የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ ቅዳሜ ግንቦት ፴ ፣ ፳፻፮ ዓ/ም
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፳
የማይሰናበቱት ጌታ
መግደላዊት ማርያም በብዙ ዕንባ ያገኘችውን ጌታ አሁንም ሳትጠግበው፣ ፍቅሯንም ሳትገልጥለት የሚለያት መሰላት፡፡ ለሞቱ ያመጣችው ሽቱ ለሕያውነቱ ስለማይመጥን የሙታንን መሥዋዕት ጣለችና በሕይወቷ ልታከብረው በህልውናው ፊት ቆመች፡፡ ለሕያውነቱ የሚገባውን የድል ነሺነቱንም ምስጋና ከስግደት ጋር ለማቅረብ ስታስብ፣ ከስግደቷ ጋር ልትሰናበተው ፈለገች፡፡ እርሱ ግን የተነሣው እንደ አልዓዛር እንደገና ሊሞት ሳይሆን በትንሣኤው ብርሃን እንደ ገነነ ሊኖር ነው፡፡ እርሱን ከሞቱ በፊት በአካል ታገኘው ነበር፡፡ አሁን ግን በመንፈስ ታገኘዋለች፡፡ እርሱ ከምድር እስከ ሰማይ ምሉዕ ነው፡፡ ከሞቱ በፊት የድካምና የመስቀል ሰው ሆኖ ይታይ ነበር፡፡ ከትንሣኤው በኋላ ግን ክብርና መስቀሉ ጎልተው ይታያሉ፡፡ ከሁሉ በላይ እርሱ የማይሰናበቱት ጌታ ነው፡፡ ማንንም ተሰናብቶ የማያውቅ ዘላለማዊ አፍቃሪ ነው፡፡ ለመሰናበትም የሚመጡትን የማይቀበል ነው፡፡
ዮሐንስ ወንጌሉን ሲጽፍ፡- «ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ» እንዳላት ዘግቦልናል (ዮሐ 20፣17)፡፡ የትንሣኤው ብርሃን አይጨልምም፡፡ የትንሣኤው ብርታት አይደክምም፡፡ ትንሣኤው ዕርገት የሚከተለው መሆኑን ገለጸላትና ስንብቷን አልተቀበለም፡፡ ሩቅ አገር ለሚሄዱ ሰዎች፣ አሊያም ለሞቱ ሰዎች የሚደረገው ዓይነት ስንብትን ጌታ አይቀበልም፡፡ ትንሣኤ ወደ ሞት ሳይሆን ወደ ዕርገት የሚቀየር ነው፡፡ በኢየሩሳሌም የሞተው ክርስቶስ፣ የዓለም ጌታ ሆኖ የሚሰበክበት ጊዜ ደርሷል፡፡ በእርሱ ግዛት ፀሐይ አይጠልቅምና ማንም እንዲሰናበተው አያስፈልገውም፡፡ በኢየሩሳሌም የነበረው አሁን ደግሞ በልባችን ይኖራል፡፡ በማይታየው አገር ሆኖ የሚታየውን ዓለም ይገዛል፡፡ በመንፈሱም ፍጥረትን ይጎበኛል፡፡ እውነት እንድታበራ ያደርጋል፡፡ ፍትሕን ለተጠሙ ብይን ይሰጣል፡፡ ሰላም ለራቃቸው ሰላምን ያስጎነጫል፡፡ እርሱ ማንንም ተሰናብቶ አያውቅም፡፡ ትተውት ለመሄድም አይቻልም፡፡ የማይገኝ ልዑል ነውና፡፡ አባ ሕርያቆስ እንዳወደሰው፡-
«የማይደፈር ግሩም ነው፤ በእኛ ዘንድ ግን ትሑት ነው፡፡ የማይገኝ ልዑል ነው በኛ ዘንድ ግን አርአያ ገብርን ነሣ፡፡ የማይዳሰስ እሳት ነው፤ እኛ ግን አየነው ዳሰስነውም፤ ከእርሱም ጋራ በላን ጠጣን»
/ቅዳሴ ማርያም ቍጥር 88/፡፡
ወንድሞቼ
በመቀጠልም ጌታችን፡- «ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ፡- እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዐርጋለሁ ብለሽ ንገሪያቸው አላት» (ዮሐ. 20፣17)፡፡ ደቀ መዛሙርቱን «ወንድሞቼ» አላቸው፡፡ ከሞቱ በፊት «ወንድሞቼ» ብሎ ተናግሮ አያውቅም፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የተናገረው አሁን ከትንሣኤው በኋላ ነው፡፡ እርሱ በመስቀል ላይ የሞተው ያጣነውን ልጅነት መልሶ ወደ አባቱ መንግሥት ሊያስገባን ነው፡፡ መሥዋዕትነቱ ሰምሮ እግዚአብሔር አብ እንደ ልጆች ተቀብሎናልና «ወንድሞቼ» በማለት ተናገረ፡፡ የዕብራውያን መልእክት ፀሐፊም፡- «ወንድሞቼ ብሎ ሊጠራቸው አያፍርም» (ዕብ. 2፣13) በማለት መናገሩ ለዚህ ነው፡፡ እርሱ እንኳ በእኛ ካላፈረ እኛ እንዴት በእርሱ እናፍራለን?
በመቀጠልም ጌታ፡- «እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዐርጋለሁ ብለሽ ንገሪያቸው አላት» (ዮሐ 20፣17)፡፡ ይህ አገላለጽ መለኮትና ሰውነት በአንድ በክርስቶስ አካል ተዋህደው እንዳሉ ለዘላለምም እንደሚኖሩ የሚገልጽ ነው፡፡ ከሞቱ በፊት ሰውና አምላክ ሆኖ በተዋህዶ እንደተገለጠ፣ ከሞቱ በኋላም ሰውና አምላክ ሆኖ በዘላለማዊ ተዋህዶ ይኖራል፡፡ እርሱ ወደ ምድር ሲመጣ የሥላሴ አካል ወደ ሁለትነት አልጎደለም፡፡ ወደ ሰማይ ሲያርግም የሥላሴ አካል ወደ አራትነት አይጨመርም፡፡ ምንታዌ (ሁለትነት) ና ርባዔ (አራትነት) በሌለው ሁኔታ ሥላሴነት ለዘላለም ይኖራል፡፡
«አባቴ» ሲል እግዚአብሔር አብ ለእርሱ የባሕርይ አባቱ ነው፡፡ ለእኛ ግን የጸጋ አባት ነው፡፡ ስለዚህ የእርሱ ልጅነት የተለየ ነውና ለይቶ አባቴ አለ (ዮሐ. 5፣18)፡፡ አባቴ በማለቱም ከአብ ጋር የአንዱን መለኮት ክብር ተካፋይ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ከትንሣኤው በኋላም ያለው አምላክነቱ ብቻ ነው፣ ሰውነቱን ትቶ ተነሥቷል እንዳንል «አምላኬ» አለ፡፡ የለበሰውን ሥጋ አብ ይፈጥረዋልና፡፡ ራሱ ወልድም ለለበሰው ሥጋ አምላክ ነውና «አምላኬ» አለ፡፡ የክርስቶስ ተዋሕዶ ዘላለማዊ ነው፡፡ ሰውነትና አምላክነት በአንዱ የክርስቶስ አካል ዘላለማዊ ሆነው መኖራቸው እኛም ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ኅብረት ዘላለማዊ መሆኑን ያበስራል፡፡
ዮሐንስ ዘገባውን ሲያስር፡- «መግደላዊት ማርያም መጥታ ጌታን እንዳየች ይህንም እንዳላት ለደቀ መዛሙርቱ ነገረች» (ዮሐ 20፣18) ይላል፡፡ ወደፊት ትንሣኤውን የሚሰብኩ የትንሣኤው ሰባክያን አሁን በአንዲት ታሪኳ በክርስቶስ በተለወጠላት ሴት ተሰበኩ፡፡ ተሰብከው ሊሰብኩ ቢወጡ ሺህውን በአንድ ቀን ማረኩ፡፡ እኛስ ተሰብከን ለመስበክ ወጥተን ይሆን? ምንም ታናሽ ብንሆን የደከሙ ደቀ መዛሙርትን «አገልጋዮችን» ለመቀስቀስ አስበን ይሆን? ክርስቶስ ተነሣ ብለን ለመመስከር ዝግጁ ነን? ለመግደላዊት ማርያም እንዳደረገው ለእኛም ባለውለታችን ነው? ላለፈው ዘመን ድካማችን፤ ይህን ታላቅ ፍቅር ላለማየት ዓይናችንን ለጨፈንበት ዘመን አሁን ንስሐ ገብተንበት ለተነሣው ጌታ ምስክር እንሁን፡፡ ጸጋው ያግዘን፤ አሜን፡፡
ማጠቃለያ
ብዙ ጊዜ ከልባችን እየተማረርን የምንናገረው ነገር አለ፡- «እኔ እንደ ሰዉ ትልቅ ወይም ብዙ ነገር አይደለም የምፈልገው፡፡ ነገር ግን የሚያስፈልገኝና የሚበቃኝን ትንሽ ነገር ነው የምፈልገው፡፡ ግን እርሱም የለኝም» እንላለን፡፡ መግደላዊት ማርያም ብዙ ነገር አልፈለገችም፡፡ የጌታችን የኢየሱስን ቅዱስ ሥጋ አግኝታ መሰናበት ብቻ ነው የፈለገችው፡፡ እርሱንም ባጣች ጊዜ ትልቅ የልብ ስብራት ደረሰባት፡፡ በመጽናቷ ግን የኢየሱስን ሥጋ ሳይሆን በሕያውነቱና በትንሣኤ አካል አገኘችው፡፡ ትንሽ ነገር ፈልገን ያጣን ሲመስለን የበለጠ ነገር እንድናይ የእግዚአብሔር ፈቃዱ ነውና ደስ ሊለን ይገባል፡፡ ያልተመኘነውን ሕያውነት፣ ያልጠበቅነውን ዘላለማዊነት እናገኛለን፡፡ ግን ክርስቶስን በመፈለግ መጽናት አለብን፡፡
መግደላዊት ማርያም አመጣጧ ሀዘኗን ገልጣ ለዘላለም ልትሰናበት ነው፡፡ ነገር ግን በተቃራኒው ዘላለማዊ ደስታ ገጠማት፡፡ ሰውን ሁሉ ሳይለይ የሚገዛ ገዥ ምንድነው? ብንል ሀዘን ነው፡፡ ተጎዳሁ፣ አጣሁ፣ ተስፋዬ መና ሆነ የምንልበት የየራሳችን ሀዘን አለን፡፡ ብዙዎቻችን ገና ወደፊት ለማዘን ምንጣፍ እናስተካክላለን፡፡ የምንፈልጋቸው ሰዎችም አብረውን የሚያዝኑና የሚያላቅሱንን ነው፡፡ ነገር ግን ከሀዘን ምክንያታችን የደስታ ምክንያታችን በዝቷል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ተነሥቷል፡፡ እስከ ዛሬ የመደሰት መብታችንን ተጠቅመን አናውቅም፡፡ ከአሁን ሰዓት ጀምሮ ግን ልንጠቀም ይገባናል፡፡ ከተጎዳነው ጉዳት በክርስቶስ ያገኘነው ድኅነት በልጧልና፡፡
ለወዳጆቻችን ግድ የሌለን የትም የማይሄዱ ስለሚመስለን ነው፡፡ እንደውም፡- «አጥብቀው ያሰሩትን ዘቅዝቀው ይሸከሙታል» እንላለን፡፡ የሚወዱን ሰዎች የትም የሚሄዱ ስለማይመስለን ለፍቅራቸው ዋጋ አንሰጥም፡፡ ያጣናቸው ቀን በብርቱ የምናዝነውም ለዚህ ነው፡፡ እነዚህን ወዳጆቻችንን ከሞት ተነሥተው ብናገኛቸው ግን ለአፍታ እንኳ ከአጠገባቸው አንለይም፡፡ ወዳጅን ከሞት በኋላ ማግኘት ብርቱ ነውና፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም ከሞት በኋላ ያገኘነው ወዳጃችን ስለሆነ ለአፍታ ልንለየው አይገባንም፡፡
ይልቁንም እርሱን እንደ መምህራችን እያየነው ልንከተለው፣ ከነድካማችን ልንቀርበው፣ በእምነት ልንከተለው፣ ጊዜአችንን ልንሰጠው፣ ተግሳጹን ልናከብር፣ አሳድገኝ ልንለው፣ በፍቅር ልንፈራው፣ በፊቱ ልንራቆት፣ የእውቀታችን ማረጋገጫ ልናደርገው፣ ደስታውን ደስታችን ልናደርግ ይገባናል፡፡
ጸሎት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
የሕይወት ቃል ያለህ፣ ከመቃብር በላይ የገነንከው፣ ለሚሹህ የምትገኝ፣ የተስፋ አምላክ የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ አመሰግንሃለሁ፡፡ እኔ ያስፈልገኛል ያልኩት የሚጎዳኝ፣ አንተ አያስፈልግህም ያልከኝ የሚጠቅመኝ ሆኖ ብዙ ዘመን አየሁት፡፡ ለራሴ ከቸርኩት፣ አንተ የነሣኸኝ በረከት እንደነበረ አስተዋልሁ፡፡ አንተ ግን ያለ እውቀት ያጕረመረምኩትን ማጕረምረም በፍቅርና በርኅራኄ አይተህ ለዚህ ስላደረስከኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ ጌታዬ ሆይ፡ ማን ይከስሃል እንጂ በእኔ ትከሰስ ነበር፡- ድሃውንና ሰነፉን አጥግበሃልና፣ ያልተማረውንና የማይመጥነውን ሾመሃልና፣ ወንጀለኛን በነጻ ለቀሃልና፡፡ ያንተ ስጦታ ከማንነቴ ልክ በላይ ሆኖብኛልና ተመስገን፡፡ ይህን ሁሉ ውለታ ተሸክሜ ዝም ብያለሁና እባክህ ይቅር በለኝ፡፡ ስለሞቱት እያዘንኩ እኔ ግን ኖሬ ለመሥራትና ለማገልገል እማረራለሁ፡፡ እኔ ብላሽ ነኝና ባለጌነቴን አትይብኝ፡፡ ባንተ መርካትን፣ የበቃኝን ኑሮ አለማምደኝ፡፡ ስቃዬ ሲበዛ ስቃይህን አስታውሰኝ፡፡ ከሁሉ በላይ ረቡኒ ብዬ እንድከተልህ መዓዛህ ይጥራኝ፡፡ ጊዜው ቀትር ነውና አንተ የበጎች እረኛ እንድመጣ መመሰጊያህን ንገረኝ፡፡ ውስጡና ላዩ የጠወለገውን ወገኔን እባክህ አለሁ በለው፡፡ የማይፈጸም ምስጋና ከልቤ እስከ አርያም ላንተ ይሁን አሜን፡፡
— ተፈጸመ—
ረቡኒ
በዲ/ን አሸናፊ መኰንን
የመጀመሪያ እትም ሚያዝያ 2002 ዓ/ም
አድራሻ – 0911 39 35 21/0911 67 82 51
ፖ.ሳ.ቁ. 62552
አ.አ. ኢትዮጵያ