የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምክር ለወዳጅ — መቅድም

የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ…… ዓርብ የካቲት 7/ 2006 ዓ/ም
የአሳታሚው ማስታወሻ
ከዐሥራ ሁለት ዓመት በፊት ይመስለኛልአንድ ደራሲ መጽሐፍ አሳትመው በየመንገዱ ማስታወቂያሲለጥፉ አየሁ፡፡ ዕድሜአቸውየገፋ በምርኩዝ የሚደገፉ ነበሩ፡፡ እየተንገዳገዱ የስልኩ እንጨት ላይ ማስታወቂያውን ይለጥፋሉ፡፡ ዝርዝር አሳቡን አሁን ማስታወስ አልችልም፡፡ ርዕሱ ግን ከነድምቀቱ በውስጤ ታትሟል፡– «አንብቡ አንብቡ አንብቡ፡ ኧረ እባካችሁ አንብቡ፤» ይህን ጽሑፍ ባነበብኩ ጊዜ የብዙ ፀሐፊያንንልብ እንደ ሰበርን፣ የእውቀት እሳታቸውን ባለማንበብናበነቀፋ አፈር እንዳጠፋነውአሰብኩና ቆዘምኩኝ፡፡ወደ ኋላ ዞር ብዬ በርተው የጠፉትን ከዋክብቶች ለአፍታ አሰብኳቸው፡፡ ቀጥሎም እንኳን ከባድ ሕይወትን ከባድ ቃላትን የማይመራመረውን የላይ የላይ ብቻ የሆነውን ዘመነኛ ሰው ታዘብኩ፡፡እኔም ተመልካች ሳልሆን ተዋናይ ነኝና ራሴንም ወቀስኩ፡፡ «አንብቡ አንብቡ አንብቡ፤ ኧረ እባካችሁ አንብቡ፤»
የአገራችን ድህነት የሀብት ሳይሆን የአመለካከትመሆኑ ታውቋል፡፡ የዚህ ችግሩ ዋነኛው አለማንበብነው፡፡ ማንበብ ብቻውንም አያስመሰግንም የምናነበውን መምረጥም ግድ ነው፡፡ ወደ አፍ ውስጥ የሚገባ ሁሉ እውነተኛ መብል አይደለም፡፡ ብዙ አደንዛዝ ዕፆችም ወደ አፍ ውስጥ ይገባሉና፡፡ እንዲሁም የሚያንፀውን አለማንበብ የአእምሮ ድህነትን ያስከትላል፡፡
የሰባ ብር ፒዛ በግፊያ በሚበላባትከተማ ላይ የአራት ብር መጽሐፍን እንኳን የሚገዛ የሚመለከት ሰው አለመኖሩን ስናስብ በጣም እናዝናለን፡፡ ለሚጠፋ መብል እየተጋደልን ለማይጠፋው መብል ሰነፎች መሆናችን ያሳዝናል፡፡እውነተኛ ፀሐፍያን በአገራችን ያለ ተመልካች የሚሮጡ ሯጮችን ይመስላሉ፡፡ተመልካች በሌለበት የሚለማመድ እንጂ የሚሮጥ ሯጭ ባይኖርም ፀሐፍያን ግን በእውነት አሉ፡፡ ስለ ትክክለኛ ነገር ቢጽፉ የሚሰማቸው ስላጡ ስለ ብልግና መጻፍ የጀመሩ፣ ራስን የሚያሳይ መጽሐፍ ቢጽፉ ዝምታ ስለበዛባቸው የሰውን ነውር የሚጽፉ ፀሐፍያንን ስናይ እኛ ያሳትናቸው መሆናቸውንእንረዳለን፡
ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል፡፡ አካላዊ እድገታችንን ከመንፈሳዊ ዕድገት ጋር ከምናስ ድበት ነገር አንዱ ማንበብ ነው፡፡ አንድ መጽሐፍን ወደ ቤታችን ይዘን ስንገባ አንድ ባልንጀራ ይዘን ወደ ቤታችን መግባታችን ነው፡፡ የመጽሐፍ ባልንጀራ ፊት አይቶ የማያደላ፣ ሳያዳልል የሚገስጸንነው፡፡ የአምና ቃሉን ዘንድሮም የማይለውጥ ባልንጀራ መጽሐፍ ብቻ ነው፡፡ አጥኚዎቹ አንድ የእውቀት መለኪያ አስቀምጠዋል፡– «ሰው እውቀት የሚገበየው በመስማት፣  በማንበብ፣ በማጥናት ነው፡፡» ስለዚህ ተውሶም ሆነ ገዝቶ መጽሐፍን ማንበብና ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ 

ሕይወት ቀጣይነት ብቻ ሳይሆን ውበትም ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ሕይወት በመሆኑ ለተፈጠረውዓለም ቀጣይነት ብቻ ሳይሆን ውበትም ሰጥቶታል፡፡ቃሉ፡– «በመንፈሱ ሰማያት ውበትን አገኙ» (ኢዮ. 26.13) ይላልና፡፡ እግዚአብሔርየሚመኝልን እንድንኖርብቻ ሳይሆን በውበትም እንድንኖር ነው፡፡ ይህም ቅድስና «ክርስቶስን መምሰል» ነው፡፡ ልንኖረው የሚገባውንልከኛ ኑሮ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ኖሮ አሳይቶናል፡፡ እንዴት መኖር እንደሚገባን ግር አይለንም፡፡ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ በቃልና በኑሮ አሳይቶናልና፡፡
«ምክር ለወዳጅ» የሚለው ይህ መጽሐፍ በውበት ስለ መኖር የሚናገር ነው፡፡ ውበት ረቂቅ ነው፡፡ እርሱም ግብረ ገብ (ሞራል) ነው፡፡ የግብረ ገብ ዋጋ በረከሰበት በዛሬው ዘመን በተቃራኒው ደግሞ እግዚአብሔርን ፍለጋ ወደ ቤተ ክርስቲያን እየገሰገሱያሉ ትውልዶች በበዙበት ወቅት ይህ መጽሐፍ አጋዥ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ዲያቆን አሸናፊ መኰንን የዚህን መጽሐፍ ረቂቁን በሰጠን ጊዜ እያንዳንዳችንን የሚጠይቅ በመሆኑ አሳብ ከመስጠት በተሰጠን ዕድሜ ምክሩን ለመኖር ተመኝተነዋል፡፡
ይህ መጽሐፍ ለአንባብያን የተቀደሰ ማዕድ፣ የውስጣቸው መሠሪያ እንደሚሆንእናምናለን፡፡ ምክር ከመንፈስ ቅዱስ እንጂ ከዕድሜ አይደለም፡፡ ቃሉ፡– «በዕድሜ ያረጁ ጠቢባን አይደሉም. ሽማግሌዎችም ፍርድን አያስተውሉም» (ኢዮ. 32.9) የሚለው ዛሬም እውነት ነው፡፡ በፀሐፊው ሕይወት ላይ ያለፉት የሕመምና የእንግልት ዘመናት እነዚህን ከወለዱ እንኳን ሆኑ እንድንል አድርጎናል፡፡ ውድ አንባብያን፡ይህን መጽሐፍ ከፊት ለፊታችሁ ላይ ተቀምጦ እንደሚመክራችሁ ወዳጅ አድርጋችሁ ብታነቡት ትጠቀሙበታላችሁ፡፡ ለደረሰባችሁ ነገር መጽናኛ፣ ለሚደርስባችሁ ነገር መረጃ ይሆንላችኋል፡፡ ፍቅር ለሚገዛቸው ሰዎች መጽሐፉ የግል መልእክታቸው እንደሆነ እናምናለን፡፡ ሰው በገዛ ኃይሉ ምንም ሊያደርግ አይችልምና የምክሩን ባለቤት እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፡፡
አሳታሚው፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፤
መቅደም
           አንድ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ቆመና፡– «ጌታ ሆይ፡ተመልከት እጆቼ ንጹሐን ናቸው፡፡ ደም አላፈሰሱም፣ የሰው ገንዘብ አልቀሙም» አለ፡፡ እግዚአብሔርም ሲመልስለት፡– «ልጄ ሆይ፣አዎ እጆችህ ንጹሐን ናቸው፣ ግን ባዶዎች ናቸው» አለው ይባላል፡፡ ንጹሕ እጅ ግን ባዶ እጅ፣ ያልገደለ እጅ ግን ያላዳነ እጅ፣ ያልሰረቀ እጅ ግን ያልመጸወተ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ የለውም፡፡ ፖሊስ ንጹሕ እጅን፣ እግዚአብሔር ሙሉ እጅን ይወዳል፡፡ እውነተኛውመልካምነት ክፉ አለማድረግ ብቻ ሳይሆን መልካም ማድረግም ነው፡፡ የሚጎዳንን መተው ብቻ ሳይሆን ስለ ሌሎች ጥቅም መድከምም ነው፡፡ ሌላውን ያለ መንካት ግብረ ገባዊነት የተሟላ የሞራል ኑሮ አይደለም፡፡ሌላውን መዳሰስም ይገባል፡፡
           በቀደሙት ዘመናት ሰዎች ስለ መንፈሳዊ ነገር ስንነግራቸው ግብረ ገባዊ (ሞራሊስት) እንደሆኑና መንፈሳዊ ነገር እንደማያስፈልጋቸው ይነግሩን ነበር፡፡ «እኔ የሌላውን መብት አልጋፋም፣ የሰውን ገንዘብ አልፈልግም፣ አልጠጣም፣ምንም ዓይነት ሱስ የለብኝም ስለዚህ መንፈሳዊ ነገር አያስፈልገኝም . . .» ይላሉ፡፡ የሚዘረዝሩት የጨዋነት መስፈርት ግን የክርስትናንመስፈርት ያሟላ አይደለም፡፡ ክርስትና ከዚህ ይልቃል፡፡ ቢሆንም ዛሬ እንዲህ የሚልም እየጠፋ ነው፡፡ ሰው ራሱንም ለመግዛት አሳብ የለውም፡፡እግዚአብሔርም እንዲገዛውአይፈልግም፡፡ ከግብረ ገባዊነት እየራቅን ባለጌነትንዘመናዊነት ካደረግን ሰንብተናል፡፡ ዛሬ ራስን ስለመግዛት በድፍረት የሚናገር ማነው? ብዙ ትልልቅ ተብለው የሚታሰቡ ሰዎች በግብረ ገብ ወድቀዋል፡፡ብዙ ባለጠጎች የአደንዛዥዕፆች ተጠቂዎች ናቸው፡፡ ብዙ ደራስያን የባዕድ ነገር ጥገኞች ናቸው፡፡ ብዙ ባለሥልጣናት ምሳሌ የሚሆን ትዳር
የላቸውም፡፡ግብረ ገብነት የሌለው ማንኛውም እሴት (የኑሮ ትርፍ) በዜሮ የሚባዛ ነው፡፡ ዐሥር ሺህም ሆነ ሚሊየን በዜሮ ብናባዛው ውጤቱ ያው ዜሮ እንደሆነ ያለ ግብረ ገብነት (ያለ ሥነ ምግባርም) ማንኛውም ከፍታ ባዶ ነው፡፡
      አንድ ወዳጄ የሚሆኑ አባት በአንድ ወቅት እንዲህ ብለውኛል፡– «በቀደመው ዘመን በምዕራብ አገሮች ላይ የበዛው ክፉ ስለሆነ ሰዎች የሚደነቁት ደግ ሲያዩ ነበር፡፡ በአገራችንደግሞ በተቃራኒው ክፉ ሲታይ ለወራት ይወራ፣ ሁሉም ይደነቅ ነበር፡፡ ለምን? ስንል የበዛው መልካም ስለ ነበር ነው፡፡ አሁን ግን ክፉ ስለበዛ እንደ ምዕራባውያኑ በመልካም መደነቅ ጀምረናል» በማለት በሀዘን ስሜት አጫውተውኛል፡፡ ሥልጣኔ ወደ ኢትዮጵያ መግባት በጀመረበት ጊዜ የነበሩት አባቶች ሥልጣኔውን አድንቀው ግን መሰልጠን መሰይጠን እንዳይሆን እያሉ አስጠንቅቀዋል፡፡ ከሥልጣኔ ጋር ነውርን እንደ ክብር የሚቆጥር አስተሳሰብ አለና፡፡
በዛሬው ዘመን አገራት የሚለዋወጡት ልምድ የልማት ብቻ ሳይሆን የኃጢአት ልምዳቸውንም ጭምር ነው፡፡ አሁን ያለው ትውልዳችንም መንፈሱ በፈረንጆችቅኝ ስለተያዘ እንደ ፈረንጅ ለማሰብና ለመናገር ሲጥር ይታያል፡፡ የፈረንጅ አገር የእግዚአብሔር ገነት የመሰላቸው ወጣቶች እዚያ ከሄዱ በኋላ የጠበቁትንሥዕል ስለሚያጡ ለአእምሮ ጭንቀትና ለአደንዛዥ ዕፅ እየተዳረጉ ናቸው፡፡  አዲሱ ትውልዳችንፈረንጅ የሚያደርገውን ሁሉ እንደ ቅዱስ ስለሚያየውመልካምን ሥልጣኔ ሳይሆን ርኩሰቱን እየወረሰ የሌሎች አተላ ማፍሰሻ ሆኗል፡፡ የራሱን መልካም ከሌሎች ክፉ ጋር ማወዳደር እንኳ እያቃተው መልካሙን እየጠላ በክፉው ተይዟል፡፡ የራስን መልካም ክፉ አድርጎ የሚያሳይ፣የሌላውን ክፉ ደግ አድርጎ የሚያሳይ ይህ የመንፈስ ቅኝ ተገዢነት ነው፡፡ የአካል ቅኝ የግድ ሲሆን አንድ ቀን በትግል ነጻ ይወጣል፡፡ የአእምሮ እስረኛ ግን ቢታገሉለትምነጻ ለመውጣት አይፈልግምናጉዳቱ ከጉዳተኞች በላይ ነው፡፡ በርግጥ የሌሎች ሁሉ ክፉ፣ የእኛ ሁሉም ደግ አይደለም፡፡ይህን ሁሉ የምንመዝነውግን የሞራል (የሥነ ምግባር) መለኪያዎች መሰበክ ሲችሉ ነው፡፡
ከቀደሙት የአገራችንሰዎች ጋር ያለንን ልዩነት ስናየው በጣም ሰፊ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የቀደሙት ከሌሎች የመጣውን ሁሉ በጥንቃቄ ይመለከታሉ፡፡ የአሁን ትውልድ ደግሞ ከሌሎች የመጣውን ሁሉ እንደ መልካም ይቀበላል፡፡ ከዐርባና ከሃምሳ ዓመት በፊት የነበሩት የአገራችን ሰዎች ወደ ውጭ አገር የሚሄዱት በግድ ነው፡፡ ሄደውም እስኪመለሱ ይጨነቃሉ፡፡ አሁን ያለው ትውልድ ደግሞ ሳይሄድ ህሊናው ሄዶ በድኑ እዚህ የቀረ፣ አይመልሰኝ ብሎም ራሱን ረግሞ የሚሄድ ነው፡፡ ስለዚህ ከቀደሙት ጋር አሁን ያለው ትውልድ ሲነጻጸር ልዩነቱ ሰፊ ነው፡፡ ከዐርባ ዓመታት በላይ በፈረንጅ አገር የኖሩ አንድ ሽማግሌ ሲነግሩኝ፡– «በእኛ ዘመን የነበረው ትውልድ የአሁኑን ትውልድ ያህል ጥፋተኛ ነበር፡፡ ልዩነቱ ግን ትውልድ ለመመለስ ቢያስብ እንኳ እውቀቱ ነበረው፡፡ የአሁን ትውልድ ግን ለመመለስ እንኳ እውቀት የሌለው ነው» ብለዋል፡፡ ታዲያ ምን መደረግ አለበት?
በቤተሰብ ድርሻ ቁሳዊ ፍላጎትን ማሟላት የአባት ድርሻ ሲሆን የእናት ድርሻ ግን ልጆችን በሥነ ምግባር ማነጽ ነው፡፡ በአገርም አገርን ተግቶ ማልማት እንደ አባት የሆነው የመንግሥት ድርሻ ሲሆን ትውልድን በሥነ ምግባር መቅረጽ ደግሞ የእናት ቤተ ክርስቲያን ድርሻ ነው፡፡ ትውልዳችን በሥነ ምግባር እውቀት ማደግ አለበት፤ አሊያ ነባቢ እንስሳ (ተናጋሪ እንስሳ) እናፈራለን ማለት ነው፡፡
ትውልዳችን ለሃይማኖትፉክክርም ቢሆን የቤተ ክርስቲያንን ደጆች እየረገጠ ነው፡፡ ከመካከል ደግሞ በብዙ ጭንቀት የሚማቅቁ ወጣቶች አጽናኝና መካሪ ይፈልጋሉ፡፡ «የነብርን ጭራ አይዙም፣ ከያዙም አይለቁም» እንደሚባል ይህ ትውልድ ራሱ ከመጣ ልንይዘው ይገባል፡፡ አሊያ ካመለጠን ባላጋራችን እንደሚሆንእርግጥ ነው፡፡ ያላስተማሩትትውልድ ጠላት ነውና፡፡ ይህን ትውልድ ለማስተማርጊዜው አሁን ነው፡፡ አሊያ ከእኛ ተስፋ ካጣ አምኖ እንዳላመነሰው ያለ ተስፋ ይኖራል፡፡ ራሱንና አገሩን በሚያሳፍር ተግባር ላይ ይሰማራል፡፡ በክህደት ዘመኑ የሚወልዳቸው ልጆቹም ከሃድያን ይሆናሉ፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ሥነ ምግባርንናየመኖርን ጥበብ፣ ሕይወትን የሚለውጠውን የክርስቶስንየአዳኝነቱን ኃይል ልትናገር ይገባታል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን አደራዋን ዘንግታለች፡፡ እንደ ዘመኑ ለመናገር ትጨነቃለች፡፡ ግራ ለተጋባው ዓለም መፍትሔ አለኝ ብላ ማቅረብ አልቻለችም፡፡ ትውልዱም መድኃኒት እያለው ሲሞት አላዘነችም፡፡ ለተበተኑት ሰብሳቢ አልሆነችም፡፡ ከዓለም ተስፋ አጥቶ የመጣ ሕዝብ ከቤተ ክርስቲያን ተስፋ አጥቶ ሲሄድም አላሰበችበትም፡፡ ቤተ ክርስቲያንየድሆች መጠጊያ መባሏም የቃላት ቅንብር እንጂ ተጨባጭ እውነት አልሆነምናእግዚአብሔር ይድረስልን፡፡
17ኛው ክፍለ ዘመን በፈረንሳይአብዮት ወቅት ክፉኛ ረሀብ ተነሥቶ ነበር፡፡ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንምአንድ ጋዜጣ ታዘጋጅ ነበር፡፡ የጋዜጣውም ርእስ፡– «ቤተ ክርስቲያን እናት ናት፤ ቤተ ክርስቲያንአስተማሪ ናት» የሚል ነበር፡፡ በዚያ ክፉኛ የረሀብ ዘመን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንሰባት ግዙፍ መንበረ ጵጵስና ታሳንጽ ነበር፡፡ ታዲያ ናፖልዮን «ቤተ ክርስቲያን እናት ናት፤ ቤተ ክርስቲያን አስተማሪ ናት» የሚለው ጋዜጣ ሲደርሰው በቁጭት ስሜት፡– «ቤተ ክርስቲያንእናት ናት የሚለውን ሰርዙት፡፡ ቤተ ክርስቲያንአስተማሪ ናት የሚለው ግን ይሁን» አለ፡፡ ለምን? ቢሉት፡– «ልጇ እየተራበ ቤት የምታንጽ እናት የለችም» አለ ይባላል፡፡ እኛንም እንዲህ የሚለን ብናጣ ታሪኩ ተደግሟልና ተግሳጹ ይመለከተናል፡፡
ቤተ ክርስቲያን ትውልድን ለማትረፍ መነሻዋ ጊዜ አሁን ነው፤
ምክር ለወዳጅ- መጽሐፍ
ለሰባተኛ ጊዜ የታተመ
የመጀመሪያ እትም የካቲት 2002 ዓ/ም
አድራሻ 0911 393521/0911 678251
መ.ሣ.ቁ. 62552 አ.አ.

ያጋሩ