የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ረቡኒ መጽሐፍ – እናከብረዋለን

የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ                    ሰኞ  ግንቦት ፳፭ ፣ ፳፻፮ ዓ/ም
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፳
                                         ረቡኒ
ለእኛስ ኢየሱስ ክርስቶስ መምህራችን ነው? እርሱን መምህር ካደረግነው፡-
እናከብረዋለን
ማክበር ከቃል ያለፈ በተግባር የሚገለጥ ነው፡፡ ማክበር አንገትን ዝቅ ከማድረግ ከአንቱታም የረቀቀ ነው፡፡ ማክበር ሕይወትን መስጠት ነው፡፡ እርሱ ራሱ በቃሉ፡- «ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል. ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል» (ማቴ. 15፣7-9) ብሏል፡፡ አክብሮት ከአፍ የሚያልፍ የልብ ታማኝነት ነው፡፡ አክብሮት ከውጫዊ ሥርዓት ያለፈ እውነተኛ መገዛት ነው፡፡ አክብሮት ከታይታ የዘለቀ ላከበርነው መኖር ነው፡፡ እኛስ እናከብረዋለን? የምንሰማው ምንድነው? ኃጢአት በሞተበት ቀን ኃጢአት ሲነግሥ አይደለምን? «የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ በዓል ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ ታላቅ የሙዚቃ ድግስ» እየተባለ ሲነገር ማዘን ማልቀስ ይገባን ነበር፡፡ እርሱ ስለ ኃጢአታችን ሞቶ በኃጢአት ልናከብረው መነሣታችን፣ በእርሱ ስም ሰይጣንን ማንገሣችን፣ በምን እንደምናከብረው አለማወቃችንን ያሳያል፡፡
ከነድካማችን እንቀርበዋለን
ብዙ ሰዎች ወደ ክርስቶስ መምጣት የሚፈልጉት ራሳቸውን ለውጠው፣ መልካም ሰዎች ሆነው ነው፡፡ «እንደዚህ ሆኜማ እርሱን ማምለክ አልፈልግም፡፡ ራሴን በደንብ አሻሽዬ በእውነት ላመልከው እፈልጋለሁ» ይላሉ፡፡ ነገር ግን ሰው ራሱን መለወጥ ቢችል ኖሮ ኢየሱስ ክርስቶስ ከኃጢአት የሚያድን ሆኖ ወደ ዓለም መምጣት ባላስፈለገው ነበር፡፡ ሰው ራሱን መለወጥ ቢችል ለራሱ አዳኝ (አምላክ) በሆነ ነበር፡፡ የሚለውጠን ግን ራሱ ጌታ ነው፡፡ ስለዚህ ወደ እርሱ ከነሸክማችን እንድንመጣ ጋብዞናል (ማቴ. 11፡28)፡፡ «ማንነቴ፣ ያልተቀባባ መልኬ ይህ ነው፤ ጌታዬ ተቀበለኝ፤ ማንነቴን ጥለህ ማንነትህን አልብሰኝ፡፡ እኔ ራሴን መለወጥ አልቻልኩም አንተ ለውጠኝ» ብለን ወደ እርሱ መምጣት ያስፈልገናል፡፡ እርሱ ራሱ በቃሉ የእኛንና የእርሱን ግንኙነት በግንድና በቅርንጫፍ መስሎ፣ ቅርንጫፍ ሊያፈራ የሚችለው በግንዱ ላይ እስካለ ብቻ እንጂ በራሱ ማፍራት እንደማይችል ከገለፀ በኋላ፡- «ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ. እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል» (ዮሐ. 15፡5) ብሏል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስን መምህር ስናደርግ አዝነን እንዳላዘነ፣ ደክመን እንደበረታ ሆነን አንቀርበውም፡፡ የእኛ ጉዳይ ይገደዋልና ድካማችን አይገርመውምና በፍቅር ድፍረት እንቀርበዋለን፤ (ዕብ. 4፣14-16)፡፡ የተበላሸ ዕቃን ለባለሙያ ስንሰጠው «ጠግነህ ተጠቀምበት፣ እኔ ጋ ግን አይጠቅመኝም» ብለን ነው፡፡ ለባለሙያው ክርስቶስም ማንነቴን ጠግነህ ተጠቀምበት ብለን እንሰጠዋለን፡፡ «በሸክላ ሠሪ እጅ ያለ ሸክላ ቢበላሽ በእጁ ነውና እንደገና ተሠርቶ ለመሟሸት ዕድል ያገኛል፡፡ እኔም በእጅህ የተበላሸው ሸክላ ነኝና እንደገና ሥራኝ፡፡ ለክብርህ ቀን የማልቆም ሰባራ ነኝና እንደገና ሥራኝ» ልንለው ይገባል (ኤር. 18፡1-6)፡፡
በእምነት እንከተለዋለን

ሕጻን ልጅ ወላጆቹን የሚከተለው «ወዴት» ሳይል ነው፡፡ የወላጆቹ መድረሻ ሁሉ ለእርሱ ጠቃሚው መሆኑን አይጠራጠርም፡፡ ጻድቃን እግዚአብሔርን የተከተሉት እንደ ሕጻን ባለ እምነት ነው፡፡ አብርሃም፡- «እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ» (ዘፍ 12፣1) ሲለው የምድሪቱን አድራሻ፣ መልክአ ምድሩን፣ የአየሩን ጠባይ፣ የሚያገኘውን ነገር አልተደራደረም፡፡ ሰባ አምስት ዓመት ከኖረበት የካራን ምድር በእምነት ወጣ፡፡ ወዳየው ምድር ሳይሆን ወደታየለት ምድር ወጣ፡፡ እግዚአብሔር ሲያዘው ውጤቱ ምን ይሆን? ብሎ አልተጨነቀም፡፡ የተጨነቀው ለመታዘዝ ነው፡፡ እምነት ማለትም ውጤቱ ምን መሆኑ ሳያሳስበን ለእግዚአብሔር መታዘዝ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስንም መምህር ስናደርግ ወደሚመራን መንገድ ሁሉ እንከተለዋለን፡፡
ጊዜአችንን እንሰጠዋለን
ተማሪ ከወላጆቹ ጋር ከሚያሳልፈው ጥርት ያለ ጊዜ ከመምህሩ ጋር የሚያሳልፈው ይበልጣል፡፡ ለመምህሩ ማንም የማይጋራው ጊዜ አለው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን መምህር ስናደርግም በአጋጣሚ ሳይሆን በተቆረጠ ጊዜ እናገኘዋለን፡፡ ለእርሱ የመደብነው ጊዜ «የንጉሥ ቀጠሮ» በመሆኑ ለማንም አንሰጠውም፡፡ ለእግዚአብሔር ሕይወታችንን፣ ጊዜአችንን፣ ገንዘባችንን መስጠት ይገባናል፡፡ እነዚህ ነገሮች ተራቸውን መልቀቅ የለባቸውም፡፡ ከሁሉ በፊት ሕይወታችንን መስጠት ይገባል፤ ከዚያ በኋላ ጊዜአችንንና ገንዘባችንን መስጠት ይገባናል፡፡ በምንም መንገድ አንዱ የአንዱ ምትክ መሆን አይችልም፡፡ ገንዘብ የአገልግሎት፣ አገልግሎትም የሕይወት ምትክ መሆን አይችልም፡፡ ብዙዎች ጊዜአቸውን መስጠት አይፈልጉም፣ ስለዚህ ገንዘባቸውን በሩቅ ሆነው ይጥላሉ፡፡ ሌሎችም ጊዜአቸውን ሰጥተው ቢያገለግሉም ሕይወታቸውን ግን አልሰጡም፡፡
አገልግሎት የምንለው ጊዜን ለእግዚአብሔር መስጠትን ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን መምህር ስናደርገው ጊዜአችንን እንሠዋለታለን፡፡ ክርስቶስ ዛሬ የሚከብረው በሰማዕትነት ሳይሆን ጊዜን በመስጠት ነው፡፡ እርሱ የሞታችንን መሥዋዕትነት ከመቀበል ዕለት ዕለት ሕያው ማንነታችንን መሥዋዕት እንድናደርግለት ይፈልጋል፡፡ ጳውሎስ ሐዋርያ፡- «እንግዲህ. ወንድሞች ሆይ. ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርህራኄ እለምናችኋለሁ. እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው» (ሮሜ 12፣1) ብሏል፡፡
ተግሣጹን እናከብራለን
የሚመክር፣ የሚገስጽ፣ የሚቀጣ የእኛን መልካምነት ከእኛ ይልቅ የሚጠማ ነው፡፡ ልጅነትና የልጅነት አስተሳሰብ ተግሳጽን ይጠላል፡፡ ተግሳጽ ግን ያቀናል፡፡ ወደ ጉድጓድ እንዳንገባ ወይም ገብተን እንዳንቀር ዓይንን ያበራል፡፡ በዚህ ዓለም ላይ በሥልጣን ከሚገስጹ አካላት ከወላጆች ቀጥለው መምህራን ናቸው፡፡ እኛ ያልታየንን መምህሩ ይታየዋልና ተግሳጹን በደስታ እንቀበላለን፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ መምህር ስናምነው ተግሣጹን በደስታ እንቀበላለን፡፡ እርሱ ያስተምራል ከዚያም አልፎ ይገሥጻል፡፡ ተግሣጹን አልቀበል ስንልም በሥልጣን ይቀጣናል፡፡ ይህ መምህርነቱ ሲገባን፡- «ጌታ ሆይ፣ ለፍላጎቴ አትተወኝ፣ እምቢ ብልህ እንኳ ቀጥተህ መልሰኝ» እንለዋለን፡፡ ቅጣት ለልጅነት አስተሳሰብ ያስመርራል፣ ካደግን በኋላ ግን ራሳችንን ለምናገኝበት መልካም ምርጫ ቅጣቱን እናወድሳለን፡፡ ብዙ ጊዜ፡- «ያኔ ወላጆቼ ጨክነው ባይቀጡኝ ኖሮ ለዚህ አልበቃም ነበር፣ ጠፍቼም እቀር ነበር» የምንለው ቅጣት ለማደግ አስፈላጊ መሆኑ ስለገባን ነው፡፡
         
የዕብራውያን መልዕክት ጸሐፊ፡- «ልጄ ሆይ. የጌታን ቅጣት አታቅልል. በሚገስጽህም ጊዜ አትድከም፤ ጌታ የሚወደውን ይቀጣዋልና. የሚቀበለውንም ልጅ ሁሉ ይገርፈዋል» (፺ዕብ. 12፡5-11) ብሏል፡፡
ማደግን እንፈልጋለን
         
ክርስትና እንደ ኩሬ ውሃ የረጋ ሳይሆን እንደ ወንዝ ፈሳሽ ግለቱን የሚጨምር ነው፡፡ ክርስትና ሕይወት ነው፡፡ በሕይወት ውስጥም የማያቋርጥ ዕድገት አለ፡፡ በክርስትናችን በጸጋ፣ በአገልግሎት፣ በቅድስና፣ በእምነት እናድጋለን፡፡ ማደግ የምንለው እንደ ሥራ ዕድገት የደረጃ ከፍታን የሚያመለክት ሳይሆን ለተሰጠንበት ዓላማ ራሳችንን ዕለት ዕለት መስጠት፣ በጥራትና በብዛት መገለጥ ነው፡፡ ለዕድገት ከሚረዱ ወገኖች የመጀመሪያው መምህር ነው፡፡ ከእኛ ደግሞ የሚጠበቀው ፍላጎት ነው፡፡ ጌታችንን እንደ መምህራችን ስናየው እንዲያሳድገን እንለምነዋለን፡፡ እርሱ የመጠማት አምላክ ነው፡፡ እኛን በጸጋ ከማርካቱ በፊቱ ብርቱ ናፍቆታችንን ማየት ይፈልጋል፡፡ ራሱ በልዑል ቃል፡- «ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ፡፡ በእኔ የሚያምን. መጽሐፍ እንዳለ. የሕይወት ውሃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል»  (ዮሐ. 7፣37-38) ብሏል፡፡
በፍቅር እንፈራዋለን
ፍርሃት ብቻ አያቀርብም፣ ፍቅር ብቻም ታማኝ አያደርግም፡ እውነተኛ ፍቅር ግን ቅዱስ ፍርሃትና ቅዱስ መሰሰት አለው፡፡ ፍቅር የወደደውን ያን ወዳጁን ማጣት አይፈልግም፡፡ ቅዱስ ፍርሃትና መሰሰት አለው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ መምህራችን ስናየው በቅዱስ ፍርሃት እንፈራዋለን፡፡ እርሱን ላለማሳዘን እንጠነቀቃለን፡፡ ከሕግ ይልቅ ፍቅር ቅዱስ ያደርገናል (ሮሜ. 13፣8-10)፡፡
በፊቱ እንራቆታለን
ተማሪው መምህሩን ባለማወቄ አይታዘበኝም ብሎ ያምነዋል፡፡ መምህሩም እንደ አባት ሲቀርበው ማንነቱን ሁሉ ያጫውተዋል፡፡ ይወደዋል እንጂ አያፍረውም፡፡ ፍቅር ለሚወደው ይራቆታልና፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም ረቡኒያችን ሲሆን ሳናፍረው ራሳችንን እንገልጽለታለን፡፡ ማንነታችንን፣ ድካማችንን፣ ነውራችንን፣ ሰው ቢሰማው የማይሸከመውን ጉዳችንን ሁሉ እናጫውተዋለን፡፡ በአደባባይ የጥንካሬ ተምሳሌት ሆነን ብንጠቀስም ራሳችንን የምናውቅበት እውቀት ግን ድካማችን ነው፡፡ ያንን እንዲያውቅ የምንፈቅደው ለክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ እርሱ አይመለከተውም የምንለው የሕይወት ክፍል አይኖረንም፡፡ በሁሉም ነገራችን ሰሚ ብቻ ሳይሆን ወሳኝ ጌ ችን ነው፡፡ ይህን ሁሉ ግን ማድረግ የምንችለው እርሱን እንደ መግደላዊት ማርያም «ረቡኒ» ስንለው ብቻ ነው፡፡
እንከተለዋለን
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአዋቂዎች አዋቂ፣ ጥበቡ የማይደረስበት፣ ተግባሩ የማይኮረጅ ልዩ አምላክ ነው፡፡ እርሱ እኛ የማንችለውን የትላንትን ስህተት ማስተካከል የሚችል፣ እኛ የማናውቀውን ነገን የሚያይልን አምላክ ነው፡፡ እርሱ ከከለከለን ነገር ውስጥ ደግ ነገር መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡ እርሱ ካዘዘን ነገር ውስጥ ለጊዜው ድሉ ባይታይም ዋስትናችን ግን የተጠበቀ፣ ፍጻሜውም የሚያምር ነው፡፡ እርሱን እንደ መምህር ስናየው በሚመራን መንገድ እንከተለዋለን እንጂ አንሟገተውም፡፡
የእውቀታችን ማረጋገጫ እናደርገዋለን
እውቀት እርግጠኛ የሚሆነው መምህሩ ሲያረጋግጠው ነው፡፡ እርግጠኛ ያልሆነ እውቀት ድፍረት አይሰጥም፡፡ ለሌሎች ቢያስተላልፉትም አደጋ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ የእውቀት ማረጋገጫው መምህሩ ነው፡፡ መምህሩ ይፈትናል፣ ውጤት ይሰጣል፣ ይጥላል፣ ያሳልፋል፣ ያስደግማል፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ዕድገትን ብቻ ለሚፈልግ ማወቅን ግን ለማይፈልግ ተማሪ አይጥሙም፡፡ በእውቀት ማደግ ግን ከባዶ ዕድገት የተሻለ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን መምህራችን ስናደርግ ገንዘባችንን፣ እውቀታችንን ከእርሱ ቃልና ፈቃድ አንጻር እናስተዳድራለን፡፡ እርሱ የሌለበትን ነገር ሁሉ እንደ ሬሳ ሸክም እንቆጥረዋለን፡፡ ምሪቱን እየጠየቅን፣ ሁሉም ነገር እንደ ቃሉ መሆኑን እያረጋገጥን እንጓዛለን፡፡ ይህ በሕይወት ላይ ትልቅ ድፍረትን ሲሰጠን፣ ለሌሎችም በረከት እንድንሆን ያደርገናል፡፡
ደስታው ደስታችን ነው
ማወቃችንና ጥሩ ውጤታችን ከማንም ይልቅ መምህሩን ያስደስተዋል፡፡ የመምህሩን ደስታ ስናይ እኛም በደስታ እንፈነጥዛለን፡፡ ደስታው ደስታችን ይሆናል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ መምህራችን ሲሆን «ረቡኒ» ስንለው ደስታው ደስታችን ይሆናል፡፡ ደስታውም ኃይላችን ይሆናል፡፡
ለእኛስ «ረቡኒ» ነው?
እውነተኛው መምህር እርሱ ነው፡፡ እርሱ ራሱ በቃሉ፡- «እናንተ ግን፡- መምህር ተብላችሁ አትጠሩ፤ መምህራችሁ አንድ ስለሆነ እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ፡፡ አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም፡- አባት ብላችሁ አትጥሩ፡፡ ሊቃችሁ አንድ እርሱም ክርስቶስ ነውና፡- ሊቃውንት ተብላችሁ አትጠሩ» (ማቴ. 23፡8-10) ብሏል፡፡
መግደላዊት ማርያም በስሟ ሲጠራት አወቀችው፡፡ በዚህ ቅላጼ፤ በዚህ የፍቅር ቃና ከእርሱ በቀር ማንም እንደማይጠራት አውቃ «ረቡኒ» አለችው፡፡ የእርሱ አጠራሩ፣ አሰጣጡ… የተለየ ነው፡፡ በስማችን የሚያውቀን ንጉሣችን እርሱ ብቻ ነው፡፡ የዚህ ዓለም ነገሥታት ሕዝባቸውን በጅምላ ቍጥር ያውቁታል፡፡ በስም ግን ለይተው አያውቁትም፡፡ እርሱ ግን እያንዳንዳችንን በስማችን ይጠራናል (ኢሳ. 43፡1)፡፡ ጌትነቱ፣ መምህርነቱ፣ ንጉሥነቱ ሁሉ ልብ ያሳርፋል፡፡
ክብር ምስጋና ለእርሱ ይሁን፤ አሜን፡፡
                       — ይቀጥላል—
ረቡኒ
በዲ/ን አሸናፊ መኰንን
የመጀመሪያ እትም ሚያዝያ 2002 ዓ/ም
አድራሻ – 0911 39 35 21/0911 67 82 51
ፖ.ሳ.ቁ. 62552
አ.አ. ኢትዮጵያ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ