ወዳጄ ሆይ !
ወደድሁት ያልከውን ሰው ጠላሁት ብለህ ለመናገር አትቸኩል ። የእገሌ ፍቅር ሻሽ አያደርቅም ይሉሃል ። ያከበርከውን ሰው አታዋርድ ። ክብር ፌርማታ የለውምና እስከ መጨረሻው ይጓዛል ። ፌርማታ ላይ የሚወርድ ተሳፋሪ እንጂ ሾፌሩ አይደለም ። አንተም በራስህ አመለካከት ያከበርከውን ሰው መልሰህ አትንቀውም ። ጎድሎ ብታገኘው ሰው መሆኑ ነው ። ቀርበህ የምትርቅ አትሁን ። እንስሳ እንኳ አጣርቶ ይቀርባል ፣ ከዚያ ወዲያ ይዋዳጃል ። ቀርበህ የምታጣራ ንዑስ አትሁን ። ማንንም ሰው አልጠላም ማለት ማንንም ሰው አልወድም ማለት ነው ። የእግዚአብሔር ሕግ አትጥላ ሳይሆን ውደድ የሚል ነው ።
ወዳጄ ሆይ !
እግዚአብሔር በሰው ይወደዳል ፣ ሰውም በእግዚአብሔር ይወደዳል ። ሰውን ስትወድ የእግዚአብሔር ፍቅር በውስጥህ አለ ማለት ነው ። እግዚአብሔርንም ስታይ ሰዎችን ለመውደድ አቅም ታገኛለህ ። ከፊል ሕይወት የሕይወት ኑፋቄ ነው ። የጥርጥር አሳብ የተዘራበት ሰው በንስሐና በትምህርት ካልወጣለት ሕይወቱ ሁሉ ከፊል ነው ። ልብ አድርግ ዓለመ መላእክት በዝሙት ሳይሆን በኑፋቄ እንደ ወደቀ አስታውስ ። ግማሽ ክብር ፣ ግማሽ ፍቅር ፣ ግማሽ ትዕግሥት ፣ ግማሽ ቸርነት የሕይወት ኑፋቄ ናቸው ።
ወዳጄ ሆይ !
እግዚአብሔርን በሰው ፣ ሰማይን በምድር አጀንዳ አትለውጥ ። ከቤተሰብህ የሚበልጠውን ፣ ከሞት ባሻገር የሚዘልቀውን የክርስቲያን ጉባዔ አታቃልል ። በሕይወትህ ውድቀት የሚገጥምህ የማይነጻጸረውን ስታነጻጽር እንደሆነ ተረዳ ። በጡረታው የሚለምን ሰው ስታይ ሰርቀህ እንጂ ሠርተህ ለመጦር አትፈልግም ። መቃብር ስፍራዎች የቆሻሻ ተራራ ሲሆኑ ስታይ መሞት ያስፈራሃል ። የሰለጠኑት ሕዝቦች ተረጋግተው የሚኖሩት በድካም ዘመናቸው መንግሥታቸው ስለሚንከባከባቸው ነው ፣ ሞትንም የማይፈሩት መቃብራቸው እንኳ በክብርና በውበት ስለሚጠበቅ ነው ። ስለዚህ አንተም ለድካምህ ዘመን የምትሆን አገር ለማግኘት ዛሬ አትዝረፍ ። ሞትም የሕይወት አካል መሆኑን ተረድተህ እንኳን ለቆመው ለሞተውም የክብር ስፍራ ይኑርህ ።
ወዳጄ ሆይ !
መላእክትን የገረማቸው የክርስቶስ ትንሣኤ ሳይሆን ሞቱ ነው ። ሰውን ግን የገረመው ትንሣኤው እንጂ ሞቱ አይደለም ። ድኛለሁና ክርስቶስን ሞት ማሰብ አያስፈልገኝም አትበል ። ክርስቶስና መስቀል አይነጣጠሉምና ። ጌታችን በዕለተ ምጽአት ሲገለጥ የከፈኑን ጨርቅ ሳይሆን የተወጋው ጎኑን እያሳየ እንደሚመጣ አትዘንጋ ። እንኳን ዛሬ በምጽአትም የማይረሳ ሞቱ ነው ።