የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምድር የማን ናት?

                         ቤተ ጳውሎስ ሐሙስ ሐምሌ 5/2004 ዓ.ም.
የሕይወት ማሳያ (ግራፉ) ከፍና ዝቅ የሚል ነው፡፡ ሕይወት ቀጥ ያለ ጉዞ ያለበት ሳትሆን እጅግ ከፍታ፣ እጅግ ዝቅታ የሚታይባት መድረክ ናት፡፡ ማሳያው ከፍ ሲል የመጨረሻውን ዝማሬ መዘመር ተገቢ አይደለም፣ ቀጥሎ ዝቅ ማለት አለና፡፡ ዝቅ ሲል የመጨረሻውን ሀዘን ማዘን አይገባም፣ ምክንያቱም ቀጥሎ ከፍታ አለና፡፡ ከቀን ቀጥሎ ሌሊት፣ ከሌሊትም በኋላ ቀን መምጣቱ የተፈጥሮ ዙረት ወይም ዑደት ነው፡፡


ዘመናችን ክፉና አስጨናቂ እንደሆነ ቃሉ ይነግረናል፡፡ ነገር ግን ክፉና አስጨናቂ ነገሮች ዛሬ የተጀመሩ አይደሉም፡፡ ዛሬ በዓለም ላይ እንደ ድንቅ፣ እንደ አዲስ የሚታዩ ኃጢአቶች ከዛሬ ሦስት ሺህ ዓመታት በፊት ይደረጉ የነበሩ፣ ዛሬ በዓለም ላይ የምናያቸው መከራዎች በኖኅና በሎጥ ዘመን የወረዱ እንደነበሩ ቃሉ ይነግረናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያውቅ እግዚአብሔር እንጂ ዓለም አዲስ ሆና አትታየውም።

ታዲያ የእኛን ዘመን ልዩ የሚያደርገው ምንድነው; ስንል ሁሉም የጠፉበትና ዓለም ዓቀፋዊ ቅጣቶች የበረከቱበት ዘመን መሆኑ ነው፡፡ ሁሉም የጠፉ ሲሆን ካህንና ነቢይ፣ ሁሉም የተቀጣ ሲሆን የሚሸሽበት ስፍራ የለም፡፡ ሥልጣኔ፣ ፍልስፍና፣ ምድራዊ አቅም ሊያስወግደው የማይችለው ነገር ቢኖር ኃጢአት ነው፡፡ ኃጢአት በፍልስፍና ሊታወቅ ይችላል፣ ኃጢአት ግን በፍልስፍና አይወገድም፡፡ ኃጢአት የሚወገደው በተአምኖ ኃጣውዕ/ኃጢአተኝነትን በማመን/ እና በመንፈስ ቅዱስ ረድኤት በማመን ነው፡፡ ኃጢአት መንፈሳዊ ውጊያ በመሆኑ መንፈሳዊ የጦር ዕቃ ይፈልጋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ኃጢአት ዋጋ ያስከፍላል፣ ሰው ደግሞ የኃጢአትን ዋጋ በመክፈል ምሕረትን ማግኘት አይችልም፡፡ ስለዚህ ቤዛ ያስፈልገዋል፡፡ ቤዛ ኩሉ ዓለም የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ካልረዳን በቀር በፍላጎት ብቻ ነጻ መውጣት፣ በፍልስፍናም መቀደስ አይቻልም፡፡
ያለፉትን የታሪክ ዘመናት ስንመለከት ኃጢአት ብሔራዊ (አገራዊ) ነበር፡፡ በእኛ ዘመን ግን ድንበር የለሽ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን ድንበር የለሽ ኃጢአትም እያየን ነው፡፡ ድንበር የለሽ ሰላዮች፣ ድንበር የለሽ ግድያዎች፣ ድንበር የለሽ ዘረፋዎች፣ ድንበር የለሽ የሕጻናት ዝውውር፣ ድንበር የለሽ የሰዎች ሽያጭ፣ ድንበር የለሽ የዕፅ ዝውውር፣ ድንበር የለሽ የክህደት አስተምህሮ እያየን ነው፡፡ ኃጢአት የባሕርይ ድካም የሚባልበት ዘመን አልፎ ሥልጣኔና ምርጫ መሆኑን እያየን ነው፡፡ ሰው ለራሱ እግዚአብሔር በሆነበት  በዛሬው ዘመን የእግዚአብሔርን ሕግ መፈጸም አይፈልግም፡፡ የእስራኤል ዋና ከተማ ተደርጋ በዓለም የምትቆጠረው ቴሌ አቪቭ በግብረ ሰዶም ፈጻሚዎች ቁጥር በዓለም አንደኛ ደረጃ ላይ ደርሳለች፡፡ ቴሌ አቪቭ ላይ ቆመን ወደ ደቡብ ምሥራቅ ብንመለከት የሎጥ ባሕር ወይም የሙት ባሕር ተብሎ የሚጠራውን በጥቂት ኪሎ ሜትሮች እናገኘዋለን። ይህ ስፍራ የኃጢአት መታሰቢያ ነው። የሰዶም ከተማ በጥፋት የጨው ባሕር የሆነችበት መታሰቢያ ነው። የሰው ልጅ ትልቁ የመማሪያው መንገድ ቃሉ ነው፡፡ ከቃሉ ሊማር ካልቻለ ከታሪክም ሆነ ከቅጣት መማር አይችልም፡፡ ስለዚህ ዘመናችን ኃጢአትን በስሙ መጥራት ያልቻለ፣ ለራሱ አምላክ የሆነ፣ ከታሪክና ከቅጣት መማር ያልቻለ በብዙ ርእዮተ ዓለም የሚለያዩ አገሮች በኃጢአት የተስማሙበት፣ እርዳታ ለመስጠት እንኳ ኃጢአትን መቀበል አስገዳጅ ፊርማ የሆነበት ዘመን ነው፡፡ ዘመኑን ክፉና አስጨናቂ ያደረገው የእኛ ምርጫና ድንዳኔ ነው፡፡
የሰው ልጅ መለያየቱ ብቻ ሳይሆን አንድነቱም፣ በር መዝጋቱ ብቻ ሳይሆን በር መክፈቱም ነውር አለበት፡፡ ነቢዩ ጽድቃችን ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው/ኢሳ.64፡6/ ያለው በእውነት ልብ ይነካል፡፡ ኃጢአታችን ብቻ ሳይሆን መልካምነታችንም በእግዚአብሔር መልካምነት መፈተሽ አለበት፡፡
በሕይወታችን ልንሰማ የማንፈልጋቸው ነገሮች አሉ፡፡ ነገር ግን እንደ ቡፌ እየመረጥን መስማት በማንችልበት ዓለም ላይ ስላለን፣ እየሳቅን ማር እንደላስን ፊታችንን እያጠቆርንም ሬቱን እንልሳለን፡፡ ለማሩ ፈቃዳችን ይጠየቃል፣ መራራን መምረጥ ግን አይቻልም፡፡ ብዙ ዘመን ልንሰማ የማንፈልጋቸውን የወላጆቻችንን ሞት፣ የወዳጆቻችንን ክዳት፣ የጓደኞቻችንን ከጠላት ጋር መሰለፍ፣ የደቀ መዛሙርቶቻችንን አድማ፣ የትዳር ጓደኞችን መራራ ጽዋ ተቀብለን ይሆናል፡፡ ገና በአሳብ ፈርተን  እግዚአብሔር ሆይ ይህን አታሳየኝ ብለን የጸለይንበትን ነገር አይተነው ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ግን በማሳለፍ ብቻ ሳይሆን አሳይቶ በማስተማርም ይረዳናል፡፡ እግዚአብሔር መማር ያለብንን ነገር እንድንማር ይጨክናል፡፡ ትምህርት አስተማሪው እየጨከነ፣ ተማሪው ዋጋ እየከፈለ ካልሆነ ሊቀጥል አይችልም፡፡ « ያረፈደው ልጅ ስለሆነ ነው፣ የቤት ሥራ ያልሠራው ጨዋታ አታሎት ነው» የሚል መምህር ተማሪ አያወጣም፡፡ አስተማሪ በመጨከን ሰው ይፈጥራል፡፡ በፍቅር ጭካኔ፡፡ ልጅ ሳለሁ የሚወጋ ነገር እግሬ ውስጥ ከገባ የእናቴ ርኅራኄ አይረዳኝም ነበር፡፡ ጨካኟ ጎረቤት ግን ነቅለው ሲጥሉልኝ ልቅሶዬ ይቆማል፡፡ ካልጨከኑ እሾህ አይነቀልም፣ ልቅሶ አይቆምም፡፡
ከላይ ከጠቀስናቸው ነገሮች በላይ ልንሰማ የማንፈልገው የጠላታችንን ከፍታ ነው፡፡ በሕይወቴ ሰው ለሰው ጉድጓድ ሲቆፍር፣ መርዝ ሲበጠብጥ፣ ሥር ሲምስ፣ ቅጠል ሲበጥስ፣ ድንጋይ ሲፈነቅል፣ የሞት አዋጅ ሲያስነግር ሳይ ፣ ስሰማ አዝናለሁ፡፡ እኔም ከሰውነት ባሕርይ ነጻ ባልሆንም ማንንም ለመጥላት አልኖርኩም ብዬ በመጨረሻዋ ሰዓት ለራሴ መናገር እፈልጋለሁ፡፡ ሰው ለሰው ጉድጓድ ቆፋሪ መሆኑን ሳስብ የማዝነው፡-
1.     ምድሩ ሰፊ፣ የሚሠራው ብዙ ሳለ ሰፊው ምድር በአመል ጠቦ፣ ሥራ እንደሌለ ተንኰል ሥራ ሲሆን ማየት ያሳዝናል፣
2.    የምንኖርበት ዕድሜ በጣም ጥቂት ነው፡፡ ይሙት በቃ ብለን መፍረድ ብንችል እንኳ ቀጥለን አንዳንዴም ቀድመን እንሞታለን፡፡ ሟቹ ሰው ገዳይ ሲሆን ማየት ያሳዝናል፣
3.    የምንኖርበት ዕድሜ በዕርቦ የተሰፈረ እጅግ ጥቂት ዘመን ነው፡፡ ለ4ዐና ለ5ዐ ዘመን እንዲህ መባላታችን ያሳዝናል፡፡ ከጥቂት ደቂቃ በኋላ ምን እንደምንሆን እንኳ አናውቅም፡፡ ይህን ማንነት ይዘን አጥፊና ጠፊ መባላችን በመጨረሻ ሁላችንም ጠፊ መሆናችን ያሳዝነኛል።
4.    መከራና ፈተና በዓለም ላይ በዝቷል፡፡ በክረምት እባብና ጓጉንቸር አብሮ ይከርማል ይባላል፡፡ ምንም ባይስማሙ ክረምቱ እስኪያልፍ እባብና ጓጉንቸር ይስማማሉ፡፡ የኢኮኖሚ አለመረጋጋት፣ የበሽታ ብዛት፣ የረሀብ ስጋት፣ …. የተንሠራፋበት ዘመን ላይ ነን፡፡ በዚህ ክረምት ተስማምተን መኖር አለመቻላችን፣ ከእባብና ጓጉንቸር አንሰን መገኘታችን ያሳዝናል፡፡
5.    መፍትሔ መሆን የሚገባቸው የሃይማኖት ተቋማት የዓለም የችግር አካል መሆናቸው ያሳዝናል፡፡ ሃይማኖት ከመጀመሪያው ብንጀምር ከመጨረሻውም ሰላምን የሚሰብክ ነው፡፡ የሃይማኖት መሪዎች ሕዝቡን በአምላክ ስም እያስፈራሩ የሚዘርፉበት ሳይሆን ለዓለም ሰላም የሚደክሙበት ሊሆን ይገባዋል፡፡ አሁን ግን እያየን ያለነው ይህን አይደለም፡፡ ሰዎች ስለ እግዚአብሔር ብለው እየተሳደቡ፣ እየተጋደሉ ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ቅዱስ ነውና በኃጢአት አይከብርም፡፡
በሃይማኖት ስም ተቋቊሞ ስለሚበጠብጥ ስለ አንድ ማኅበር ከአንድ ሊቀ ጳጳስ ጋር ስንነጋገር እንዲህ አሉኝ፡- “ይህ ማኅበር የፖለቲካ ድርጅት እንዳንለው በሃሳብ ልዩነት አያምንም፣ የሃይማኖት ተቋም እንዳንለው ወንድሜ ይዳን ሳይሆን ይጥፋ የሚል ነው፡፡ ጀግና እንዳንለው ያለው በእኛ ቀሚስ ውስጥ ነው፡፡ እንዲያው ባጭር ቃል ቫይረስ ነው” አሉኝ፡፡ እንዲህ ያሉ የሰላም ተዋጊዎች የሃይማኖትን ስፍራ የሚመርጡት በቀላሉ ሊገኙ ስለማይችሉ ነው፡፡ የማያቋርጡ አብዮቶች መነሻቸው የሃይማኖት ተቋም ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካውም ሆነ የጥቁር አሜሪካውያን የነጻነት እንቅስቃሴ መነሻው ሃይማኖት ነው፡፡ እነዚህ በጥባጮች ረጅም ርቀት ለመጓዝ፣ ለዱላ ላለመመቸት፣ የብዙዎችን ልብ ለመያዝ ሃይማኖት ወሳኝ መሆኑን አስልተው የገቡ ናቸው፡፡ በሃይማኖት ጀምረው በፖለቲካ የሚያልቁ ያሳዝናሉ፡፡
ብቻ ለዛሬው ዘመን መባላታችን ያሳዝናል፡፡ ሰው፣ ሰው የሚባለው ዘመን በከፋበት ጊዜ ሲረዳዳ ነው፡፡ ከዘመን ጋር የሚከፋ የአውሬዎች አውሬ ነው፡፡ አንበሳ አውሬ ነህ ቢሉት እኔ የምገድለው ልበላው ነው፣ ሰው ግን ሰውን የሚገድለው ላይበላው ነው አለ ይባላል፡፡ በእውነት በአውሬ ከተበሉት በሰዎች የተበሉት በቁጥር ይበዛሉ፡፡ ሮማውያን፡- ለሰው አውሬው ሰው ነው የሚሉት በደንብ እየተፈጸመ ነው፡፡
ታዲያ ይህን ስናይ ክፉዎች እየተጉ ደጐቹ ነፍሳቸው ትጨነቃለች፡፡ ደጎቹ ምድር የክፉዎች ናት ብለው አሳልፈው ለመስጠት፣ በር ዘግተው ለመቀመጥ፣ ጊዜ ሞታቸውን ለመጠበቅ ይሰናዳሉ፡፡ ምድር ግን የማን ናት;
ውሎዬ ድካም ያለው ቢሆንም ሥራ ካደከመው ክፉ ዜና ያደከመው ሰውነት ይዝላል። ድካም ያስተኛል፣ ክፉ ዜና ይቀሰቅሳል። ግን ከዋሉበት ስሜት ጋር ላለማደር ፈውሱ ቃሉና ጸሎት ነው፡፡ በምሽቱ የሰማኹት ብዙዎች የሆኑ ወገኖች አንድ ሰው እንዴት ማጥፋት እንዳለባቸው ያወጡትን ዕቅድና ያንንም ዕቅድ ለማስፈጸም ጊዜአቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ሕይወታቸውንም ጭምር እንደሠዉ ሰማሁ፡፡ ይህ ሁሉ የስለላ መዋቅር፣ ይህ ሁሉ የዕዝ ሰንሰለት፣ ይህ ሁሉ የመግደል ስልት፣ ይህ ሁሉ የሠራተኞች ስምሪት ለምንድነው;
በከንቱ ጥላቻ፣ እንደ እኔ ካላሰብክ ብሎ ጦርነት ማወጅ ይህ ስልጣኔ ሳይሆን መሰይጠን ነው፡፡ በእውነት ሰው ለወንድሙ ጥፋት ሲባጅት መስማት አሳዝኖኛል፡፡ ይህች ምድር ለክፉዎች ተላልፋ ተሰጥታለች፡፡ በሰላም መሰብሰብ (ማለፍ) መታደል ነው ብዬ ተናገርኩ፡፡ ጥሩ መኖር ሲያቅተን በጥሩ መሞት ለካ ያምረናል፡፡ ኃጢአት ስህተት ሳይሆን ኃጢአት ዓላማና ዕቅድ ሲሆን ያሳዝናል፡፡
ታዲያ ወደ መኝታዬ ከማለፌ በፊት የዕለቱን ንባብ ከመዝሙር 84፡1 ላይ ገለጥሁ፡- ‘‘አቤቱ ለምድርህ ሞገስን አደረግህ’’ ይላል። መልሱን ስላገኘሁ በቁስሌ ላይ ዘይት ሲፈስስ ተሰማኝ። ጌታ ሆይ ተመስገን አልኩ። መልሱን ያገኘሁት ከሐረጉ ሳይሆን ከአንድ ፊደል ነው። የጌታዬ ቃል አንዱም ፊደል ያድናል። ‘‘ለምድር’’ ልቤ የተፈወሰው ምድር የእግዚአብሔር መሆኗን ሳስብ ነው። ክፉዎች ቢበዙ፣ ፍርድን በገንዘብ ቢያጣምሙ፣ ከቡድናቸው ውጭ ያለውን በረሀብ ለመቅጣት ቢሰናዱም አሁንም ምድር የእግዚአብሔር ናት። የእግዚአብሔር ልጆች ምድርን ለክፎች አሳልፋችሁ አትስጡ። ዛሬም ምድር የእግዚአብሔር ናት። አዋጁም በመርዶክዮስና በአይሁድ ላይ ይውጣ። አዋጅን በአዋጅ የሚሽር ጌታ ዛሬም ሕያው ነው። ለመግዛትና ለመነገድ የሐሳዊ መሲህ ቁጥር ይዘርጋ። መናን የሚያወርድ እግዚአብሔር ዛሬም ሕያው ነው። እነዚህ ሁሉ የምድሪቱ ባለጠጎች የምድሪቱ ሹመኞች ቢሆኑ እንኳ የምድሪቱ ባለቤት ግን የእኛ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሞገስ ማማር ነው። እግዚአብሔር ባለአደራዎቹ ሰዎች ያበላሿትን ምድር ያሳምራታል። ‘‘አቤቱ ለምድርህ ሞገስን አደረግህ’’  ይላልና። ምድር የማን ናት? አንተ ጎበዝ፣ አንቺ እህት ተማምናችሁ ውጡ። ይች ምድር እናንተን የሠራ ጌታ አበጅቷታል ፣ በእናንተም አገልግሎት በሞገስ ያሳምራታል።
                             ምድር የእግዚአብሔር ናት።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ