የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሥጋዊ አሳቤ

 እንደ ሰላይ ወዳጅ መስሎ አቅሜን ይለካኛል ። አብሮኝ እየተጋበዘ መድከሜን ለጠላቴ ሰይጣን ያሳብቅብኛል ። የውጭውን ጠላት ስታገል በውስጤ ሥጋዊ አሳቤ ያደባብኛል ። ስቆጣ ሎሌ ፣ ስበርድ ጌታ እየሆነ ይመጣብኛል ። ክረምት ከበጋ ይተጋብኛል ፣ እኔ ተኝቼ ሥጋዊ አሳቤ ከተማ ያስሳል ። ለማመስገን ስነሣ ጉድለቴን ይቆጥርብኛል ። ለመንፈሳዊ ነገር ስታጠቅ በከንቱ ነገሮች ጊዜዬን ይበላል ። ሥጋዊ አሳቤ እንደ ክፉ ጎረቤት ይነዘንዘኛል ። አብረን ማርጀታችን ፣ ስንጣላ ስንታረቅ ዘመን ማሳለፋችን ይደንቀኛል ። ሥጋዊ አሳቤ አካሌ ደክሞ ሳለ ነፍሴን አባብሎ ይወስድብኛል ። ልብ አይሞትምና ነፍሴ ማድረግ ቢያቅታት በአሳብ ስትዘምት ትውላለች ። ነፍሴ በተመስጦ ወደ ሰማይ ስትሄድ ሥጋዬን ይሻረክብኛል ። ሥጋዬ አገሯ መሬት ነውና ከመሬት ስበት ጋር ወደ ታች ትጎትተኛለች ።
በሁለት አሳብ በደግነትና በክፋት ስንገላታ ሥጋዊ አሳቤ ብዙ መረጃዎችን እየጠቀሰ ክፋት ያስከብርሃል ይለኛል ። ነፍሴም መረጃ ከእምነት አይበልጥም ትለኛለች ። አስታራቂ መስሎ ሥራውን የሚሠራ ፣ ለደግነት ትቶ ለክፋት የሚያደላ ሥጋዊ አሳቤ እርሱ ይሞግተኛል ። መቅዘፊያዋን እንደ ጣለች ጀልባ አቅጣጫ እያሳተ ፣ የአሳብ ሰይፍ ፣ የበቀል ስለት እያስጨበጠ ሥጋዊ አሳቤ በቂም ያዘምተኛል ። ከክርስቶስ መከራ ያንተ ይበልጣል እያለ ያስታብየኛል ። ሥጋዊ አሳቤ ገላጋይ መስሎ የሚያስደበድበኝ ፣ ጠበቃ መስሎ የሚያስረታኝ ፣ ወዳጅ መስሎ ወደ ገደል የሚገፈትረኝ እርሱ ነው ። በዝማሬ ውዬ በልቅሶ እንዳድር ፣ በፍቅር ውዬ በቂም እንድሰክር የሚያደርገኝ ፣ አንዱን ቀን ሁለት የሚያደርግብኝ ሥጋዊ አሳቤ እርሱ ነው ።
እንደ ማጥ ጉዞ ወጣሁ ስል የሚይዘኝ ፣ ጨረስሁ ስል የሚያስጀምረኝ ፣ ሸመገልሁ ስል ልጅ የሚያደርገኝ ፣ ታጠብሁ ስል መልሶ የሚያቆሽሸኝ ፣ ተፋሁ ስል እንደ ውሻ የሚያስልሰኝ ሥጋዊ አሳቤ በክለሳ ኑሮ የሚያደክመኝ እርሱ ነው ። በእምነት ሰላሜን አገኘሁ ስል በአዳዲስ ጉድ የሚያናውጠኝ ፣ እጆቼን ፣ ዓይኖቼን ፣ ጆሮዎቼን እየኮረኮረ ክፉ ወሬ የሚያስቃኘኝ ሥጋዊ አሳቤ እርሱ ነው ። አዳም ሲወድቅ ውስጤ የገባው ረቂቅ መንግሥት ሥጋዊ አሳቤ ነው ። ሳላውቀው ከእኔ ጋር የኖረው ፣ ተገላገልሁት ለማለት የማልደፍረው ጠላቴ ሥጋዊ አሳቤ እርሱ ነው ። አገሬ በሰማይ ነው ስል ጎሣ የሚያስቆጥረኝ ፣ ተበደልሁ እንጂ በደልሁ የማያሰኘኝ ፣ መንግሥተ ሰማያት ላያስገባኝ ትክክል ነህ እያለ የሚያጸድቀኝ ሥጋዊ አሳቤ እርሱ ነው ። አገልግሎት ሕይወትህ ነው እያለ ከሰው የሚያጋድለኝ ፣ ሕይወት ክርስቶስ መሆኑን በዘዴ የሚያስጥለኝ ፤ ከመድረክ አትጉደል እያለኝ ከጽሞና የሚያጎድለኝ ፣ በዘዴ የጠለፈኝ ሥጋዊ አሳቤ እርሱ ነው ።
ኃጢአትን ጽድቅ ለማድረግ ሱባዔ የሚያስገባኝ ፣ ሃይማኖቴን ለመለወጥ የሚያጸልየኝ ሥጋዊ አሳቤ እርሱ ነው ። እንደ አቡን ሥልጣነ ክህነት የሚሰጠኝ ፣ ሳልሾም የተሾሙትን የሚያስንቀኝ ፣ የሕልም ዓለም የሚያወርሰኝ ሥጋዊ አሳቤ እርሱ ነውና በቁም የሚያቃዠኝ ። ሚስቴን አመንዝራ ፣ ወዳጄን ጉድጓድ ማሽ አድርጎ የሚስልብኝ አእምሮዬን የሚያቆሽሸው ፣ ባልተጨበጠ ነገር የተጨበጠ ጦርነት የሚሰጠኝ ሥጋዊ አሳቤ እርሱ ነው ።በስግብግብነት ከተማውን ካልገዛህ የሚለኝ ፣ አልጠግብ ብዬ ስተፋ የሚያሳድረኝ ፣ የኪስ ጣዖት የሆነውን ገንዘብ የሚያሳየኝ እርሱ ሥጋዊ አሳቤ ነው ። በአሥራት ታማኝ አድርጎ ለድሀ የሚያስጨክነኝ ፣ ሬሳ እየተራመድሁ እንዳልፍ የሚያደርገኝ እርሱ ነው ፤ ሌላ ጊዜም ለድሀ ቸር አድርጎኝ የእግዚአብሔር ሥራ እንዲበደል አሥራቴን የሚያሰርቀኝ ሥጋዊ አሳቤ ነው ፣ ጎዶሎ ጽድቅ ውስጥ የሚያስዋኘኝ ። ከሥጋው ጦመኛ ነኝ ፣ ከመረቁ አውጡልኝ የሚያሰኘኝ ፣ ከወገብ በላይ ታቦት ፣ ከወገብ በታች ጣዖት የሚያደርገኝ ሥጋዊ አሳቤ እርሱ ነው በሁለት ማንነት የሚያኖረኝ ።
ካድሁ እንዳልል በሃይማኖታዊ ፉከራ እየጠመደኝ ፣ ቀጥሎ ሁሉን የሚያስረሳኝ ፣ በስሜት እሳት የሚያሟሙቀኝ ሥጋዊ አሳቤ እርሱ ነው እኔን ለእኔ ያስጠፋኝ ። እያደባ የሚይዘኝ አውሬ ፣ እንደ እባብ ለመንደፍ የሚለሰልሰኝ ጠላቴ እርሱ ሥጋዊ አሳቤ ነው ። ሁሉም ሰው ኀጥእ ነው ብሎ ኃጢአት አሠርቶኝ ፣ ቀጥሎ አንተማ ከእንግዲህ ክርስቲያን አይደለህም የሚለኝ ፣ አሳስቶ የሚከሰኝ ሥጋዊ አሳቤ እርሱ ነው ። የሰይጣን ቆንሲል ሁኖ በውስጥ የሚዋጋኝ ሥጋዊ አሳቤ እርሱ ነው ። እንደ ክፉ ጎረቤት የሚነዘንዘኝ ፣ እንደማይሸጡት ልጅ መላቀቂያ ያሳጣኝ ሥጋዊ አሳቤ እርሱ ነው ። እንደ ባሕር ንውጽውጽታ የማያጣው ሥጋዊ አሳቤ እርሱ ነው ። የዘመኑ ሰማዕትነት ሥጋዊ አሳብን ማሸነፍ ነው ። እባክህ ጌታዬ ሥጋዊ አሳቤን አሸንፌ መንፈሳዊ እንድሆን ፣ የጨለማን አሳብ ጥላቻን ድል ነሥቼ ውሉደ ብርሃን እንድሆን እርዳኝ ። ክፉ ከሆንሁት ከራሴ አድነኝ ። ለዘላለሙ አሜን ።
ሐምሌ 20 ቀን 2011 ዓ.ም.
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ