የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምክር ለሰሚው/5

ወዳጄ ሆይ !

መንገዱን ከያዝኸው የቀረህ መራመድ ነው ። መንገዱን ባለማወቅ ካወጣኸው አቅም ይልቅ በመንገዱ ለመሄድ የምታወጣው ጉልበት ትንሽ ነው ። መንገዱ የጠፋው ሰው ጥርጣሬና መንከራተት ላይ ነው ። ጥርጣሬ የነፍስ ማዕበል ፣ መንከራተትም በከንቱ መድከም ነው ። የሚጓዝና የሚንከራተት ልዩነት አለው ። የሚራመድ ግን ግቡን አይቷልና በቶሎ ይደርሳል ። የሚንከራተት የበለጠ ጉልበት አውጥቶ ከመነሻውም ከመድረሻውም ሳይሆን ይቀራል ። ለመንከራተት ያልሰሰትከውን ጉልበት ለመራመድ አትቆጥበው ።

ወዳጄ ሆይ !

ለሕይወትህ አቅጣጫ ካልሰጠኸው ሁኔታዎች የሚመሩህ ፣ መሪ የሌላት ጀልባ ትሆናለህ ። ቀዛፊ የሌላት ጀልባ በነፋሱ አቅጣጫ የምትጓዝ ናት ። ሕይወትህም ዓላማ ከሌለውም የቀኑ ወሬ ፣ የሳምንቱ ዘፈን ፣ የወሩ ፊልም ሲወዘውዝህ ይኖራል ።

ወዳጄ ሆይ !

ውረድ እንውረድ ማለት ያለበት ሞት የሌለበት ብቻ ነው ። ሁልጊዜ ገዳይ አትሆንምና አንድ ቀን ሟች ነህ ። ሞቶ ተመልሶ የመጣ ሰው አታውቅምና የራስህንም የሰዎችንም ሕይወት ከማጨለም ተጠንቀቅ ። አነሰብኝ ጎደለብኝ ያልከው ስለኖርህ ነውና ስለ መኖርህ አመስግን ። ሲያነጋልህ ላላስከፈለህ ጌታ የማለዳ ምስጋና ለማቅረብ አትዘግይ ። ወጥቶ የመግባት ዋጋው ትልቅ ነውና የምሽት ጸሎትን አታስታጉል ። በውሎህ መኪናህ ቢገለበጥ ሚሊየን ብር ከስረሃል ። ልጅህ አደጋ ቢደርስበት በአልጋህ ሳይሆን በመፍትሔ ፍለጋ ላይ ነበርህ ። እያጣጣርህ ስለ ጤና ከመጸለይ በጤናህ እግዚአብሔርን አመስግን ።

ወዳጄ ሆይ !

ክህደት ሁለት ዓይነት ነው ። አንደኛው እግዚአብሔር የለም ማለት ሲሆን ሁለተኛው የበልቶ ካጅ ክህደት እርሱም እግዚአብሔርን አለማምለክ ነው ። በአንድ ገበታ ተቀምጦ መብላት በሰማይም በምድርም የታመነበት ሐቁ “ያፋቅራል” የሚል ነው ። ጌታችን ቅዱስ ቍርባንን በመብል በመጠጥ ያደረገው ለዚህ ነው ። የገባው ሲወጣ ፣ የወጣው ይገባልና ብዙም አትደሰት ፣ ብዙም አትከፋ ። ልክ የሌለው ደስታ ዝንጉ ፣ ልክ የሌለው ኀዘን ከሀዲ ያደርጋል ።

ወዳጄ ሆይ !

ዲያብሎስ ለገሀነም ርስቱ እየሠራ አንተ ለመንግሥተ ሰማያት ርስትህ አትስነፍ ። እምነት ብቻ ከሚሉ ሰነፎች ፣ ምግባር ብቻ ከሚሉ ትዕቢተኞች ተጠበቅ ። ከዛሬ የተሻለ ምቹ ቀን የለም ። ዛሬ የጨበጥከው መክሊትህ ነገ የምትናፍቀው ገንዘብህ ነው ። ከተሰጠህ የበለጠ ትልቅ ነገር የለም ። የጨበጥከውን ባልጨበጥከው ነገር አትዘንጋው ። ጥያቄ እጠይቃለሁ ብለህ መመለስን ፣ አከብራለሁ ብለህ ማዋረድን ፣ ንግግር አሳምራለሁ ብለህ ማስቀየምን ፣ አንዱን ከፍ አደርጋለሁ ብለህ ሌላውን ማኮሰስን ካንተ አርቅ ። ሰይጣን የሚገባው በተከፈተ በር ነውና በርህን ሳትዘጋ ተፈተንሁ አትበል ።

ወዳጄ ሆይ !
ጉልበት ይደክማል ፣ እውቀት ይሻላል ፤ ጥበብ ይሻራል ዘመድ ይበልጣል አትበል ። የማይጠልቀው ፀሐይ እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ቀኑ መብትህ ሳይሆን ስጦታህ ነውና አመስግንበት ። እሰይ ነጋ ማለት ሲገባህ ደሞ ነጋ አትበል ። የምትሰጠው ሰው የሚሰጥህ አለው ። ከሥርህ ያለው አንተ የማትችለውን የሚችልልህ ነው ። ቆጥረህ ከሰጠህ ስጦታህ ይረክሳል ። ደብቀህ ከሰጠህ ስጦታህ ሲወራ ይኖራል ። ከፍ ስትል ሁሉም ሰው ስትወድቅ ያይሃል ። በከፈትክለት መጠን ጠላት ይገባል ። ሰይጣን አስገድዶ ሳይሆን አዘናግቶ የሚገድል ጠላት ነው ። መውለድ ምጥ ፣ ደስታም ጭንቅ አለው ። እንደ ብቸኛ ልጁ የሚወድህን አምላክ ፣ ብቸኛ አምላክህ አድርገው ።

ክብር ምስጋና ለሥላሴ ይሁን !

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ