የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሦስቱ መመሪያዎች

አንድ ሰው አባ እንጦንስን ፡- “እግዚአብሔርን እጅግ በጣም ደስ ማሰኘት የምችለው የትኛውን ግ በመጠበቅ ነው ?” ሲል ጠየቀው ሽማግሌውም እንዲህ ብሎ መለሰለት ፡- “የምነግርህን ጠብቅ ፣ ሁልጊዜ የትም ቦታ ብትሄድ እግዚአብሔር በዓይንህ ፊት ይሁን ። ምንም ነገር ስታደርግ ከቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃ ይኑርህ ። የትም ቦታ ብትኖር ያንን ቦታ ለመልቀቀ አትቸኩል ። እነዚህን ሦስት ግጋት ጠብቅ ትድናለህም ።
አባ እንጦንስ ከዚህ ዓለም ጣዕምና ጫጫታ ተለይቶ በገዳም የኖረ ትልቅ አባት ነው ። “የበረሃው ኮከብ” የሚል የሙገሳ ስም የተሰጠው ለብዙዎችም ምሳሌ የሆነ መነኮስ ነው ። ዓለምን ለማየት ከዓለም መውጣት ግድ ነው ። ከዓለም የምንወጣው በአካል ሳይሆን በልብ ነው ። የእግዚአብሔር ዓላማ ከዓለም መውጣታችን ሳይሆን ዓለም ከልባችን መውጣቷ ነው ። አባ እንጦንስ ይህችን ዓለም የናቀ ትልቅ አባት ነው ። ይልቁንም በእግዚአብሔር ቤት ያለውን የሥልጣንና የገንዘብ ፍጅት የጠላ ፣ ሁሉን ትቶ እግዚአብሔርን መከተል ምን ማለት መሆኑን በሕይወቱ ያሳየ ትልቅ መምህር ነው ። እግዚአብሔር በመንፈሳዊ ተጋድሎና በመንፈስ ቅዱስ ያስተማረው ትልቁ ነገር የእግዚአብሔር ቸርነት የፍጥረት ጥላ መሆኑን ነው ።
አባ እንጦንስ ከመከረው ታላላቅ ምክሮች አንዱ ፡- “ሁልጊዜ የትም ቦታ ብትሄድ እግዚአብሔር በዓይንህ ፊት ይሁን” የሚል ነው ። እግዚአብሔር ደስ ከሚሰኝባቸው ነገሮች አንዱ ነው ። እውነተኛ ቅድስናም እግዚአብሔር እንደሚያየን ሆነን መኖር ነው ። ቅድስና ለእግዚአብሔር ነው ። ቅድስና ማኅበራዊ ከበሬታ ለማግኘት ፣ ዝቅ ብሎ ሌላውን ለመግዛት የሚደረግ ስልት ሳይሆን ቅድስና የዋህነት ነው ። እግዚአብሔር መንፈስ እንደሆነ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል ። እግዚአብሔር በቦታና በጊዜ ያልተወሰነ አምላክ ነው ። ለእርሱ ስንገዛም በቦታና በጊዜ ሳንወሰን ሊሆን ይገባል ። እግዚአብሔርን በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ማምለክ ፣ በመንፈሳዊ ጉባዔዎች ብቻ ማግነን እውነተኛ አይደለም ። እንደውም ቤተ ክርስቲያን መመሪያ መቀበያ ዓለም ደግሞ ትእዛዙን መፈጸሚያ ስፍራ ናት ። ትዕግሥትን ስንማር የሚያበሳጩ ሰዎችን ስለመማረክ እየተማርን ነው ። የቃሉ መተግበሪያ ስፍራ አመፀኛ ሰዎች ናቸው ። ለክፉዎች ደግ ፣ ለስስታሞች ቸር ፣ ለቂመኞች አፍቃሪ በመሆን ልናሳይ ይገባናል ። ክርስትና ከቤተ ከርስቲያን ግቢ አልዘለለም እያልን ብዙ ዘመን ወቅሰን ነበር ። አሁን ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ግቢም እየጠፋ ነው ። ቂም ይዞ ጸሎት ፣ ቅዳሴ አቋርጦ ስድድብ እየሰማን ነው ። አንድ አባት ሲናገሩ ፡- “ድሮ ሐሜት አንድ ቦታ ለመድረስ ቢያንስ ሦስት ቀን ይፈጅበት ነበር ። አሁን ግን እዚያው ቅዳሴ ላይ ቁሞ አባ ቅዳሴውን አበላሹት እያለ ቻት ያደርጋል” ብለዋል ። ሥልጣኔ ክፋትን ማፍጠኛ መሆኑ ያሳዝናል ። የትም አገርና ጠረፍ ብንኖር ከዘመድ እንጂ ከእግዚአብሔር አልራቅንም ። በሁሉ ቦታና በሁሉ ጊዜ እግዚአብሔርን ማየት አለብን ። የተለያዩ ሕዝቦችን ስናይ ፣ የተለያዩ እንስሳትን ስናይ በዚያ ውስጥ እግዚአብሔርን መፈለግ አለብን ። ይህን ሁሉ ወፈ ሰማይ እንዴት ታሳድረዋለህ ? ሳይከብድህ እንደ አንድ ሰው ታኖረዋለህ እያልን ልናሞግሰው ይገባል ። ለሚያዩ ሰዎች እግዚአብሔር የማይታይበት ጊዜና ስፍራ የለም ።
ቃሉም “ሳታቋርጡ ጸልዩ” ይላል ። ቀኑን በሙሉ ሌሊቱን በሙሉ መጸለይ አንችልም ። ለአንድ ድሃ ስንሰጥ እርሱ ስለ እኛ እግዚአብሔርን ማመስገን ይጀምራል ። የጥዋቱ ጸሎት በድሃው ቀጥሏል ። ቢሮአችን ገብተን አንድን ሰው ደስ ስናሰኘው ያ ሰው “ለካ እግዚአብሔር በሁሉ ቦታ ሰው አለው” እያለ ስለ እኛ ሲያመሰግን ጸሎቱ ሙሉ ቀን ሆነ ማለት ነው ። ጸሎት ተግባር ነው ፣ ተግባርም ጸሎት ነው ።
 አባ እንጦንስ የመከረው ሁለተኛው ምክር ምንድነው ? “ምንም ነገር ስታደርግ ከቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃ ይኑርህ ።” ቅዱሳት መጻሕፍት የእምነት መሠረት ፣ የክርክር ሁሉ ማብቂያ ፣ እግዚአብሔርን የምናይባቸው መስተዋት ናቸው ። ቅዱሳት መጻሕፍትን መናፍቃንም አማንያንም ሁሉም ለአሳባቸው ማስረጃ ይጠቅሱአቸዋል ። ነገር ግን በእግዚአብሔር አሳብ መሠረት ቃሉን ማወቅ ይገባል ። ቃሉን ማንበብ ብቻ ሳይሆን በቃል ማጥናትም በጣም ወሳኝ ነው ። መንፈስ ቅዱስ የሚናገረን በተጻፈው ቃል ነውና ቃሉ ከሌለን የመንፈስ ቅዱስን ድምፅና ማጽናናት መስማት እንቸገራለን ። ከምናልፍበት የሕይወት ገጠመኝ ጋር የሚሄደውን ቃል በማስታወስ መንፈስ ቅዱስ ይጠግነናል ። ይህ እንዲሆን የቃሉ ሙላት ያስፈልገናል ። ማንኛውንም ነገር ስናደርግ የቃሉ ማስረጃ ያስፈልጋል ። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚሆነው ቃሉን አክብሮ እንጂ ሽሮ አይደለም ። የእግዚአብሔር ቃል የሚለውን ለመቀበል ፣ የማይለውን ለመጣል ቆራጥነት ያስፈልጋል ። የእግዚአብሔር ቃል የሚከለክለውን ነገር በጸሎት ማቅረብም ተገቢ አይደለም ። የተገለጡ ፈቃዶች ላይ ጸሎት አይቀርብም ። መታዘዝ ብቻ ይገባል እንጂ ። ማንኛውንም ትንሽ የምንለውን ነገር ስናደርግ የቃሉ ማስረጃ ያስፈልገናል ።  ምክንያቱም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚሆነው ቃሉን ባከበርነው መጠን ነውና ። የእግዚአብሔር ቃላትን ብቻ ሳይሆን አሳቡንም መረዳት ያስፈልጋል ። በዚህ ዘመን ቃሉን የማያውቁና ቃሉን የጠመዘዙ ክርስቲያኖች እየበዙ ነው ። ብዙዎችም ሳያነቡ ሳይማሩ የሚያውቁ ይመስላቸዋል ። በእነርሱ አስተሳሰብ እገሌ የሚያስተምረውን ቃል እኔ ማወቅ አያቅተኝም ብለው ነው ። ቃሉን ለማወቅ ግን የራሱ ዲሲፕሊን እንዳለው መዘንጋት የለብንም ።  ይልቁንም ጥልቅ የሆነ የሥላሴና የሥጋዌ መሠረት ያስፈልጋል ። ለዚህ ደግሞ ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን የተሻለ የሚያብራራልን ሊኖር አይችልም ። በዚህ መሠረትነት ቃሉን ስናነብ ይበልጥ መረዳት ይኖረናል ። ማንኛውንም ነገር ስናደርግ የሰዎችን ይሁንታ ሳይሆን የቃሉን ድጋፍ መፈለግ አለብን ። ይልቁንም ያለ ትሕትናና ፍቅር ከምናደርገው ስብከትም ሆነ ደግነት መጠንቀቅ አለብን ። መልካም የሆኑ ነገሮችን ከሚያበላሻቸው አንዱ ያለ ትሕትናና ፍቅር ሲደረጉ ነው ።
አባ እንጦንስ እግዚአብሔርን ደስ ስለማሰኘት የሰጠው ሦስተኛው ምክር አስገራሚ ነው ፡- “የትም ቦታ ብትኖር ያንን ቦታ ለመልቀቀ አትቸኩል ።” ሰይጣንን ከምናሸንፍባቸው ፣ ከፀፀት ከምንድንባቸው መንገዶች አንዱ አጽንዖ በአት ነው ። በስፍራችን መጽናት ወሳኝ ነው ። ሰይጣን ከስፍራችን ሊነቅለን በጣም ይፈልጋል ። ምክንያቱም አንድ ጊዜ ዙረት የጀመረ ሰው ማቆሚያ ስለሌለው ነው ። በእግር የገባ ሰይጣን መቆሚያ የለውም ይላሉ ገዳማውያን። በስፍራችን መጽናት ወሳኝ ነው ። ብዙ ወጣቶች በየጊዜው እዚህ ነበርኩ እያሉ ምስክርነት ሲሰጡ እንሰማለን ። ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ ሲለቁ በጣም ማሰብ ያስፈልጋል ። ሐዋርያው ጳውሎስ አዲሱን ኪዳን ከተቀበለ በኋላ ከፊተኛው እውቀቱ ጋር ለማጣጣም ሦስት ዓመት በዐረብ በረሃ ተቀምጦ አጥንቷል /ገላ. 1፥17/ ። እንዲህ ያለ ጊዜ ሳይወሰድ የሚታወጅ አዋጅ ሳያጸጽት አይቀርም ። ስሜትን ማመን በመጨረሻ ብቸኛ ያደርጋል ። ስሜቱን የሚያምን ሰው የገዛ ማንነቱም ቆይቶ ይከዳዋል ። የትም ብትሄዱ የባሰ እንጂ የተሻለ የለም ። ሰው በጥባጭ ነውና ሰው ባለበት ጥሩ ውኃ አይጠጣም ። በመጽናት ግን ከእግዚአብሔር ዋጋን መቀበል ይቻላል ። አንድ እህት “ባሌን እፈታለሁ” እያለች ስትናገር እናቷ ፡- “ልጄ ታገሺ ጥሩውን ባል ሚስቱም አትለቅልሽም” ብለዋታል ። ክፉውን ፈትቼ ደጉን አገባለሁ ሲባል ያኛውን ደግ ያገኘችዋ እንደማትለቀው እየተናገሩ ነው ። ደግሞም የአለቃ ገብረ ሃና ምክር እዚህ ጋ አስፈላጊ ነው ፡- “እዚያም ቤት እሳት አለ ።” የተገለጠ እሳትና የተዳፈነ እሳት ካልሆነ ሁሉም ቤት እሳት አለ ። ፈረንጅ ጥንቁላ የማያውቅ ንጹሕ መስሎት አንድ ሰው አንድ አባትን ሲጠይቃቸው ፡- “አይ ልጄ ኋይት ማጂክና ብላክ ማጂክ ካልሆነ በቀር ሁሉም አገር ሰይጣን አለ” ብለዋል ። አዎ በቦታችን መጽናት ያስፈልጋል ። አንድ ዛፍ የሚበቅለው በተተከለበት ሲያድግ ነው ። ተነቅሎ ብዙ ቦታ የሚሄድ ከሆነ ይደርቃል ። ተዘዋዋሪ ክርስቲያንም መድረቁ አይቀርም ። ብዙ ቦታ የሚበላ ሰው ሆዱ ጤነኛ አይደለም ። የሃይማኖት ቀላዋጭም መንፈሳዊ ጤንነቱ ጥሩ አይደለም ። ሁለት ቤት ያለው እዚያ ነው ሲባል መንገድ ይቀራል ። እንዲሁም በአንድ እረኛ ሥር ያላደረ ክርስቲያን ፈላጊ ያጣል ። በተበጠበጠ ዘመን ደግሞ ቆም ማለት ጥሩ ነው ። መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እንዳለው፡- “የፈጠረንን እስክናውቅ ባለንበት እንጽና ።” “ከእባብ ጉድጓድ አምልጦ ዘንዶ ጉድጓድ” እንዲሉ ብዙዎች የባሰ ነገር ውስጥ ገብተዋል ። ለዚህ ምልክቱ የኖሩበትን ነገር ሲሳደቡ መስማት ነው ። ያረፈ ሰው አይሳደብም ። ዕረፍቱን አያጣጣመ ይኖራል ። ልክ አይደለህም የሚለውን ኅሊና ለማብረድ ጩኸት ማብዛት የሰው ባሕርይ ነው ። ውስጡ ካልጮኸበት የሚጮኽ የለምና ። “እስከ መጨረሻይቱ ህቅታ ልዩ ሦስትነትህን በማመን አጽናን” እያለች ቤተ ክርስቲያን የምትጸልየው ትልቅ ጸሎት ነው ።
በስፍራችን ያጽናን ።
ተጻፈ በአዲስ አበባ
ዓርብ ግንቦት 9/2010 ዓ.ም.
[1] ከልብህና ከሳብህ አትለየው
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ