የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ረቡኒ

 “ኢየሱስም፦ ማርያም አላት ። እርስዋ ዘወር ብላ በዕብራይስጥ፡- ረቡኒ አለችው ፤ ትርጓሜውም፡- መምህር ሆይ ማለት ነው ።” ዮሐ. 20፡16
. . .
“ይትፌሣሕ ሰማይ ወትትሐሠይ ምድር ወይንፍሑ ቀርነ መሠረታተ ሕምዝ ወይወውዑ አድባር ወአውግር ወኩሉ ዕፀወ ገዳም ወዮምሰ ዐባይ ፍሥሐ በሰማያት ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሐፂባ በደመ ክርስቶስ” /መጽሐፈ ድጓ/
ትርጓሜ፡-
“ሰማይ ይደሰታል ፣ ምድርም ትደሰታለች ፣ የምድር መሠረቶችም ቀንደ መለከትን ይንፉ /ይደሰቱ/ ፤ ተራሮችና ኮረብቶችም /ነገሥታት መኳንንት/ ይጩኹ/ይደሰቱ/ ፣ የምድረ በዳ እንጨቶችም ይጩኹ ፣ ዛሬ በሰማያት ታላቅ ደስታ ሆነ ፤ ምድርም በክርስቶስ ደም ታጥባ ፋሲካን/ደስታን/ ታደርጋለች ።”
. . .
የጥቁሮች መብት ታጋይ የነበረው ማርቲን ሉተር ኪንግ፡- “ከዋክብትን ማየት የሚቻለው በጨለማ ብቻ ነው” ብሏል ። ጨለማው የሚሰውራቸው ተራሮች አሉ ፣ ጨለማው የሚገልጣቸው ከዋክብት ደግሞ አሉ ። ጨለማው የሚሰውራቸው የቅርብ ከፍታዎች አሉ ፣ ጨለማው የሚገልጣቸው የሩቅ ብርሃናት አሉ ። በቀን የሚታዩ ኮረብታዎች በማታ አይታዩም ። ሰርጋችንን ያጀቡ መከራችንን ማጀብ አይፈልጉም ። ቍስላችን ላይ እንጨት የሰደዱ መከራቸው ላይ እንድናለቅስ ይፈልጋሉ ። አመመኝ እንጂ ያማቸዋል የማይል ሰው ከሁሉ ይልቅ አላዋቂ ነው ። ራስን ብቻ እያዳመጡ መኖር ብቸኛ ያደርጋል ። ሥልጣን ፀሐይ ነው ፣ ብዙ ሰዎችን በፊታችን ይኮለኩላል ። ሰው ባይኖረንም ያለን አስመስሎ ያደነዝዘናል ። ሀብትም ደስታን ሳይሆን ሳቅን ፣ የልብ አክባሪዎችን ሳይሆን አንገት አዘቅዛቂዎችን ያተርፍልናል ። ዝናም እንደ ጎርፍ ጠርጎ እስኪወስደን ሳቅ ፣ ሳቅ ይለናል ። እዩኝ እዩኝ ማለትም ደብቁኝ ፣ ደብቁኝ ያሰኛል ። የከበቡን ብዙዎች ሲበተኑ የሚቀሩ ትንሽ ከዋክብት አሉ ። እነዚህን በሰላም ቀን ለማየት ዓይን አላበጀንም ነበር ። ጨለማው ግን ያበሩ ፀሐዮች የሚጨልሙበት የተሰወሩ ከዋክብት የሚገለጡበት ነው ። ይህ ሰዓት ባይኖር የእውነት ሳይሆን የግምት ነዋሪዎች እንሆን ነበር ። መግደላዊት ማርያም በጨለማ ሰዓት የታየች ኮከብ ናት ። መከራውን የተካፈሉ ደስታውን ያያሉ ። ቀድመው የመጡ የምሥራቹን ቀድመው ይሰማሉ ። በዋጋ እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ዋጋቸው ከፍ ይላል ።

የለመድነው አለ ብለን ያልነው ነገር ስንደርስ መሞቱ ነው ። አለው ብለን የገሰገስንበት ስናገኘው ለማኝ ሁኖ ፍርፋሪ መልቀሙ ነው ። ቁንጅናው እየገረመን በድሮ መልኩ የመዘንነው ስንደርስ እንደ አበባ መርገፉ ነው ። በዓለም ላይ የምንጠብቀውን ብቻ ሳይሆን የማንጠብቀውንም እንድንቀበል ሕይወት ዕዳ ጥላብናለች ። መግደላዊት ማርያም የገጠማት ግን በተቃራኒው ነው ። ሞትን ስትጠብቅ ትንሣኤ ፣ በድን እየፈለገች ሕያውን አገኘች ። ፍቅሩን ሞት አልወሰደባትም ። ፍቅር ዘላለማዊ የሚሆነው በሞት ነው ። እየወደድናቸው የሞቱ ፍቅራቸው በውስጣችን ተቀብሮ ይኖራል ። ጌታ የሞተው በፍቅሩ ፣ የተነሣው በኃይሉ ነው ። ካህናት ያወገዙትን ፣ ነገሥታት የፈረዱበትን ብትክድ ኖሮ ረቡኒ እያለች አትፈልገውም ነበር ። ፍቅር በፍቅር እንጂ በድምፅ ብልጫ አይወስንም ። ካህናትና ነገሥታት በእውነት ይመዘናሉ እንጂ እውነት በሰዎች አትመዘንም ። እውነት ነገሥታት እየፈረዱባት ፣ ካህናት እያወገዙአት ፣ አፈኞች እያሳደሙባት ፣ ጉልበተኞች እየዛቱባት ፣ ገንዘብ የበሉ የሐሰት መስካሪዎች እያሳበሏት ፀንታ ትኖራለች ። የእውነት አገሯ ወዴት ነው ? ብንል እውነት አገር የላትም ። አገራት ሁሉ በእውነት ውስጥ አሉ ። መግደላዊት ማርያም ፍቅሯ በፍቅር ላይ የተመሠረተ ነበር ። ልቧ ስለ ክርስቶስ እየነገራት ዙሪያዋን አታዳምጥም ነበር ። በዓይን የሚያዩትን በጆሮ መፈለግ ያላዋቂዎች ኑሮ ነው ። ከመንፈስ ቅዱስ ምስክርነት ወጥታ ወደ ደጋፊዎች ድጋፍ ዝቅ አላለችም ። የሆነላትን ታውቀዋለችና የሆነልኝ ምንድነው ? ብላ ጎረቤት አልጠየቀችም ። ይህ ስሜ ማነው ? እንደ ማለት ያህል ነው ። ሁሉን ይወርስ ዘንድ አምላኳ ሞተ ተባለ ። የሕያዋንና የሙታን ጌታ ይባላልና ።
ካህናትና ነገሥታት ተስማምተው የገደሉትን ሴቶችና መላእክት ተስማምተው እያመሰገኑት ነው ። አጋንንትና የሮማ ወታደሮች ይጠብቁት የነበረውን መቃብር ቅዱሳን መላእክት ድንጋዩን አንከባለው እያሳዩት ነው ። ባዶ ነገር ተጎብኝቶ አያውቅም ። የክርስቶስ መቃብር ግን ከተጎበኙ ነገሮች ሁሉ ይልቅ እስከ ዛሬ ድንቅ ስፍራ ነው ። በጉብኝት ስፍራዎች ላይ ታሪክ አዋቂዎች ወይም ጆሮ ጠገቦች ያስጎበኛሉ ፣ ቅዱሳን መላእክት ያስጎበኙት ግን ባዶው የክርስቶስ መቃብር ነው ። ቤተ ልሔም ጊዜያዊ ጽርሐ አርያም ሁና መላእክት ዘመሩባት ። በትንሣኤው መላእክት በምድር ምስክርነት ፣ በሰማይ ምስጋና አሰሙ ። አምላኩን በመግደሉ በሰው ደንግጦ የነበረው ፍጥረት በትንሣኤው ተረጋጋ ። ሰውን ፈርቶ የነበረው የምድርና የሰማይ ሠራዊት ለሰው በተከፈለው ዋጋ ሰው ትልቅ ነው አለ ። ሞት እንደ እንቅልፍ ፣ ቋጥኝ እንደ ጠጠር ፣ ወታደሮች እንደ ሕፃናት ፣ ወርቅና ገንዘብ እንደ ዝገት ፣ ጉልበት እንደ ውድቀት የሆነባት ያች የክርስቶስ ትንሣኤ ቀን ምንኛ ትደንቅ ! ክርስቶስን ለማሥነሣት የመጣ መልአክ የለም ፣ ክርስቶስ መነሣቱን ለማብሰር ግን መልአክ መጥቷል ። በዳግም ምጽአት ሙታን ይነሡ ዘንድ የመለከት ድምፅ የሚነፋው ያ መልአክ ነው ። ትንሣኤው ትንሣኤያችንን ካላስታወሰ ክርስቶስ በከንቱ ተነሣ ይባል ነበር ። መግደላዊት ማርያም አምላኳን እንደ ሳለችው ሳይሆን እንደ ራሱ አገኘችው ። ለሕያውነቱ የሚወርደውን የመላእክትን ምስጋና ስትሰማ ለሙታን የሚሆነውን ሽቱ ጣለችው ። ደስታ የሚጥል ቢሆንም የእግዚአብሔር ደስታ ግን የሚያቆም ነው ። ደስታችንን እንቋቋም ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ይደግፈናልና ። መግደላዊት ማርያም ፀናች ። ብሥራቱን በመልአክ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሰማች ፣ ትንሣኤውንም መልአክ ለመግደላዊት ማርያም አበሰራት ። ብሥራቱ ለተቀደሰችው ለቅድስተ ቅዱሳን ለድንግል ማርያም ተነገረ ፣ ትንሣኤው ወድቃ ለተነሣቸው መግደላዊት ማርያም ተሰበከ ። ድንግል ማኅፀኗን ያድርበት ዘንድ ተበሠረች ። መግደላዊት ማርያም ያደረበትን መቃብር ታይ ዘንድ ተጋበዘች ።
ነገሥታት ግብዐ መሬታቸው ሲፈጸም መድፍ ይተኮሳል ፣ ክርስቶስ ግን ነፍሱን ሲሰጥ ምድር ተናወጠች ። የያዘቻቸውንም ሙታን ተፋች ፣ ብዙ ቅዱሳንም ተነሡ ። ነገሥታት ጉዞ ሲጀምሩ የደስታ መሣሪያ ይተኮሳል ። የነገሥታት ንጉሥ ክርስቶስ ሲነሣም ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ ። በንጉሡ ፊት ወታደሩ እየቀደመ ንጉሥ መምጣቱን ያበሥራል ፣ መልአኩም ትንሣኤን አበሰረ ። ሙትልን የማይሉት ብዙ ቅዱሳን ሳሉት ለእኛ መሞቱ ይደንቃል ።መላእክት ዓርብ ዕለት ተደነቁ ፣ እኛ እሑድ ዕለት ተገረምን ። የሕይወት ባለቤት ሲሞት መላእክት አረመሙ ። ሞት ድል ሲነሣ የሰው ልጆች ተገረሙ ። ርኩሳን ሰዎች የዘበት ስግደት ዓርብ ዕለት ያቀረቡለትን መላእክት በሰው ዓለም ላይ ቆመው ሰገዱለት ። ጎልጎታ ከሰማይ በልዩ አትኩሮት ትታይ ነበር ። ጥቂት ሴቶች የተገኙበትን መቃብር እልፍ አእላፋት ወትእልፊት የሚሆኑ ቅዱሳን መላእክት ከሰማይ በጽሞና ያዩ ነበር ። ዓርብ ዕለት ቢቀየሙን ኑሮ መላእክት እሑድ ዕለት አይመጡም ነበር ። የጌታቸው ይቅርታ ወርሶአቸዋል ። የወዳጅ ልጅን ማየት በጣም ደስ ይላል ፣ ሰው በተፈጠረ ጊዜም የእግዚአብሔር ወዳጆች መላእክት አዳምን ወደውት ነበር ። ሰው በዋጋ ተፈጥሮ ያለ ዋጋ በሞተ ጊዜ አዘኑ ። ትንሣኤውን ሲያዩ ግን የወዳጃቸው ልጅ እንደሚነሣ ፣ የሰው መጨረሻ ሞት እንዳልሆነ በማሰብ እፎይ አሉ ። በአንድ ኃጢአተኛ መመለስ በሰማይ የሚዘምሩ መላእክት ለኃጢአተኞች ሁሉ በተከፈለው ዋጋ በትንሣኤው ደስ ቢላቸው የሚጠበቅ ነው ። መላእክት ወዳጆቻችን ናቸው ። ሰይጣን ጠላታችን ነው ስንል የምንውል ፣ መላእክት ወዳጆቻችን መሆናቸውንም መናገር አለብን ።
ሰው የሚከብረው በእግዚአብሔር ነው ። ይድን ዘንድ እግዚአብሔር ወልድ ሥጋንና ነፍስን ከድንግል ነሣ ። አሁንም በትንሣኤ ሥጋው ሲነሣ ፣ በነፍሱ ወደ ሲኦል ወርዶ ነፍሶችን ሲማርክ የሰው ሥጋና ነፍስ በድል ሽቱ ታወደ ።መቃብር  መወርወሪያውና ቁልፉ ተሰበረ ። መቃብር የታተመ ሳይሆን እስከ ምጽአት ገርበብ ያለ በር ሆነ ። ለዘመናት እስር ቤት በር አለው ፣ መቃብር ግን በር የለውም ሲባል ኖረ ፣ ዛሬ ግን በክርስቶስ ትንሣኤ መቃብር በር አገኘ ። ዓለም ክርስቶስን ስትሰቅል ቀኑ ጨለመ ፣ ክርስቶስ ሲነሣ ሌሊቱ በራ ። በታሪካችንና በምርጫችን እርሱን ስንሰቅለው ቀኑ ይጨልማል ፣ የሚቻል ነገር የማይቻል ይሆናል ፣ የመጣውም ይርቃል ። ክርስቶስ ሲነሣ ደግሞ የአገር ጽልመት ይገፈፋል ፣ የትውልድ ውድቀት ትንሣኤ ያገኛል ። መግደላዊት ማርያም አንድ ነገር እያሰበች ወደ መቃብሩ ትገሰግሳለች ። ትንሣኤው ግን ብዙ አስተንትኖ ይዟል ። ዘማሪዋ እንደ ዘመረችው ነው፡-
እዩት ኢየሱስን መስቀሉ ማማሩ ፣
ለተመራመረው ብዙ ነው ምሥጢሩ ።
ይቀጥላል
የመስቀሉ ገጽ 8 ሀ
ሚያዝያ 20 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ያጋሩ