መግደላዊት ማርያም ሙሉ ፍቅር ነበራት ። ለዚህም ሽቱ ይዛ ወደ መቃብሩ ወርዳለች ። ሙሉ እምነት ግን አልነበራትም ። ለሙታን የሚሆን ሽቱ ይዛ ሂዳለችና ። በሰማይ ያለውን ልዕልናውን የሚያውቁ ቅዱሳን መላእክት ሰው በመሆንና በሰው እጅ መከራ በመቀበል ያሳየውን ትሕትና ባሰቡ ጊዜ ከአእምሮ በላይ ሆኖባቸዋል ። ክርስቶስ በበረት ሲወለድ ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም በማለት ቅዱሳን መላእክት አመሰገኑ ። በምድርማ ለእግዚአብሔር የተለቀቀለት የከብቶች በረት ነበረ ። ልዕልናው በሚታወቅባት አርያም ክብር ይሁንለት ማለታቸው ነው ። እኛ ባናከብረው መላእክቱ ያከብሩታል ፣ መላእክት ባያከብሩት ባሕርዩ ባሕርዩን ያከብረዋል ። እርሱ በነገሥታት ቤተ መንግሥት መወለድ አልፈለገም ፣ እረኞች ሊያዩት መሄድ አይችሉምና ። ነገሥታት ዝቅ ማለትን ይማሩ ዘንድ በበረት ተወለደ ። የምሥራቅ ነገሥታትም በበረት ሰገዱለት ። በትክክል ካለን ትዕቢተኛ አንሆንም ። ትዕቢትን የሚወለደው የሚታበዩበት ነገር ሲያጠራጥር ነው ። ሌሎች የላቸውም እንዳይሉን በትዕቢት ፣ በቍጣና በጩኸት ለመሸፈን የሚደረግ ሙከራ ነው ። ጌታችን ወደ ግብጽ ሲሰደድ መላእክት አልተለዩም ። እንዲራዱ አልፈቀደላቸውም ፣ እርሱ መከራ ለመቀበል ፈቅዷልና ። በገዳመ ቆሮንቶስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሲጦምና ሲፈተንም መላእክት በአንክሮ ያዩ ነበር ። በለበሰው ሥጋ ፈታኙን ድል ከነሣልን በኋላ ቀርበው አገለገሉት ። በመስቀል ሲሰቀልም ከአቅማቸው በላይ ሆነ ። ሲነሣም ትንሣኤውን ከሰው አለማመን ጋር እየታገሉ ሰበኩ ።
ትንሣኤ ለሐዋርያው ጴጥሮስ ንስሐ ክብር የሰጠ ነው ። ባለመውደቅ እግዚአብሔርን ብናከብረው ምንኛ መልካም ነበር ። ወድቀን በመነሣት እንድናከብረው እግዚአብሔር ንስሐን አዘጋጀ ። ሰውን ሰው ያደረገው ሥራ ሳይሆን ንስሐ ነው ። ሐዋርያው ጴጥሮስ ለዚህ ምስክር ነው ። እንደ ጴጥሮስ በአፋችን ባንክድም በሥራችን ክደነዋል ። እግዚአብሔር የለም ማለትና እግዚአብሔር እንደ ሌለ መኖር ሁለቱም አንድ ዓይነት ነው ። እየሰበኩን በክርስቶስ የማያምኑ አሉ ። ስብከት የአማርኛ መለማመጃ የሆነባቸው የእምነት ልብ የሌላቸው ብዙ የኢየሱስ የአፍ ወዳጆች አሉ ። አልካድነውም ብለን አንኮራም ።
ጌታችን ከሥቃዩ በላይ የጴጥሮስ የልብ ኀዘን ይሰማው ነበር ። ከመስቀል ጣሩ በላይ የጠላቶቹ መጥፋት ያሳዝነው ነበር ። ጠላቶቹ ይቅርታውን ሳይሰሙ እንዳይሄዱ የመጀመሪያውን የመስቀል ቃል የተናገረው ለእነርሱ ነው ። ቃሉም፡- “አባት ሆይ ፣ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” የሚል ነው ። አሁንም ትንሣኤውን ለጴጥሮስ አስቀድማችሁ ንገሩልኝ ማለቱ ንስሐው ተቀባይነት ማግኘቱን ለመግለጥ ነው ። የክርስቶስ መነሣት ጴጥሮስን እንደገና ቀና ያደረገ ነው ። ሐዋርያው ጴጥሮስ በዶሮ ተሰብኮ ንስሐ የገባ ፣ በመግደላዊት ማርያም ተሰብኮ ትንሣኤን ያረጋገጠ ነው ። ልቡ ቅርብ ነውና እግዚአብሔር ተቀብሎታል ። አንዳንድ ልቦች የመንፈቅ መንገድ ብንጓዝም አንደርስባቸውም ። በልባችን ያሳዘነውን ያህል በእጃችን አንክሰውም ። ክፉ ልብ በእግዚአብሔር የተጠላ ነው ። እኛ ስንቀየም የተቀየምነውን ሰው ስሙን አንጠራም ። የጴጥሮስ ስም መጠቀሱ ግን ዛሬም እንደሚወደው ማረጋገጫ ነው ። ጴጥሮስ የሚለውን ስም መላእክትም ያውቁት ነበር ። ቅድሚያ ለተነሣሕያን/ለንስሐ ገቢዎች ነው ። በዚህም ጴጥሮስ ይቅር እንደ ተባለ አወቀ ።
መላእክት መሄጃ አጥተው በሰማይ የቀሩ አይደሉም ። ነጻ ፈቃድ ያላቸው ሲሆኑ ሥላሴን መርጠው በክብሩ የተጠለሉ ናቸው ። ከወገናቸው አንደኛው ነገድ ክዶ ሰይጣን ሁኗል ። አዳምም ነጻ ፈቃዱን ተጠቅሞ ቅጠል በልቷል ። እነዚህ መላእክት ግን አንድ ቀን ያላስቀየሙት ወዳጆቹ ናቸው ። እነርሱን በዱር ትቶ የጠፋነውን ፍለጋ የመጣ አምላክ ስሙ ይባረክ ። እኛን የፈለገን የወዳጅ ረሀብ ኖሮበት አይደለም ። ከቍጥር ውጭ የሆኑ ብዙ መላእክት አሉት ። ዕለት ዕለት የመላእክት ወዳጅነት ሊታሰበን ይገባል ። በቀንና በሌሊት እኛን የሚጠብቁን መላእክት አሉና ። እነዚህ መላእክት ለሴራ እየሄድን እያዘኑም ቢሆን ስለ እግዚአብሔር ብለው ይጠብቁናል ። ስለ ወዳጅ እሬት ይላሳልና ። መላእክት ወዳጆቻችን ናቸው ። የእግዚአብሔር ፈቃድ ሙሉ የሆነው በሰማይ ወይም በማኅበረ መላእክት ነው ። ጌታችን ትንሣኤውን በመላእክት አስነገረ ። እጅግ ኃያላን የሆኑ መላእክትና ዓለም ያደከማት መግደላዊት ማርያም ትንሣኤውን ይናገራሉ ። ጌታ ደግሞ በጊዜው ይገለጣል ። መላእክት ፣ መግደላዊት ማርያም ጌታን የሚያብራሩ እንጂ የሚሸፍኑ አይደሉም ።
ጌታችን እስከ ሆሳዕና አገልግሎቱ በገሊላ አውራጃ ነበር ። የመጨረሻ ሳምንት አገልግሎቱ ግን በኢየሩሳሌም ሆነ ። በገሊላ እቀድማችኋለሁ አላቸው ። የሞተው ጌታ ያልሞቱትን እቀድማችኋለሁ አለ ። ማንም አይቀድመውምና ። እርሱን የሚቀድም ሯጭ ፣ እርሱን የሚያስከትልም ፊታውራሪ የለም ። ገሊላ መታየቱ ገሊላ ደስ እንዲላት ፣ ትንሣኤው እርግጥ መሆኑን ለማሳየት ፣ እስከ ገሊላ ድረስ በመታየት ኢየሩሳሌም እንደማትይዘው ለመግለጥ ነው ። በገሊላ እቀድማችኋለሁ በማለት የተናገረው ወደ አባቴም ዐርጋለሁ አለ ።
ልብ በኀዘን ሲሞላ የምሥራችን መስማት ፣ ዓይን በእንባ ሲሸፈን የቆመውን ጌታ ማየት ይቸገራል ። ደቀ መዛሙርቱ በኀዘነተኛ ልብ የምሥራቹን መቀበል አቃታቸው ፣ መግደላዊት ማርያምም በእንባ በተሸፈነ ዓይን ጌታን መለየት አቃታት ። ቤተ ክርስያን ስለ ክርስቶስ ሞት በዘመናት አልቅሳለች ። ስለ መሰረቁ ግን አላለቀሰችም ። መሰረቁን ማመን ትንሣኤን አለመቀበል ነውና ። ብዙ ሰዎች ጌታዬን ከልቤ ውስደውታል በማለት በሰዎች ያሳብባሉ ። በዓመፀኛ ሰባክያን ፣ በጨካኝ አገልጋዮች ምክንያት ጌታዬ ከልቤ ተወስዷል የሚሉ አሉ ። በተለያዩ ገጠመኞች እያሳበቡ ፣ ይልቁንም በወንጌል በሚመጣ መከራ እያጠጋጉ ጌታዬን ከልቤ ወስደውታል ይላሉ ። ወስደውታል ክስ ነው ። ጌታ ግን ተነሥቷል ። ማንም እጁን ላይጭንበት ፣ ማንም ላይወስድብን ከፍ ከፍ ብሏል ።
ሰማያውያን መላእክት ድንጋይ ሲፈነቅሉ ፣ ባዶ መቃብር ሲያስጎበኙ ከሰው ጋር ቃል ለቃል ሲነጋገሩ ማስታወስ ይገባናል ። ትንሣኤ ምድራውያንና ሰማያውያን ኅብረት የፈጸሙበት ነው ። ከመቃብሩ ድንጋይ በላይ የሰውን ጥርጣሬ ማንከባለል መላእክትን ከበዳቸው ። ጌታ በፊታቸው ቆሞ ብቻዬን ነኝ የሚሉ ፣ እየተናገራቸው ተስፋ የሚቆርጡ ብዙ ማርያሞች አሉ ። ኀዘን የምናስበውን እንድንሰማ እንጂ እውነቱን እንድንቀበል አያደርገንም ። ኀዘን ዓይንና ጆሮን በመያዝ የታወቀ ነው ።
ለአገልጋዮቹ ስላቃተች ራሱ ጌታ ወደ መግደላዊት ማርያም መጣ ። ባሮቹን ሲገፉ ወራሹ እንደመጣ አሁንም በአትክልት ስፍራ ውስጥ ጌታ ተገለጠ ። ጌታዋን ማንም አልወሰደባትም ፣ አለማመን ግን ወስዶባታል ። ጌታ የተሰረቀው ከልቧ እንጂ ከመቃብሩ አልነበረም ። የቅርቡን ሩቅ ፈለገችው ። ሕያውን ሙት አደረገችው ። “ኢየሱስም፦ አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ? አላት።” /ዮሐ. 20፡15 ።/ ለምን እንደምታለቅስ ያውቃል ፣ የምታለቅሰው ግን ጌታ ተሰረቀ ብላ ነው ፤ እርሱ ግን አልተወሰደምና ልቅሶዋ ትክክል አይደለም ። ብዙ ሰዎች በእንባ ሐሰትን እውነት ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ ። የምትፈልገው አጠገቧ ቆሟል ። ካልተደሰተች የምትፈልገውን አታውቅም ማለት ነው ። ጌታ የአትክልት ጠባቂ መሰላት ። አካባቢው ሊሰጣት የሚችለው ምክንያት ይህ ነው ። ወስደኸው እንደሆነ ንገረኝ ብላ ስታለቅስ፡- “ኢየሱስም፦ ማርያም አላት፡- እርስዋ ዘወር ብላ በዕብራይስጥ፡- ረቡኒ አለችው ፤ ትርጓሜውም፡- መምህር ሆይ ማለት ነው ።”
“ኢየሱስም፦ ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ ፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ፡- እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዓርጋለሁ ብለሽ ንገሪአቸው አላት ።” ተሰርቋል ሲትይኝ ገና ዐርጋለሁ ፣ በጥርጣሬ ልብሽ ሕያውን ሙት እያልሽ አትንኪኝ እያላት ነው ። መነካትን የከለከለው መሰናበት አሁን እንዳልሆነ ሊነግራት ፣ እንዳይሄድባት ልትይዘው ስትል ተይ ሊላት ፣ ከሁሉ በላይ ባለማመኗ ሊገሥጻት ነው ።
ረቡኒ አለችው ። አንተ ፈራጅ ብትሆንም አትፈርድብንም ገና ታስተምረናለህ ። ገድለንህ በሦስተኛውም ቀን ትወደናለህ ። አንተ የነፍስ ረቡኒ ፣ የአገር መምህር ፣ የትውልድ አቅኚ ነህ ። ረቡኒ እኛን ማሳመን የማይደክምህ ፣ በተራራ በሸለቆ የማትለየን ፣ ሁሉን ለትምህርታችን የምታደርግልን ነህ ። ረቡኒ መባል ካንተ ለተማረች ፣ ፍቅርን ለቀመሰች ነፍስ ተገቢዋ ነው ። ረቡኒ የአሳብ ምርኮኛውን የምታነጻ ፣ ካለማመኑ ጋር የተወዳጀውን የምትገሥጽ ፣ ሰባራውን የምትጠግን ረቢኒ አንተ ነህ ፣ የሕይወት መምህር።
የሆንከውና የሆንነው ፣ የምትፈልገውና የምናቀርበው ቢለያይም ፣ እየተናገርከን ተስፋ ብንቆርጥ ፣ እያየንህ ባናይህም ፣ ብርሃን ለብሰህ ሳለ አትክልት ጠባቂ ብናደርግህም አንተ ግን ሳትቀየም አንተን ወደ ማመን አድርሰን ። ዓለም ከማታሞጋግሰን አንተ ገሥጸን ። አትንኩኝ በለንና በልባችን እደር ። ለእጃችን ከልክለኸን ሥጋና ደምህን ለመብላት አብቃን ። በዙሪያችን ማማተር ትተን በልባችን እንድንሸከምህ እርዳን ። በማይሰለቸው መምህርነትህ ለዘላለሙ አሜን ።
ረቡኒ ተፈጸመ
የመስቀሉ ገጽ 8 ሰ
ሚያዝያ 27 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን