የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምክር ለሰሚው /32

ወዳጄ ሆይ !

መቶውን ብር ሰጥቶ አሥሩን ብር ስጡኝ የሚል ፣ ሳምንቱን አድሎ ሰንበትን የሚጠይቅ ጌታ ፤ ተቀብሎ እንደገና አብዝቶ የሚሰጥ አምላክ ከእግዚአብሔር በቀር የለም ። የገንዘብ አሥራትህን ለእርሱ ፣ የዕድሜ አሥራትህን ለሕያውነትህ ምሥጢር አትከልክል ። ከአሥር አንድ ብታወጣ አሥራትህን መልሰህ የምትበላው ፣ የምትገለገልበት አንተው ነህ ። ሰንበትን ብታከብር ለሥጋህ ዕረፍት ፣ ለነፍስህ እፎይታ የምታገኘው አንተው ነህና ለራስህ ምቀኛ እንዳትሆን ተጠንቀቅ ። አሥራትም ላለፈው ተቀብያለሁ የምትልበት ምስጋና ፣ ለሚመጣው እንዳትራብ ዘር ነው ። አሥራትን አለመክፈል አልተቀበልኩም ብሎ እግዚአብሔርን መክሰስ ነው ። ሰንበትንም አለማክበር አልደረስኩም ብሎ ራስን መርገም ነው ። ያንተ ያንተ እንዲሆን ፣ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጥ ። አሊያ መንግሥታት አስጨንቀው ፣ ሌቦች ዘርፈው ፣ ጨካኝ ገዥዎች ወርሰው ባዶ ያደርጉሃል ። በሚያልፈው ገንዘብና ዕድሜ እግዚአብሔርን አክብርበት ።

ወዳጄ ሆይ !

ለሰዎች መንገዱን ታሳያቸዋለህ እንጂ አንተ አትሄድላቸውም ። መድኃኒቱን ብትውጥላቸው ከበሽታቸው አይድኑም ። ስላላቸው ነገር አንተ ብትደሰት እነርሱ ፍሡሐን አይሆኑም ። ሰዎች ከእግዚአብሔርና ከራሳቸው ጋር እንዲገናኙ ምከራቸው ። ራሳቸውን ጠልፈው የሚጥሉ ሰዎችን በትዕግሥት እንጂ በጉልበት አታስተምራቸውም ። መጽሐፍን የሚጠሉ ሰዎች አብረው ምግብን ቢጠሉ መልካም ነበር ። ሰው ሥጋውን ብቻ ሲመግብ ሥጋዊ ፣ መንፈሱን ሲመግብ መንፈሳዊ ይሆናል ። በእንጀራ ብቻም አይኖርም ፣ በቃሉ ብቻም አይኖርምና በእንጀራና በቃሉ ኑር ። እንጀራ ብቻ ከሚሉ ሆድ አደሮች ፣ ቃሉ ብቻ ከሚሉ ሰነፎች ተጠበቅ ።

ወዳጄ ሆይ !

ጸጋ ተሰጥቶአቸው ጸጋን የሚጠብቁ የዘነበው ዝናብ ካልዳመነ የሚሉ ናቸው ። ሥራ እያላቸው ሥራ የሚፈልጉ ሲናወጡ የሚኖሩ ናቸው ። ጊዜ ተሰጥቶአቸው ጊዜ የሚፈልጉ በራሳቸው የሚቀልዱ ናቸው ። ብዙ ወገን በዙሪያቸው እያለ ብቸኝነት የሚሰማቸው ራሳቸውን ብቻ የሚያዩ ናቸው ። ችሎታ እያላቸው በሰው ችሎታ የሚቀኑ የመለወጥ አሳብ የሌላቸው ናቸው ። የእኔ አገር እያሉ የሚያዳንቁ የሚያወሩለት እንጂ የሚሠሩለት አገር የላቸውም ። የእኔ አሳብ ብቻ የሚሉ አፍ እንጂ ጆሮን የከሰሩ ናቸው ። ጥረትን የማይፈልጉ ድኩማን ናቸው ። ማግኘትን ወደው መስጠትን የሚጠሉ ምንም የማያገኙ ናቸው ። አንተ ግን ያለህን ነገር ተመልከት ፣ የጎደልህን ታጣዋለህ ።

ወዳጄ ሆይ !

መሰባሰብ ብዙዎች እንዲደመጡ ነውና በብዙሃን መካከል ብቻህን ተናጋሪ አትሁን ። እቅዶች ሳይኖሩህ የሰዎችን ዕቅድ አትተች ። ስታስጥል የምታስጨብጠውን ቀድመህ አስብ ። ማፍረስ ቀላል ነውና የመገንባት ሊቅ ሁን ። ማስተማር እንጂ መቅጣት ቀላል ነውና በመቅጣት አትመን ። አሻራህ በሰዎች ላይ እንዲኖር እያንዳንዱን ደቂቃ ለመልካም አጋጣሚ ተጠቀምበት ። ደግነትህ አጠገብ ስሌት ካለ ድካምህ ከንቱ ሁኖ ይቀራል ፤ የደከምህላቸውም ሰዎች ይጠሉሃል ።  ድክመቶችህን የሚያውቁ ሰዎች በዚያ ሊያጠቁህ ይሻሉና ራስህን አበርታ ። በውበትህ የሚሳቡ ሰዎችን ፣ ውበት ያለው ቆዳ ላይ እንደሆነ ንገራቸው ። ቆዳ ሲላጥ ሁሉም ሰው አንድ ዓይነት ነው ። ያላገባኸው ያገቡ ሰዎችን ስትመክር ሊሆን ይችላልና የሌሎችን ልምድ በራስህ ላይ እየተረጎምህ ከምትፈልገው ትዳር አትራቅ ።

ወዳጄ ሆይ !

እምነትህን አንተ በምግባርህ ፣ ሰዎች በቀልድ እንዲንቁት አትፍቀድ ። እምነትህ ከሁሉም ነገርህ በላይ ነው ። ከሞት በኋላ የሚከተልህ ዜግነትህ ሳይሆን ሃይማኖትህ ነውና ሃይማኖትህን ነቍጥ እንደሌለበት ፀዓዳ ተመልከተው ። በማስተማር የሚደክሙትን አክብር ። መብራት ቢጠፋ እንደምትጨነቅ ፣ አስተማሪዎች ሲጠፉም ሕይወት ትጨልማለች ። ዘመኑ ያስጨነቀን ሁሉ ባልጎ ገላጋይ በመጥፋቱ ነውና መካሪ አታሳጣን ብለህ ጸልይ ።

ምክር ለሰሚው 32

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ሰኔ 9 ቀን 2015 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ