መግቢያ » ከመጻሕፍት » ወዳጄ ሆይ » ሠርከ ኅብስት

የትምህርቱ ርዕስ | ሠርከ ኅብስት

 

ወዳጄ ሆይ !

 

የቀሳውስትና የጳጳሳት ረድዕ ስትሆን አገልግሎትህን በክብር ለመፈጸም ምሥጢር ጠባቂ ሁን ። የገዳም አበምኔት ስትሆን አባትና እናታቸውን ትተው ለመጡ መነኮሳት አባትና እናት እንደሆንህ እወቅ ። 

ወዳጄ ሆይ !

መሠዊያ መሥዋዕትን ይጣራል ፣ መሥዋዕትም መሠዊያ ይፈልጋል ። ክርስትናም ዋጋ ከፋዮችን ይሻል ። ክርስቲያኖችም መሥዋዕት የሚሆኑለትን ዓላማ በትክክል ማወቅ አለባቸው ። ያለ ዋጋ የኖረ መልካም ነገር የለምና ያለ ዋጋም ነገ ላይ ማድረስ አይቻልም ። 

ወዳጄ ሆይ 

ወይን ጠጣ ብለው ግድ ሲሉህ እንዳይቀየሙኝ ብለህ አትጠጣ ። ራስህን መግዛት አቅቶህ ከሚታዘቡህ በቁጥብነትህ ቢቀምሁ ይሻላል ። 

ወዳጄ ሆይ !

አገልጋይ ሆነህ ስትታዘዝ አትከፋ ። ክርስቶስ የመጣው በባሪያ መልክ ነውና ። እርሱ በጌትነት አርአያ ቢመጣ አይደንቅም ነበር ። የዘላለም ጌታ በባሪያ መልክ መምጣቱ ግን ድንቅ ነው ። አገልጋይነትን ክርስቶስ ሥጋ ለብሶ የባረከው ተግባር ነውና ደስ ይበልህ ። አንተ የሰው አገር ተሰድደህ ተመችቶህ እንኳ ከፍቶህ ከሆነ ክርስቶስ ግን ወደማይመቸው ወደ ሲና በረሃ እንደ ተሰደደ አስታውስ ። አንተ ለምነህ እንጀራ ስታገኝ በእንባ ትጎርሰዋለህ ፣ ክርስቶስ ግን በመስቀል ላይ ተጠማሁ ብሎ ሆምጣጤ እንደ ሰጡት አስብና ትሑት ሁን ። አንተ በራስህ መቃብር ስትቀበር ክርስቶስ ግን በተውሶ መቃብር እንደ ተቀበረ እወቅ ። 

ወዳጄ ሆይ !

ማወቅ መልካም ነው ። የታላላቅ ሰዎችን ምሥጢር ለማወቅ መታደልም ደስ የሚል ነው ። ታላላቅ ሰዎች ከሰው የደበቁትን ምሥጢር ከነገሩህ በአንገትህ ሰይፍ ይዘህ እንደምትዞር እወቅ ። ዝምታና የምሥጢር መቃብር መሆን ብቻ ዕድሜህን ያረዝማል ። 

ወዳጄ ሆይ !

የምንሮጠው ለየራስ ነው ፣ የምንመገበው ግን ተመሳሳይ ነው ። አንዱ ያለ ዕረፍት ይሮጣል ፣ ሌላው እያረፈ ይሠራል ። የሚመገቡት ግን ተመሳሳይ ነው ። ወንዝ ብትወርድ የወንዙን ውኃ በሙሉ አትጠጣም ። እሸት ብትበላ የእርሻውን ፍሬ በሙሉ አትበላም። ተፈጥሮ ራሱ ልክህን እየነገረ በቃ ይልሃል ። ስለሚያስፈልግህ እንጂ ስለምትፈልገው ነገር አእምሮህን ሰላም አትንሣ ። 

ወዳጄ ሆይ !

ወፍ በቅርንጫፍ ፣ አይጥ በጉድጓድ ፣ ጉማሬ በባሕር ፣ ዝንጀሮ በገደል ፣ መላእክት በሰማይ ፣ ሰው በምድር ይኖራሉ ። ቅርንጫፍን መኝታ ፣ ጉድጓድን መኖሪያ ፣ ባሕርን ቤት ፣ ሰማይን አገር ፣ ምድርን ተስማሚ ያደረገ እግዚአብሔር ነው  ። እግዚአብሔር የመደበልህ ቦታ ከአደጋና ከሞት የምትተርፍበት ነው ። 

ወዳጄ ሆይ !

ባለመቻልህ አትበሳጭ ፣ ሰው ሁሉ ቢችል ኖሮ አንተን የሚያኖርህ ፣ አንተም የምታኖረው አይኖርም ነበር ። አለመቻል ጭምትና ጸሎተኛ ያደርጋልና ውደደው ። ምኞትህን እግር ካልሰጠኸው እያደከመህ ይመጣል ። እግዚአብሔር የሚባርከው ምኞትህን ሳይሆን ተግባርህን ነውና የተግባር ሰው ሁን ። 

ወዳጄ ሆይ !

ውኃ ራሱን ሳያረካ ሌላውን እንዳረካ ይኖራል ። ሌላውን ለማንጻት ብሎም ይቆሽሻል ። አንተ ግን ረክተህ የምታረካ ፣ ተቀድሰህ የምትቀድስ ሁን ። የሚበቃህን ካላወቅህ ከሰዎች ጋር ብቻ ሳይሆን ከገዛ ተፈጥሮህ ጋርም ግጭት ውስጥ ትገባለህ ። ቢፈቅዱልህም በሰዎች ነጻነት ውስጥ አትግባ ። 

ወዳጄ ሆይ !

ዮሴፍ በከነዓን ሲሸጥ በግብጽ ይገዙታል ። አንተም አንድ ቦታ አይፈልጉህም ሌላው ቦታ ግን በውድ ይገዙሃል ። ዮሴፍ ወንድሞቹ ሲገፉት ባዕዳን ይቀበሉታል ። እግዚአብሔርን የሚያውቁ ሲከፉበት አያውቁም የሚባሉ ይራሩለታል ። ወኅኒ ጣልነው ሲሉ ቤተ መንግሥት ያገኙታል ። መገፋትህ የእግዚአብሔር ክብር መገለጫ ይሆናልና ደስ ይበልህ ። እልፍ ስትልም እልፍ ታገኛለህ ። 

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ጥቅምት 19 ቀን 2013 ዓ.ም.

https://t.me/Nolawii

እባክዎ ይህን ቻናል ይቀላቀሉ፣  ለሌሎች ወገኖቻችንም ያስተዋውቁ

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም