የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምክር ለሰሚው /8

ወዳጄ ሆይ !

በዓለም ላይ ትልቁ ውሸት ሰነፍ ማልዶ ለሥራ ተነሣ የሚለው ነው ። ለወሬ የጎበዙ ፣ ለሥራ ደካማ ናቸው ። ሰነፍ ማለት ለመብል የሚፈጥን ፣ ለሥራ የሚያዘግም ማለት ነው ። ሰነፍ ወጥ መቅመስ እንጂ መሥራት አይሆንለትም ። ትችት እንጂ ማሳያ የለውም ። እነዚህ እጆችህ አንድ ቀን ይታሠራሉና ዛሬ ሥራባቸው ። እነዚህ እግሮችህ አንድ ቀን ተግባር ያቆማሉና ወደ እግዚአብሔር ቤት ገስግስባቸው ። ርግማን የሚደርሰው የሠራኸው ሥራ ክፉ በመሆኑ እንጂ ተራጋሚው ጻድቅ በመሆኑ አይደለም ። ኖኅ ሰክሮ ቢረግመው ካም እንደ ተረገመ ቀርቷል ።

ወዳጄ ሆይ !

መሐል ሰፋሪ ስትሆን ከሕሊናህ ፣ ከሰው ፣ ከሁሉ በላይ ከእግዚአብሔር ትርቃለህ ። ከመሐል ሰፋሪው ጲላጦስ ጌታን የሰቀሉት አይሁድ ጠላትነታቸው ግልጽ ነው ። የሁሉን ወዳጅነት የሚፈልግ ሁሉም ጠላት ይሆንበታል ። መሐል ሰፋሪ ፍርድ አያውቅም ። በርባንን አጽድቆ ፣ ኢየሱስን ይሰቅላል ። መሐል ሰፋሪ ራሱ ስለማይገድል ይጽናናል ፣ ሰዎች የሚጋደሉበትን መድረክ ግን ያዘጋጃል ። መሐል ሰፋሪ እጁን መታጠብ ቢወድም ፣ ደም በውኃ አይነጻም ። ከሚያገሣ አንበሳ የሚለሰልስ እባብ ጎጂ ነው ። ልብን የሚያለዝብ ቅባት ያስፈልግሃል ። ሸካራ ልብ የሚያሰቃይ ድምፅ አለው ። ልብ የሚለዝበው በፍቅር ፣ በይቅርታ ፣ በቀና አመለካከት ነው ። ልብህ እግዚአብሔርን የምታነግሥበት መናገሻ ከተማ ነውና ንጽሕናው የተጠበቀ ይሁን ። ብዙ ጊዜ ከማቀድ አንድ ጊዜ መጀመር ፣ ብዙ ጊዜ ከማልቀስ አንድ ቆርጦ ከኃጢአት መውጣት የተሻለ ነው ።

ወዳጄ ሆይ !

ወንዶችና ሴቶች አንድ ዓይነት ጥንካሬና የሕይወት መልክ የሚኖራቸው በክርስቶስ ሲያምኑ ነው ። በክርስቶስ ያመነች ነፍስ ወንድነትና ሴትነት ሳይሆን ክርስቶሳዊነት ይታይባታል ። እርሱ በገዛ መልኩ ወንድና ሴትን አንድ ሊያደርግ መጥቷል ። እኔ ወንድ ስለሆንሁ ፣ እኔ ሴት ስለ ሆንሁ ፣ አስተዳደጌና ጠባዬ የሚል ሰው አማኝ አይደለም ። ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን የእግዚአብሔር ነውና ሰዎች ይቅር በለኝ ሲሉህ “ሁላችንን እግዚአብሔር ይቅር ይበለን” ብለህ መመለስ አለብህ ። ቅንዓት የተሞላ ሕይወት ሲቅበጠበጥ ይኖራል ። ተቀምጠህ የሰቀልከውን ቆመህ ማውረድ እንዳይቸግርህ ከፍ የምታደርገው ሰው ማን መሆኑን አስቀድመህ እወቅ ። ባለጌን ምክር እንጂ ሥልጣን ጨዋ አያደርገውምና ይለወጣል ብለህ አትሹመው ።

ወዳጄ ሆይ !

ፍቅር ተግባር ሲያንሰው ማብራሪያ ይበዛዋል ። እግዚአብሔር እንኳ ሰዎችን እወዳለሁ ብሏልና ፍቅርህን መግለጥ ተሸናፊነት አይደለም ። ከልጅነት ጀምሮ ያልታከሙ ቍስሎች ካሉ ሰዎች ርእስ ያለው ወጥ ንግግር መናገር አይችሉም ። አንዱን ጀምረው ወዲያው በማቆም ሌላ አዲስ ወሬ ይጀምራሉ ። የተሰጠህን ነገር በዋጋ አትፈልገው ፣ በዋጋ የሚገኘውንም በነጻ አትከጅለው ። የተሰጠህን በዋጋ ስትፈልገው ታቃልለዋለህ ፣ በዋጋ ያገኘኸውን በነጻ ስትፈልገው ትሰንፋለህ ። ጠርተህ ያመጣኸው ቢያውክህ “አህያ ተማልላ ጅብ አወረደች” የተባለው ይፈጸምብሃል ። አገልግሎት ከሌለህ መገልገል ተስፋ እያስቆረጠህ ይመጣል ። የሚሰጥ እንጂ የሚቀበል ሁልጊዜ ደስተኛ አይደለም ። የቻሉ ሰዎችን ስታይ ያስቻላቸው ያንተ አምላክ ነውና በጸሎት ለምነው ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ