሚፋጭ ፣ ድምፁ የሚረብሽ ፣ ዕድሜው የሚያጥር ነው ።

ወዳጄ ሆይ !

መዝሙር መዘመር የተፈጠርህበት ዓላማ ነው ። መዝሙር እንድታዳምጥ ሳይሆን እንድትዘምር ተፈጥረሃል ። መዝሙር በለሆሳስ የማይደረስ የዜማ ጸሎት ነው ። መዝሙር ምስክርነትና መንፈሳዊ አዋጅ ነው ። መዝሙር እንኳን በአርአያ ሥላሴ የተፈጠረውን ሰው አእዋፋትንና እንስሳትን ሳይቀር የሚማርክ ረቂቅ ጣዕም ያለው ነው ። ዜማን ማጣጣም ውስጣዊ ምላስ ያለው ሰው መገለጫ ነው ። አእምሮህ በተወጠረ ጊዜ ፣ የገዛ አካልህ እንደ በድን በላይህ ላይ የተከመረ በመሰለህ ወቅት ፣ ድባቴ ውስጥ ገብተህ አልሰማ አለማ ስትል ፣ ሁሉም ነገር ጣዕም ሲያጣብህ ፣ ያለህ ነገር እንደሌለህ ሁኖ ሲሰማህ ፣ ያሳለፍከውን ዕድሜ በዜሮ ስታባዛ መዝሙር ጀምር ። ጉዳይህ ሳይሆን እግዚአብሔር ትልቅ ሁኖ ይታይሃል ። ዜማ ስታወጣና ስትጮህ ሥጋህና ነፍስህ ይነቃቃል ። ደግሞም በሰማይ ስትሄድ የዘላለም ሥራህ መዘመር ነው ። በምድር ካልጀመርከው በሰማይ የሚቀጥል እንድም በጎ ነገር የለም ።

ወዳጄ ሆይ !

የሆነው መሆን ስላለበት ነው ። ፍርሃትም የታዘዘ ነገርን አያስቀርም ። “ወደ ፈተና አታግባን” ብሎ መጸለይ ግን ከታዘዘ መከራ ያድናል ። በፈቃድህ ወደ ዓለም አልመጣህምና ያለ ፈቃድህ የምትቀበለው ነገር እንዳለ አትርሳ ። እንዴት ይህ ይደርስብኛል አትበል ። ከሁሉ በላይ የሆነው ጌታ ሰው ሁኖ መከራ ደርሶበታል ። መከራ የጥሩነትና የመጥፎነት መገለጫ ሳይሆን ሰው የሆነ ሁሉ የሚቀበለው ዕዳ ነው ።

ወዳጄ ሆይ !

“ሰዎች ምን ይፈልጋሉ ?” ብለህ እንደ ሆቴል አስተናጋጅ ሜኑ ይዘህ አትዙር ። ያየኸውን ዓላማ ፣ የተሰጠህን ተልእኮ ፣ የሚያስከፍልህን ዋጋ ፣ የምትደርስበትን ግብ ፣ ሥራህን የምትገመግምበት የጊዜ ሰሌዳ አስቀምጠህ ወደ ሕይወት ሰልፍ ዝመት ። ዜግነትህን በመወለድ ፣ እምነትህን በማመን ያገኘኸው እንጂ ሰው በቸርነቱ የሰጠህ አይደለም ። ሰውም ሊነሣህ አይችልም ። ጸጋዬ ከሌሎች ጸጋ ያንሳል ብለህ አትፍራ ። ከትልቁ እግዚአብሔር የተቀበልነው ትንሽ ስጦታ የለም ። ለእርሱም ክብር ምስጋና ከልባችን እስከ አርያም ይሁን ። አሜን ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ