የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ
ዓርብ ግንቦት ፰፣ ፳፻፮ ዓ/ም
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፳
ማረጋገጫ የሚፈልጉ
ስምዖን ጴጥሮስ ሁለተኛ የወጣ ሯጭ ቢሆንም መቃብሩ በር ላይ አልቀረም፡፡ ወደ ውስጠኛው ክፍል ዘለቀ፡፡ ጨርቁንም አየ፡፡ አለመኖሩንካረጋገጠ በኋላ ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡ጴጥሮስ ከቃል ማስረጃ የዓይን ማረጋገጫ አገኘ፡፡ በዚህ ረክቶ ተመለሰ፡፡ጴጥሮስ ግን የሠራው የአንድ ፖሊስን ሥራ ሊሆን ይችላል፡፡ መረጃው ትክክል መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ ከዮሐንስ ጋር ተመለሱ፡፡ መግደላዊት ማርያምን ሊያወያያት እንኳ አልፈቀደም፡፡ ዛሬም በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ መንፈሳዊውን ነገር ከመረጃ ባላለፈ ሁኔታ የሚያጠኑ አማንያን ሳይሆኑ ምሁራን አሉ፡፡ ክርስቶስ ተወለደ፣ ተሰቀለ፣ ተነሣ የሚለውን ይቀበላሉ፡፡ ይህ ሁሉ ነገር ግን የእነርሱንልብ አይገዛም፡፡ ስሜታቸውንአይነካም፡፡ ራሱን ለሰጣቸው ጌታ ራሳቸውን እንዲሰጡ አያደርጋቸውም፡፡ ፍቅሩ እንዲማርካቸው አይፈቅዱም፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ የእውቀት እምነት እንዳለ ሲያረጋግጥ፣ይህ እምነት ግን ከአጋንንት እምነት የተለየ እንዳልሆነ ይገልጻል፡፡ «. . . እግዚአብሔር አንድ እንደሆነ አንተ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል፡፡ አንተ ከንቱ ሰው እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን?» ብሏል (ያዕ. 2፡ 19-20)፡፡
ለመዳን የሚፈልጉ
መግደላዊት ማርያም ኢየሱስ ክርስቶስን በብርቱ ትፈልገው ነበር፡፡ እርሱን ካላገኘች ወደ ቤቷ ለመግባት ጠልታ፣ ዱር ቤቴ ብላ ትባዝናለች፡፡ የምትፈልገው «ጌታየ» እያለች እየመሰከረችለት፣ የዕንባ ፈሳሽ እያፈሰሰችለት ነበር፡፡ መላእክት ቢገለጹላትም እርሱን ግን አልተኩላትም፡፡ እርሱን እስክታገኝ ዕረፍት አልነበራትም፡፡ በመጨረሻ አግኝታው በድል ደስታ ተመልሳለች፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስንአውቀውት የሚፈልጉት፡– «አምንህ ዘንድ ራስህን ግለጽልኝ፣ ፍቅርህ ይግዛኝ፣ ህልውናህ ይሰማኝ፣ መዳሰስህ ይፈውሰኝ . . . . » እያሉ በእንባ ይሹታል፡፡ እነዚህ ሰዎች ስለ ዘላለም ሕይወት እርሱን የሚፈልጉት ናቸው፡፡ ስለ አስቤዛ ኑሮ መሟላት ብቻ ክርስቶስንየሚፈልጉትና ስለ ዘላለም ሕይወት እርሱን የሚፈልጉት ሁለት ዓይነት ሰዎች አሉ፡፡ እኛስ ከየትኞቹ ፈላጊዎች እንመደብ ይሆን?
ዮሐንስ ወንጌሉን ሲጽፍ፡– «ስምዖን ጴጥሮስም ተከትሎት መጣ፤ ወደ መቃብሩም ገባ፤ የተልባ እግሩ ልብስ ተቀምጦ አየ፤ ደግሞም በራሱ የነበረውን ጨርቅ ለብቻው በአንድ ሥፍራ ተጠምጥሞ እንደነበረ እንጂ ከተልባ እግሩ ልብስ ጋር ተቀምጦ እንዳልነበረ አየ፡፡» ብሏል (ዮሐ. 20፡ 6-7)፡፡
የጌታችን ቅዱስ ሥጋ ቢሰረቅ ኖሮ ከፈኑ አብሮ ይሄድ ነበረ፡፡ ወይም ተበታትኖ ይቀመጥ ነበር፡፡ ነገር ግን ጴጥሮስ ሲገባ ክብ የነበረው የራሱ ጥምጥም እንኳ አየር እንደተሞላ ከፍታውን ሳይቀንስ ነው ያገኘው፡፡ጌታችን መግነዝ ፍቱልኝ፣ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል ተነሥቷል፡፡ የአይሁድ ካህናት ሞት ያልያዘውን ጠባቂ ይይዘዋል ብለው ማሰባቸው ትልቅ ሞኝነት ነው፡፡ ገደልነው ብለው ለተደሰቱትትንሣኤው፡– «እውነት እንደማይሞት» ገለጠ፡፡ በርግጥም ሞቱ የህልውና ማክተሚያ ሳይሆን የአንድ ታላቅ ሕይወት መነሻ ነበር፡፡ በሞቱ ያዘኑም ላይከፉ ትንሣኤው ደስታን ሰጣቸው፡፡የትንሣኤው ኃይል ሁለት ሺህ ዓመት ተሻግሮ ከኃጢአትና ከሥጋ ፈቃድ በላይ እንድንኖርይረዳናል፡፡
በፍጹም ልብ መሻት
ፍላጎታችን ገደብ የሌለው መሆኑ አንዱ ክፉ ጎን ሲሆን ፍላጎታችንን ለማሟላት ረክሰን ማርከሳችን፤ ሞተን መግደላችን፤ጠፍተን ማጥፋታችን ደግሞ ሌላው አሳዛኝ ጎን ነው፡፡ ከሁሉ የሚያሳዝነውግን ከማይቆጠር ፍላጎታችንውስጥ ጌታችንን አለመፈለጋችንና እንኳን ዋጋ ልንከፍልለት የከፈለልንን ዋጋ አለመረዳታችን ነው፡፡ የሕይወታችንመዘባረቅ ያለው አንደኛን ሁለተኛ ላይ፣ ሁለተኛውን አንደኛ ላይ አድርገን በመኖራችን ነው፡፡
እግዚአብሔር ያልቀደመበትነገር ሁሉ ሰላም የሌለው፣ ዕረፍት የማይሰጥ ነው፡፡ ከሞት የተነሣው ጌታ ለግል ሕይወታችን፣ለስኬታችን ለኅብረታችን፣ . . . ያስፈልገናል፡፡
ክርስቶስ የሌለበት ሕይወት መዓዛ የለውም፡፡
ክርስቶስ የሌለበት ኅብረት ሕይወት የለውም፡፡
ክርስቶስ የሌለበት ምኞት ዕረፍት የለውም፡፡
ክርስቶስ የሌለበት ሥልጣን ነጻነት የለውም፡፡
ክርስቶስ የሌለበት ተግባር ፍጻሜ የለውም፡፡
ክርስቶስ የሌለበት እውቀት ማስተዋል የለውም፡፡
ክርስቶስ የሌለበት ጥበብ ቅድስና የለውም፡፡
ክርስቶስ የሌለበት ኃይል እርዳታ የለውም፡፡
ክርስቶስ የሌለበት ልግስና ደስታ የለውም፡፡
ክርስቶስ የሌለበት ስኬት እርካታ የለውም፡፡
ክርስቶስ የሌለበት ዝና ሰላም የለውም፡፡
ክርስቶስ የሌለበት አገር ዋስትና የለውም፡፡
ክርስቶስ የሌለበት ዳኝነት ፍትሕ የለውም፡፡
ክርስቶስ የሌለበት ምክክር አንድነት የለውም፡፡
እርሱ የሌለበት መልካም ነገር እንኳ በራሱ መልካምነትና ደስታ የለውም፡፡ ስለዚህ እርሱን መፈለግ የእያንዳንዷ ነፍስ ጥማት ነው፡፡ እርሱን መፈለግ ትልቅ ጥበብ፣ ክርስቶስንም ማግኘት ትልቅ ድል ነው፡፡
መግደላዊት ማርያም ኢየሱስ ክርስቶስን የፈለገችውበብርቱ ነው፡፡ የእርሱ የቅርብ ደቀ መዛሙርት እንኳ ፍለጋቸውን አቋርጠው ወደ ቤታቸው ቢመለሱም እርሷ ግን ተስፋ ቆርጣ አልተመለሰችም፡፡ በልቧ ከጴጥሮስና ከዮሐንስ እኔ ለእርሱ ቅርብ አይደለሁም፡፡ እቤቴ ቁጭ ብዬ የሆነውን እሰማለሁ አላለችም፡፡ ከአምስት ገበያ ከሚያህል ሕዝብ አንድ ፈላጊ ያጣውን ጌታ ብቻዋን መፈለግ ጀመረች፡፡እርሱን በእውነት የሚፈልጉ የዘመናት ፈተናቸው ብቸኝነት ነው፡፡ ትልልቅ የሚባሉ ሰዎችም፣ ብዙ የተማሩ መንፈሳውያን መሪዎችም በሌሉበት ኢየሱስ ክርስቶስን መፈለግ ማስተዋል ነው፡፡ በዙሪያችንያሉ ቤተሰቦቻችን፡– «እናንተ ምንድን ናችሁ? ዋናዎቹ ዝም ብለው ስለ ክርስቶስ ምን ያንገበግባችኋል?» ይሉናል፡፡ በእግዚአብሔር መንግሥት ግን ይገባኛል ለማለት የሚያስፈልገን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት እንደወደደን ማወቅ ብቻ ነው፡፡ ክርስቶስ የሚከብረው በሥልጣን ሳይሆን በሚቃጠል ልብ ነው፡፡ ብቸኝነት ሳይሰማት ክርስቶስንትፈልግ የነበረችው ሴት ጽናቷና ፍቅሯ ዛሬም ይዘልፈናል፡፡ እርሱ የሌለበት የብዙኃን ክምችት በመቃብር ውስጥ እንዳሉ የሙታን ሐውልት ነው፡፡ እርሱን < /span>ወዶ በዱር መኖርም ያለ እርሱ በሞቀ ከተማ ከመኖር ይበልጣል፡፡
ለመሆኑ እንዲህ የምትንገበገበው ለምን ይሆን? ይህች ሴት ሰባት አጋንንት አድረውባት ያሻቸውን ያሰሯትና ያሰቃዩአት ነበር፡፡ ከእነዚህ ሰባት ገዢዎች ሕይወቷን ነጻ ያወጣ፣ የኑሮን ጣዕም ያስጀመራትየእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው (ሉቃ 8፡2)፡፡ በአንድ ወቅት ስለ ሰባት ሰይጣናዊ ገዢዎች የወጣ መጽሐፍን አስታውሳለሁ፡፡ እነዚህ ገዢዎች የገደሉትን የሰው መጠን መተንተን አይቻልም፤ የማሰቃያ ዘዴአቸውም አልፈው እንኳ ሲወራ ይዘገንናል፡፡ ግን ሰዎች ናቸው፡፡ የሰው ጨካኝ ገዥ ጭካኔው ተተንትኖ የማያልቅ ከሆነ ያውም ሰባት ገዢዎች፤ ያውም የአጋንንት ባለሥልጣኖችበአንድ ሰው ላይ ሲያድሩ መከራው ጥልቅ ነው፡፡ መላው ኡጋንዳ አንድ ኢዲ አሚንን አልቻለችውም ነበር፡፡ አንድ መግደላዊት ማርያም ግን ሰባት አጋንንት አድረውባትትሰቃይ ነበር፡፡ ከእነዚህ ጨካኝ፣ ርኵሳንና ምሕረት የለሽ ገዢዎች አላቅቆ በፍቅርና በይቅርታ የገዛት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በእውነት ያደረገችው ሁሉ ካደረገላት ጋር ለንጽጽር እንኳ የሚቀርብ አይደለም፡፡ያደረገችው ሁሉ የውለታው መታሰቢያ ቢሆን እንጂ ክፍያ ሊሆን በፍጹም አይችልም፡፡ ይህ ውለታና ያገኘችው ፀጥታ ነው እንቅልፍ የነሣት፡፡እርሱ ሞቶ እን የሰጣት ነጻነት የማይሞት ነበረ፡፡ በቃሉ ትእዛዝ ሥጋዋን በምድር ከሚገዙ አጋንንት ነጻ ያወጣ ጌታ፣ በሞቱ ደግሞ ነፍሷን በሲኦል ከሚገዙ ጨካኞች አድኗል፡፡
ዮሐንስ ሲጽፍ፡– «ማርያም ግን እያለቀሰችከመቃብሩ በስተውጭ ቆማ ነበር» (ዮሐ. 20፡11) ይላል፡፡ አገላለጹ እኛ ሁላችን ወደ ቤታችን ብንሄድም ማርያም ግን በዕንባ ትፈልገው ነበር የሚል ራስን የመውቀስ ነገር ያለበት አጻጻፍ ነው፡፡ ለምንድን ነው? የምታለቅሰው ስንል የሕይወቴ ጌታ ሞተ፤ የነፍሴ አለኝታ ጠፋብኝ ብላ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ነገር ሰው ለሰው ያደርገው ይሆናል፡፡ወዳጆቻችን መቃብር ላይ ብዙ ጊዜ አልቅሰን ይሆናል፡፡ ለሰው ያደረግነውን ያህል ለጌታችን የማድረግ ድካም ግን ሁላችንም አለብን፡፡ መግደላዊትማርያም ግን ይህን አደረገች፡፡ ልቅሶዋ የግፍ ግፍ ደረሰበት የሚል ስሜት ነበረው፡፡ መግደላቸውሳያንስ እንዴት ሥጋውን ያጠፋሉ በማለት ትቆጭ ነበር፡፡ ከየትኛውም ዘመን ይልቅ ዛሬ የሰው ልጆች ያለቅሳሉ፡፡ ልቅሶአቸውግን እንደ መግደላዊትማርያም ኢየሱስ ክርስቶስንለማግኘት አይደለም፡፡
«ስታለቅስም ወደ መቃብር ዝቅ ብላ ተመለከተች፤ሁለት መላእክትም ነጭ ልብስ ለብሰው የኢየሱስ ሥጋ ተኝቶበት በነበረው አንዱ በራስጌ ሌላውም በእግርጌ ተቀምጠው አየች» (ዮሐ. 20፡11-12)፡፡ መላእክቱ ትንሣኤውንለማብሰር መጥተዋል፡፡ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት እንዲነሣ ለመርዳት ግን አልመጡም፡፡ የመጡት ሞት ያልያዘውን ጀግና ሊሰብኩ ነው፡፡ ሰውና መላእክት በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ዙሪያ ምሥጢር ሆኖባቸዋል፡፡ መላእክት ሞቱን መቀበል ይከብዳቸዋል፤ ሰዎች ደግሞ ትንሣኤውን መቀበል ይከብዳቸዋል፡፡ በልደቱና በትንሣኤውመላእክት አልተለዩም፡፡ ልደቱንና ትንሣኤውንየሰበኩት ለሴቶች ነው፡፡ ልደቱን ለእመቤታችንለቅድስት ድንግል ማርያም፤ ትንሣኤውን ለመግደላዊትማርያም ሰብከዋል፡፡
በጌታችን መስቀል አጠገብ ብዙ ሴቶች መራራ ልቅሶ ያለቅሱ ነበር (ዮሐ. 19፡25)፡፡ ትንሣኤው ለሴት መሰበኩ መከራውን የተካፈሉ ደስታውን መካፈል ስለሚገባቸውነው፡፡ ዛሬም የክርስቶስንደስታ ለመካፈል ስለ ስሙ የሚመጣውን መከራ ያለመሰቀቅ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ «አብረንም እንድንከብርአብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን» (ሮሜ. 8፡17)፡፡
መላእክቱም ብርቱ ጥያቄ ጠየቋት፡– «አንቺ ሴት. ስለምን ታለቅሻለሽ?» አሏት (ዮሐ. 20፡13)፡፡ ልቅሶ አንድ ነገር ነው፡፡ ልቅሶ ብቻውን ለትክክለኛነት ማስረጃ አይሆንም፡፡ዕንባ እየፈሰሰም ስለምን እንደሚያለቅሱ የማያውቁ አሉ፡፡ ብዙ አባዮች (ውሸታሞች) እውነት ልትገለጥባቸው ስትል በዕንባቸው ያጨልሟታል፡፡ ዕንባ የእውነት ማኅተም ብቻ ሳይሆን ፍርድን ለማዛባትምውሸታሞች የሚጠቀሙበትነው፡፡ ለእነርሱ ዕንባ እንደ አሽከር ናና ሂድ የሚሉት ነው፡፡ እያለቀስን ከሆነ ስለምን ታለቅሳላችሁ? እንባላለን እንጂ የምትሹትን ጠይቁ ይሆንላችኋልአንባልም፡፡ የምናለቅስበት ጉድለት ሁሉ ትክክለኛ ጉድለት አይደለም፡፡ያለንን ነገር ባለማወቅ የሌለን እየመሰለን ልናለቅስ እንችላለን፡፡ በእርግጥ ስለተቸገርንሳይሆን ትላንት የረዳናቸውሰዎች ስለበለጡንም ልናለቅስ እንችላለን፡፡ ልቅሶአችን ሁሉ ራበኝ ሳይሆን አልረካሁምየሚል ሊሆን ይችላል፡፡ልቅሶአችን ስለተጎዳንሳይሆን ለምን ተነካሁ? የሚል እልህም ሊሆን ይችላል፡፡ አዎ ብዙ አልቃሾች ዛሬም አሉ፡፡ ግን ስለምን ያለቅሳሉ? የኢየሱስ ክርስቶስንፍቅርና ጸጋ ለመጎናጸፍነው?
መግደላዊት ማርያም የምታለቅስበት ምክንያቱ ጸጋን አጣሁ የሚል አልነበረም፡፡ ባለጸጋውን አጣሁት የሚል ነበር፡፡ መልሷም፡-«ጌታዬን ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም አለቻቸው» (ዮሐ. 20፡13)፡፡ አሁንም ጌታዬ አለችው፡፡ ቢሞትም ጌታዋ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚህ በላይ ተሰውሮ መቆየት አልሆነለትም፡፡ እርሱ በእውነት ለሚሹት የቅርብ አምላክ ነውና፡፡ እርሷ አታየውም፣እርሱ ግን ያያታል፤ አልተሰረቀም፣ ሞትን ድል ነሥቶ ተነሥቷል፡፡ እርሱ ከመቃብር ስፍራ አይፈለግም፣ከመሬት በታች የለም፤ ከሰማያት በላይ ገኗል፡፡ ኢየሩሳሌም የገፋችው ዝናው በዓለም ሁሉ ወጥቷል፡፡ለሙታን የሚሆን ሽቱ ሳይሆን ለሕያውነቱ የሚቀርበውንየምሥጋና መሥዋዕት የሚቀበል ነው፡፡ ያ የፍቅር ጌታ የማርያምንሰቀቀን ችሎ መቆየት አልሆነለትም፡፡ በኃይሉ ጉልበት ሁሉን ሲረታ፤ በፍቅር ግን ይሸነፋል፡፡ ስለዚህ ተገለጸላት፡፡ «ይህንንም ብላ ወደኋላ ዘወር ስትል ኢየሱስን ቆሞ አየችው፤ ኢየሱስ እንደሆነ ግን አላወቀችም፡፡ ኢየሱስም፡– አንቺ ሴት ስለምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ?» አላት (ዮሐ. 20፡15)፡፡ የመላእክቱን ጥያቄ ደገመላት፡፡ አንገብጋቢ ጥያቄ ነው፡፡ ማንን ፈልገሽ ታለቅሻለሽ? አላት፡፡ «ማን» ለሕያው የሚጠቀስ ነው፡፡ «ምን» ግን ለቍሳቁስ ፍላጎት የሚጠቀስ ነው፡፡ እኛን ቢሆን፡– «ምን ፈልጋችሁ ታለቅሳላችሁ?» ይለን ነበር፡፡
መግደላዊት ማርያም ግን አላወቀችውም፡፡ «እርሷም የአትክልት ጠባቂ መስሎአት ጌታ ሆይ አንተ ወስደኸው እንደሆንህ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ እኔም እወስደዋለሁ አለችው» (ዮሐ. 20፡15)፡፡ ይህንን ቃል ልጽፍ ስል ኃይሌ ደከመ፤ ሰውነቴ ተሰነጣጠቀ፡፡ ልቤ በቅዱስ ፍርሃት ራደ፡፡ ትንሽ ተከዝኩ፡፡ ዕንባም ፈተነኝ፡፡አምላኬን ጠየቅኹት፡– «ጌታዬ ሆይ– ለማይጠቅምናለማያጠግብ ምክንያት ብዙ ዘመን ኖሬአለሁ፡፡ለፍቅርህ ኃይል ግን ዛሬም አልተሸነፍኩም፡፡ ያንተን ቅዱስ ሥጋ እንኳ ለማክበር ያች ሴት ፈለገችህ፤እኔ ግን ለሕያውነትህእንኳ አልተገዛሁም፡፡ የሚጎዳኝንኃጢአት በመተው እንኳ ልታዘዝህ አልቻልኩም፡፡ ወይኔ ይህን ፍቅር ተቋቁሜ መኖሬ፤ ይህን ታላቅነት ሳላይ መታወሬ? እባክህ ይቅር በለኝ።»
ጌታችን የተቀበረበትስፍራ ውብ የአትክልትስፍራ ነበረ፡፡ በሕይወቱ ራሱን እንኳ የሚያስጠጋበት ደሳሳ ጎጆ አልነበረውም (ማቴ. 8፡20)፡፡ መቃብሩ ግን ከባለጠጎች ጋር ነበረ (ኢሳ. 53፣9፤ዮሐ. 19፣41)፡፡ በቍማቸው አንድ የሚያጽናና ሰው አጥተው፣ በሞታቸው ቀን ግን ሺህ ቀባሪ የሚያገኙ ብዙዎች ናቸው፡፡ በቍማቸው አንድ ዳቦ አጥተው በረሀብ ሞተው፣ የቀብራቸውቀን ግን በሬ የሚታረድላቸው የማይቆጠሩ ናቸው፡፡ በቍማቸው ጣራ እያፈሰሰባቸው የሞቱ ቀን ሊሾ የሚደረግላቸው እልፍ ናቸው፡፡ በስቃይ ኖረው በክብር ለሚቀበሩት መከረኞች ኢየሱስ ክርስቶስ መከራቸውንቀመሰላቸው፡፡ የከበረ ቀብር እንጂ የከበረ ኑሮ የሌላትን የዓለምን መከራ ጌታችን አየልን፡፡በእውነት ወገኖቻችንንታመው ለመጠየቅ የማይመቸን፣ሲሞቱ ግን ለቀብር የሚመቸን፤ በረሀብ ሲወዘወዙ ግድ ሳይለን፣ ሲሞቱ ግን ጌጠኛ የሬሣ ሳጥን የምንገዛ፤ በቍማቸው ሸሽተናቸው ሲሞቱ ግን ሬሣቸውን የምናጅብ፣ በጨለማ ተምረንባቸው በአደባባይ የምንቀብር፤ገድለን ሞቱ ብለን የምናውጅ ዓለም እኛ ነን፡፡ ይህ ሁሉ ተግባራችን በክብሩ በተቀመጠውጌታ እንደ መዘበት ነውና ንስሓ እንግባ።
— ይቀጥላል—
ረቡኒ
በዲ/ን አሸናፊ መኰንን
የመጀመሪያ እትም ሚያዝያ 2002 ዓ/ም
አድራሻ – 0911 39 35 21/0911 67 82 51
ፖ.ሳ.ቁ. 62552
አ.አ. ኢትዮጵያ