የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምኲራብ

                         
  የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ…………..እሑድ፣  የካቲት 22/  2007 ዓ.ም.

የእስራኤል ልጆች ከባቢሎን ምርኮ በኋላ በምኲራብ እየተገኙ እግዚአብሔርን ማምለክ ተለማምደው ነበር፡፡ መቅደስና ምኲራብ የሚባሉ ሁለት መንፈሳዊ መገናኛዎች ነበሩአቸው፤ መቅደስ የሚባለው በኢየሩሳሌም ብቻ የሚገኝ ስለ ኃጢአት ስለ ምስጋና መሥዋዕት የሚቀርብበት የብሉይ ኪዳን ማዕከል ነበር፡፡ ምኲራብ ግን ከባቢሎን ምርኮ መልስ ማለት ከክርስቶስ ልደት 500 ዓመት ቀደም ብሎ የተጀመረ መሰብሰቢያ ነው፡፡ በምኲራብ የሚደረገው መንፈሳዊ አገልግሎት ቃሉን ማንበብ መስማትና መተርጎም ነበር፡፡ ምኲራብ የቦታ ወሰን የሌለው በየመንደሩ ወይም በየአቅራቢያው የሚገኝ አጥቢያ ቤተ – ጸሎት ነው፡፡ ማንኛውም እስራኤላዊ በዓመት ሦስት ጊዜ በኢየሩሳሌም መቅደስ ተገኝቶ አምልኮን መፈጸም ግዴታው ነበር፡፡ በምኲራብ ግን በየዕለቱ እየተገኙ ቅዱሳት መጻሕፍትን በንባብ በትርጓሜ ይሰሙ ነበር፡፡ በዐቢይ ጾም ሦስተኛው እሑድ ምኲራብ ተብሎ ተሰይሟል፡፡ ጌታ በምኲራብ ተገኝቶ እንዳስተማረ ለመግለጥ ቅዱስ ያሬድ ዕለቱን ምኲራብ ብሎ ሰይሞታል፡፡ ያሬድ በመዝሙሩ፡- “ ቦኦ ኢየሱስ ምኲራበ አይሁድ ወመሐረ ቃለ ሃይማኖት ወይቤሎሙ ምጽዋት አበድር እምከዋት አነ ውእቱ እግዚአ ለሰንበት ወአቡሃ ለምሕረት ኢትግበሩ ቤተ አቡዬ ቤተ ምስያጥ ቤትየስ ቤተ ጸሎት ትሰመይ . . .”
 
ትርጓሜው፡- “ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኲራብ ገባ፡፡ የሃይማኖትን ቃል አስተማረ፡፡ ከመሥዋዕትም ምጽዋትን እወዳለሁ አላቸው፤ የሰንበት ጌታዋ የምሕረት አባቷ እኔ ነኝ አላቸው የአባቴ ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት ቤቴ የጸሎት ቤት ነው ይባላል፡፡ ምኲራብ ገብቶ ተቆጣቸው ዝም ይሉ ዘንድ ትምህርቱን የቃሉን ሞገስ፣ የነገሩን መወደድ፣ የአፉን ለዛ አደነቁ”በማለት ቅዱስ ያሬድ ዘምሯል፡፡

ቅዱስ ያሬድ ጌታችን በምኲራብ ስላደረገው ጉብኝት ሳይሆን ስለ አስተማረው የእምነት ቃል ገልጧል፡፡ ስለዚህ ምኲራብ የትምህርት፣ የተግሣጽ፣ የከበረውን ከተዋረደው ለመለየት የምክር ስፍራ መሆኑን ያትታል፡፡ የጌታ ትምህርትም እንኳን በሚወዱት በሚጠሉትም ዘንድ ጣዕም ያለው መሆኑን ቃሉ በሞገስ ወይም በመወደድ የሚሰማ መሆኑን ይገልጣል፡፡ ያሬድ ወንጌልን በዜማ እየሰበከ ይመሰክራል፡፡ በዕለቱም የሚነበበው የወንጌል ክፍል ዮሐ. 2÷ 12- ፍጻሜ ነው፡፡


 
ዮሐንስ ገና በሁለተኛው ምዕራፍ ላይ ስለ ጌታችን የመጨረሻ የአገልግሎት ሳምንት መናገር ጀመረ፡፡ ለምንድነው ይህንን መግለጥ የፈለገው? ስንል የእግዚአብሔር ቤት በቅድስና ክብሩ መቆየት እንዳለበት በአስቸኳይ ሊነግረን በመፈለጉ ነው፡፡ ዮሐንስ እንደ ሌሎቹ ወንጌላውያን የጌታን ተአምራት በሰፊው አልዘረዘረልንም፤ ከእጁ ተአምራት ይልቅ በቃሉ ትምህርት ላይ አትኲሯል፡፡ የክርስትና ታላቅ ትምህርት የሆነውን ዳግም ልደትን በምዕራፍ ሦስት፣ እውነተኛ የአዲስ ኪዳን አምልኮን በምዕራፍ አራት ለመግለጥ ቸኩሏልና ታሪኩን ትቶ መሠረታዊውን የክርስትና ትምህርት ጽፏልናል፡፡ አንድን ነገር ከተለያየ አራት አቅጣጫ ብንመለከተው እይታው የተሟላ እንደሚሆን እንዲሁም የጌታችንን ሕይወት እና ትምህርት ከተለያየ አራት አቅጣጫ ወንጌላውያኑ ዘግበውልናል፡፡ ይህም የተሟላ መልእክት ይሰጠናል፡፡ ዮሐንስ በምዕራፍ 2÷ 12 ጀምሮ ባለው ንባብ ጌታ ወደ ኢየሩሳሌምና  ወደ መቅደሱ እንደ ገባ ቤቱን ከነጋዴዎች እንዳፀዳ ትንሣኤውን እንዳወጀ ይነግረናል፡፡ ጌታ በኢየሩሳሌም ትልቅ ጉዳይ አለው፡፡  ትልቅ ጉዳዩ በመስቀል ላይ ስለ ኃጢአታችን ሞቶ ዋጋ መክፈል ነው፡፡ ይህም መላው  ዓለም የሚጠብቀው ሰዓትና ደቂቃ ነው፡፡ መዳን በትምህርት ሳይሆን በቤዛነት ብቻ የሚገኝ ነውና ቤዛ ኲሉ ዓለም ሆኖ ሊሰቀል ጊዜው ደርሷል፡፡ ስለዚህ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ በኢየሩሳሌም ያደረገው የመጀመሪያው ተግባርም መቅደሱን ከነጋዴዎችና ከንግዳቸው ማጽዳት ነው፡፡ የጌታችን የመጀመሪያ ሥራና ፍርድ የሚጀምረው ከቤቱ ነው፡፡ እግዚአብሔር ዛሬም ለፍርድ ከተነሣ የሚጀምረው ከቤቱ ነው (1ኛ ጴጥ. 4 ÷17)፡፡ ዛሬ ሴት ወንድ ትንሽ ትልቅ ሳይባል ሁሉም የሳተበት ዘመን ነው፡፡ እግዚአብሔር በፍርድ ከተነሣ የሚጀምረው ዓለማውያን ከሚባሉት ሳይሆን ከእኛ ነው፡፡ እግዚአብሔር በእኛ የሚያዝነውን ያህል በዓለማውያን አያዝንም፡፡ ብዙ ሰዎች ንጹሕ ውሃ ለመጠጣት ይጠነቀቃሉ፤ ነገር ግን ያመነዝራሉ፡፡ ቆሻሻ መልበስ አይፈልጉም፣ ነገር ግን በሌብነት ይጨቀያሉ፡፡ በእግዚአብሔር ቤት ያለውም ነገር ውጫዊ ጽዳት ውጫዊ ንቃት ነው፡፡ ዘመናዊነት የሚመስል ኃጢአትን መላመድ ዛሬም ሞልቷል፡፡ ዛፎች ባደጉ ቍጥር መጥረቢያ እንደሚሳል እንዲሁም ኃጢአት ባደገ ቍጥር ፍርድ ይሳላል፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ቤት በፍርድ ዋዜማ ላይ ነውና እግዚአብሔር በመልካም ያስበን!
 
ዮሐንስ ወንጌሉን ሲጽፍ፡- ‹‹የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር፡፡ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ››ይላል ( ዮሐ. 2፡13)፡፡ ይህ ሦስት ነገሮችን እንድንገነዘብ ያደርገናል፡-
1.     ኢየሱስ እንደሚሞት እያወቀ ወደ ኢየሩሳሌም መሄዱ ጀግንነቱን ያሳየናል፡፡
2.    የአይሁድ ፋሲካ ላይ የአማንያን ፋሲካ ሆኖ እንደሚታረድ፣ እውነተኛው የፋሲካው በግ ምሳሌና ጥላ የሆነውን ሥርዓት እንደሚያሳልፍ ያሳየናል፡፡
3.    ጌታ ኢየሱስ የሚያውቀው ስለ ሞቱ ብቻ ሳይሆን ስለ ትንሣኤውም እንደ ነበር ያሳየናል (ዮሐ. 2፡20–21)፡፡
 
ጌታችን ወደዚህ ዓለም የመጣው ለመሞት ቢሆንም ያለ ጊዜው ላለ መሞት ግን ተጠንቅቋል፡፡ ሄሮድስ ሊገድለው ሲል ሸሽቷል፣ አይሁድ በድንጋይ ሊወግሩት ሲሉ ከመካከላቸው ተሰውሮ ሄዷል (ሉቃ. 4፡29)፡፡ አሁን ግን ጊዜው ደርሷልና ለመሞት በታላቅ ጀግንነት ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ እንኳን ኑሮአችን ሞታችንም ፈቃዱን ሲያከብር በእውነት የእግዚአብሔር ልጆች ነን፡፡ እስራኤል ከግብፅ ምድር ሊወጡ ሲሉ ባረዱት የፋሲካ በግ ሞት በደጃፋቸው አልፏል፡፡ ስለዚህ ቀኑን ፋሲካ ወይም አለፈ ብለው ጠርተውታል፡፡ ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ሳምንቱ የፋሲካ ሳምንት ነበር፡፡ ፋሲካችን ሆኖ በመታረዱ ምሳሌ የነበረውን ሥርዓት አሳልፎታል(1ቆሮ. 5፡7)፡፡ እስራኤል በበጉ ደም የዳኑት ከሞተ ሥጋ ነው፡፡ እኛ የዳንበት የፋሲካው በግ ክርስቶስ ግን ያዳነን ከዘላለም ሞት ነው፡፡ ጌታችን ሞቱን በተናገረ ጊዜ ሁሉ ትንሣኤውንም ይናገር ነበር፡፡ ሞት በሌለበት ትንሣኤ የለም፡፡ ክርስቲያንም ስለ መከራው ብቻ ሳይሆን ስለ ክብሩም ስለሚመጣውም ዓለም መናገር አለበት፡፡ የክርስትናችን ሙሉ ገጽታ መከራ ብቻ አይደለም፡፡
 
ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም እንደ ገባ በቀጥታ የሄደው ወደ መቅደሱ ነው፡- “በመቅደስም በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችም ተቀምጠው አገኘ፤ የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው& የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ& ርግብ ሻጪዎችንም ይህን ከዚህ ውሰዱ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም፡- የቤትህ ቅናት ይበላኛል ተብሎ እንደ ተጻፈ አሰቡ” (ዮሐ. 2፡14-17)፡፡
 
መቅደሱ ከተቋቋመበት ዓላማ ወጥቶ ነበር፡፡ ስለዚህም የሚቆጭ አልነበረም፡፡ ለጸሎት የመጡ ሰዎች እዚያው ገብይተው ይሄዳሉ የሚል ዘመናዊ የሚመስል አስተሳሰብ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ካህናቱም ለአገልግሎት ሲገቡ እስክመጣ ሽጡልኝ እያሉ ነበር፡፡ ስለዚህ ጸሎቱ የሚደርሰው ለወጉ ነበር፡፡ ከልብ ባይጸልዩ ከልብ የሚነግዱ አገልጋዮች ተፈጥረው ነበር፡፡ ምን እሰጣለሁ ሳይሆን ምን እቀበላለሁ የሚሉ ነጋዴ አገልጋዮች መቅደሱን ሞልተውት ነበር፡፡ ጸሎት ለማድረስም የከብቱ ሽታና የገበያው ጫጫታ በፍጹም የሚያውክ ነበር፡፡ የሰው ቤት እንኳ ሥርዓት አለው፡፡ የእግዚአብሔር ቤት ግን ሥርዓት አጥቶ ነበር፡፡ ቤቱ ግን ባለቤት አለው፡፡ ባለቤቱ ሲመጣ እየቀጣ አስወጣ፡፡
 
የቤትህ ቅናት ይበላኛል
ቅናት አያስተኛም፣ ቅናት እሳት ነውና፡፡ ቅናት ማንም አይቋቋመውም፡፡ ቅናት ይሉኝታ አያውቅም፣ቅናት ያሰበውን እስኪፈጽም አይደክመውም፣ ቅናት ያከሳል፡፡ ሁለት ዓይነት ቅናት እንዳለ መጽሐፍ ቅዱስይነግረናል፡፡ የመጀመሪያው የሥጋ ቅናት ሲሆን ሁለተኛው ግን መንፈሳዊ ቅናት ነው፡፡ሥጋዊ ቅናት በሌሎች መልካም ዕድል ሀዘንተኛ መሆን ወይም ሁሉም የእኔ ብቻ ይሁን የሚል ነው፡፡ መንፈሳዊ ቅናት ግን መልካሙ ዕድል ከሰዎቹ እንዳያልፋቸው የሚሰማን ጥልቅ ጉጉት ነው፡፡ ሰው ሁሉ መልካሙን ያግኝ የሚልየፍቅር እንፋሎት ነው፡፡ ይህ ቅናት ነው ወንጌልን እንድንሰብክ የሚያደርገን፡፡ ይህ ቅንዓት ነው ራእይንየሚያነሣሣ ወይም ባለ ራእይ የሚያደርገን፡፡ ይህ ቅንዓት ልቻልህ ተብሎ የማይቻል ነው፡፡
 
እግዚአብሔር ተካደ፣ ማደሪያው ተደፈረ ብለው በዘመናት የቀኑ ብዙ ሰዎች ነበሩ፡፡ ነቢዩ ኤልያስ ለእግዚአብሔር የቀና ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስም ቤቱ የነጋዴዎች መጠራቀሚያ መሆኑን ባየ ጊዜ አዘነ፡፡ እየገረፈም ከቤቱ አስወጣቸው፡፡
 
ዛሬም የሚቆጭ እስኪጠፋ የእግዚአብሔር ቤት የንግድ ቤት ሆኗል፡፡ አገልጋዮች ሳይቀር በገንዘብና በሀብት የሚወዳደሩበት፣ ይህን ሀብት ከያዝኩኝ አገልግሎቱን ትቼላቸው እወጣለሁ የሚሉበት ዘመን ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቤት አደባባዮች ነፍስ ለመቀበል ሳይሆን ብርና ወርቅ ለመቀበል ተከፍተዋል፡፡ በልማት ስም ንግድ ተጧጡፏል፡፡ ስለተጨነቀው ወገን፣ በዕንባ ስለጨቀዩት ምእመናን የሚያስብ ለማሰብም ፈቃደኛ የሆነ ታጥቷል፡፡ ሁላችንም አንድ ስለሆንን ተዉ የሚል ጠፍቷል፡፡ በደንብ ያጠፋ ከተገኘ እንደውም ይሾማል፡፡ በቅድስና ብልጫ ሳይሆን በግፍ ብልጫ ታላቅ የሚባሉ በዝተዋል፡፡ ጠንቋዮችና ደብተራዎች ከወንጌል ሰባኪዎች ይልቅ ተፈላጊዎች ናቸው፡፡ አንድ ኃላፊነት የተሰጣቸው አባት ሲናገሩ፡- “ወንጌል ወንጌል ትላላችሁ፣ ወንጌል ካመጣው ገንዘብ ኤድስ ያመጣው ገንዘብ በልጧል” ብለዋል፡፡ በእግዚአብሔር ቤት  እንደ ቃሉ ማሰብ ቆሟል፡፡ እግዚአብሔር ገና የሚፈርድብን ሳይሆን አሁንም ያለው በፍርድ ክልል ውስጥ ነው፡፡ ፈጥነን ካልተመለስን ዛሬ የኮራንበት ካባና ቀፀላ የነገ ማፈሪያችን ይሆናል፡፡ የእግዚአብሔር ቅናት ይህን ያደርጋል!! 
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ