የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ረቡኒ /3

 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከመስቀል አውርደው ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ የገነዙት ሁለት ሰዎች ናቸው ። የአርማትያሱ ዮሴፍና የማታው ተማሪ ኒቆዲሞስ ናቸው ። በስውር ተምረው በግልጥ መሰከሩ ። ዛሬ አሥር ሰዎች ብቻ ስለ ተገኙበት ቀብር በታላቅ ኀዘን እንሰማለን ። ሟች ወገናችንን አሥር ሰው ስለ ቀበረው ውስጣችን ያዝናል ። ጌታችን ግን ሁለት ሰዎች ገንዘው ቀብረውታል ። ይህንን ስሜታችንን እርሱ አስቀድሞ ተቤዥቶታል ። በሕይወቱ ከአምስት ገበያ የሚበልጥ ሕዝብ የተከተለው በሞቱ ሁለት ሰዎች ብቻ ገነዙት ። ከብዙዎች ጋር ኖረው ብቻቸውን ለሚሞቱት ድፍረት ለመሆን ይህ እንዲሆንበት ፈቀደ ። እንጀራ አበርክቶ ሲያበላ አምስት ሺህ ሰዎች ነበሩ ፣ ራሱን ለዓለም ሲሠዋ ግን ዮሐንስና እመቤታችን ብቻ ነበሩ ። ለሰላማዊ ሰልፍ ስሜት እንጂ እውነት አያስፈልግም ። እውነቱ ያለው ሰልፉን የሚመሩት ጋ ነው ። ለሚጮኽለት ሰዎች ይጮኻሉ ፣ የተከበበን ሰዎች ከበው ይዘፍኑለታል ። ብቸኛ የሚባለው ግን በሰው ጠኔ ይሞታል ። ለእንጀራ አቤት የሚለው ዓለም ለሕይወት ዲዳ ይሆናል ።

በመከራ ሰዓት ሁለት ወዳጆች ፣ በቀብራችን ሰዓት ሁለት ቀባሪዎች ካገኘን ጌታን መሰልን ማለት ነው ። በመከራ ሰዓት የሚገኙ ሁለት ወዳጆች ከሺህ ወረተኞች ይበልጣሉ ፤ በቀብር ሰዓት የሚገኙ ደቀ መዛሙርቶች ከሚሊዮን ደጋፊ ይልቃሉ ። ከሕይወት አልፈን የቀብራችን ሥነ ሥርዓት ያስጨንቀናል ። በትክክል ያልኖረ ሰው በትክክል ስለ መቀበር ያስባል ። ሥራውን ያልጨረሰ ሞትን ይፈራል ፣ እያጉረመረመም ይህችን ዓለም ይለቃል ። የምንሞተው ሞትን ስለምንወደው ሳይሆን ሞት ስለሚወደን ነው ። የማይቀበር ሥራ መሥራት ግን ከመኖር ይበልጣል ። ሥራውን የጨረሰ በሰላም በአልጋው ላይ ያርፋል ። ሲኦል ማለት ያልጨረስናቸው መልካም ነገሮች ከፊታችን ላይ ሲደቀኑ የሚሰማን ስቃይ ነው ። ሰው ማለት ከሞት ባሻገር ስላለው ሕይወት የሚያስብ እንጂ በቀብሩ ላይ ስለሚኖረው ሥነ ሥርዓት የሚናዘዝ ፣ ባላየውም የሕዝብ ጎርፍ ይገኝልኝ የሚል አይደለም ። ብዙ ሰዎች የሚኖሩት ለቀብራቸው ነው ። ለቀብራችን መኖር ስንጀምር ለእውነት መሞት እናቆማለን ።
በእኩለ ቀን ደቀ መዛሙርት ሲበተኑ ፣ በእኩለ ሌሊት ቅዱሳን ሴቶች ደፈሩ  ። ወንዶች በቀን ፈሩ ፣ ሴቶች በሌሊት ደፈሩ ። ያልተለመዱ ነገሮች በመስቀሉ ዙሪያ ይሆናሉ ። መስቀሉ ሰው ልኩ የሚመዘንበት መለኮታዊ መለኪያ ነው ። ሞት ለሦስት ቀን ነው ። ለሦስት ቀንም የሞተው በፈቃዱ እንጂ ገዳዮች መግደል ስለ ቻሉ አይደለም ። መከራችንም ለአጭር ጊዜ ነው ፣ ይህ ሁሉ የሚሆነው ጠላት ስለ ቻለ ሳይሆን በዚህ ውስጥ አልፈን የምንማረው ነገር ስላለ ነው ። አንዳንዴም እግዚአብሔር እኛን አስችሎ ሌሎችን ያስተምራል ። ትንሣኤ ግን ለዘላለም ነው ። ለሚያልፍ ቀን ይሁዳ ሠያጤ እግዚእ/ጌታን ሻጭ ሆነ ። ጴጥሮስ ፈሪዋን ፈርቶ ካደ ። ደቀ መዛሙርት ያለ አባራሪ ሸሹ ። የዛሬው መዋረድ ፣ የዛሬው ሰው አልባ መሆን ፣ የዛሬው የስድብ መለማመጃ መሆን ፣ የዛሬው አለመደመጥ ፣ የዛሬው መገፋት ፣ የዛሬው ስሜት እንደሌለው ሰው በጦር መወጋት ፣ የዛሬው ተሰናባች መብዛት ያበቃል ። እግዚአብሔር ቀኝ ኋላ ዙር ሲል የመጨረሻው የመጀመሪያ ይሆናል ። ዮሴፍን የሸጡት ዮሴፍን እህል ሊለምኑ መጡ ። እነርሱ ያኔ መሸጥ ይችላሉ ፣ እርሱ ዛሬ ፈርዶ መግደል ይችላል ። የምንገፋቸው በበለጠ ኃይል ይጠብቁናል ። ዮሴፍ የሚችለውን ክፉ አላደረገም ፣ ዮሴፍ መብቱንም አላስከበረም ። የሚችሉት ሁሉ አይደረግም ። የሚችሉት መልካም ነገር ሁሉ አይቀርም ። ዛሬ ገሸሽ ያልናቸው ፣ በማጣታቸው ንግግራቸው እሬት የሆነብን ፣ በሐሰት መስክረን ያስፈረድንባቸው ፣ በብቸኝነታቸው አጥራቸውን ያፈረስንባቸው ፣ ስማቸውን ሽረን ሥራቸውን የቀማናቸው ታላቅ ይሆናሉ ፤ እኛም እንደ ዮሴፍ ወንድሞች እግራቸው ሥር ዝቅ እንላለን ። ዮሴፍ ተለውጦ ስለነበር ወንድሞቹ አላወቁትም ፣ እርሱ ግን አወቃቸው ። በክፉዎች ሰፈር ለውጥ የለም ፣ ደጎች ግን ይለወጣሉና የቀድሞ መልካቸው ይሰወራል ። መግደላዊት ማርያም በዚያች ሌሊት ስትገሰግስ የእግዚአብሔር እንጂ የጊዜ ሎሌ ስላልነበረች ነው ።
የኢየሩሳሌም ቆነጃጅት ደረታቸውን እየደቁ ያለቀሱለት መስቀል ተሸካሚው የምድርን መሠረት እያናጋ ተነሣ ። እናቱ ትንሣኤውን እያወቀች ያለቀሰችለት እርሱ የብዙዎችን እንባ ሊጠርግ ተነሣ ። ጭፍሮች ከበው የደበደቡት የኃይሉን ምስጋና ከመላእክት ተቀበለ ። ርኩስ ምራቅ የተተፋበት ዛሬ በግርማው ሲነሣ የታጠቁና የሰለጠኑ ወታደሮች ባፍጢማቸው ተደፉ ። እግዚአብሔር ሲነሣ እንኳን ለክንዱ ለጣቱ የሚሆን አቅም የለንም ። ልብሱን ገፍፈው የተዘባበቱበት የማይወልቅ የብርሃን ልብስ ለበሰ ። ስምዖን የቀሬናው መስቀል ያገዘው መከራችንን ሊያቀል በጎልጎታ ተነሣ ። ተራራ የተጫነውን ማንም አያወጣውም ፣ ሞትና መቃብር ከተራራ በላይ ናቸው ። የሞትን  ተራራ በትንሣኤው አንከባለለ ። እስከ ዛሬ በትምህርቱ ረቡኒ ፣ በተአምራቱ ድንቅ አድራጊ ይባል የነበረው አሁን በትንሣኤው የኃያላን ኃያል ተባለ ። ኃያላን ሁሉ ኃያል የተባሉት ራሳቸውን ከሞት አድነው ሳይሆን ገድለው ነው ። እርሱ ሞትን እንደ ባለጌ የገሠጸ ኃያል ነው ። ማታ የተኛ ጠዋት እንገናኝ እንደሚል ሞትን እንደ እንቅልፍ ቆጥሮ በገሊላ እቀድማችኋለሁ ያለ ነው ። ከሞት በኋላ ቀጠሮ የሰጠ እርሱ ብቻ ነው ።
አልዓዛር ቢነሣ በክርስቶስ ሥልጣን ተነሣ ፣ ክርስቶስ ግን በራሱ ሥልጣን ተነሣ ። አልዓዛር ቢነሣ በአሮጌው ሥጋ ተነሣ ፣ ክርስቶስ ግን በአዲሱ የትንሣኤ አካል ተነሣ ። በዚህም የትንሣኤ በኩር ተባለ ። ዛሬ በንስሐ ትንሣኤ ልቡናን ፣ በምጽአት ትንሣኤ ሥጋን የሚሰጠን እርሱ ተነሣ ። የመቃብሩ ጠባቂዎች በእምነት ትንሣኤውን ባያወሩም በድንጋጤ ስካር ግን መሰከሩ ። በዚያች ሌሊት ከተማውን የሞላው ዜና መግደላዊት ማርያም ጋ አልደረሰም ነበር ። በታላቅ ኀዘን ውስጥ ያሉ የእግዚአብሔርን መነሣት አይሰሙም ። የድንጋጤው ስካር ወታደሮችን ጊዜያዊ ሰባኪ አደረጋቸው ። በርግጥ ሞቷል ተብሎ በሕግ አስፈጻሚዎች ተረጋገጠ ፣ አሁንም ትንሣኤው በሕግ ተረጋገጠ ።
የካህናት አለቆቹም የወታደሮቹን ስብከት በሰሙ ጊዜ ደንግጠው፡- “እኛ ተኝተን ሳለን ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት በሉ” አሏቸው ። ከተኙ ሊያውቁ አይችሉም ። እንዲጠብቅ የተመደበ ወታደር ቢተኛ ፍርዱ ሞት ነው ። ደቀ መዛሙርቱ ይህ አቅም ካላቸው ዓርብ ዕለት የማስለቀቅ ሙከራ ያደርጉ ነበር ። ወታደሮች ተዘናግተው ደቀ መዛሙርት ከሰረቁ ደግሞ ፍርድ ቤት መቅረብ አለባቸው ። የካህናት አለቆች ማግባቢያ አደረጉ ። ለምን ተኛችሁ ካለ ገዥው እኛ እናስረዳዋለን አሉ ። ጲላጦስ ግን ወታደሮቹን ጠርቶ ነገሩን ተረዳ ። ክርስቶስ መነሣቱን አመነ ። የመሰከሩለት ወታደሮች ግን ገንዘብ ተቀብለው ተሰረቀ እያሉ ማውራቱን ቀጠሉ ። የሰበከው ካደ ፣ የተሰበከው አመነ ። ጲላጦስም ልቡ ኀዘነተኛ ነበር ፣ አምኖበት ሳይሆን ሰው ላለማጣት ክርስቶስን ሰቅሎት ነበር ። ለገደለው ጌታ ሰማዕት ሆነ ።
የካህናት አለቆች ዛሬም በክፋታቸው ተስፋ አልቆረጡም ። ሰው ለፍቅር እንዲህ በማይታመንበት ዓለም ለቅናታቸው ታማኝ ሆኑ ። ገንዘብ ሲናገር ፍትሕ ጸጥ ይላል እንደሚባለው ወታደሮቹም ትንሣኤውን ለማሳበል በገንዘብ ኃይል መለፍለፍ ጀመሩ ። ሰይጣን ወታደር አስቆመ ፣… ብዙ ነገር አደረገ   ። የተሳካላት ግን በገንዘብ የገዛቸው የሐሰት ምስክሮች ነበሩ ። ዛሬም በብዙ ነገር እጅ ያልሰጡ በገንዘብ እጅ የሰጡ ብዙዎች ናቸው ። ክርስቶስ ተነሥቷል የገንዘብ ሎሌ መሆን አይገባም ።
የትንሣኤ ጌታ ወደ ኋላ የሚጎትተኝን የዚህን ዓለም ማሰሪያ ቍረጥልኝ ።
ይቀጥላል
የመስቀሉ ገጽ 8ሐ
ሚያዝያ 22 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።