የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ረቢኒ /5

 ትንሣኤ ላይ ሴቶችና መላእክት ይታወሳሉ ። የተዘነጉ ሲሆኑ ድርሻቸው ትልቅ ነው ። ጌታ ሲነሣ አብረው እንዲነሡ አደረገ ። መግደላዊት ማርያም በአካል ባላገኘውም ፍቅሩን አስታውሳለሁ ብላ ፣ ወደፊት ይህን አድርግልኝ ባልለውም ያደረገልኝ በቂ ነው በማለት ወደ መቃብሩ ገሰገሰች ። ክርስቶስ ግን ሞት ድንበሩ አይደለም ። ከሞትም የሚጀምር የትንሣኤ አምላክ ነው ። አካሉም ፍቅሩም ሕያው ነው ። ገና ሊሰጠንም ያኖረናል ። እርሱ በስጦታውና በፍቅሩ ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው ።
ምድር የከዳችውን ፣ መሬትን ያረክሳል ተብሎ ከፍ አድርገው መስቀል ላይ ያንጠለጠሉትን ዮሴፍ ዘአርማትያስ ፍልፍል መቃብሩን ለቀቀለት ። ጌታችን በዮሴፍ ቤት እንደ ተስተናገደ አልተጻፈም ፣ በመቃብሩ ውስጥ ግን ሦስት ቀን አደረ ። በእስራኤላውያን ባሕል መቃብር ትልቅ ዋጋ አለው ። ዛሬ በታወቀ የአይሁድ መቃብር ለመቀበር በሚሊየን የሚቆጠር ዶላር ለአንድ መቃብር ይከፈላል ። ዮሴፍ ዘአርማትያስ ይህን ለጌታ ተወለት ። በቁም ብዙ ጋባዦች ነበሩ ፣ ዛሬ አልተገኙም ። ማንም በማይገኝበት ቀን የተገኘ ፣ ማንም በማይሰጥበት ቀን የሰጠ ዮሴፍ ዘአርማትያስ ነው ። ክርስቶስን እንዲህ ሲወዳጀው ጠላት ይነሣብኛል ብሎ አልፈራም ። በሁሉ ቦታ ክርስቶስ ወዳጅ አለውና ከአይሁድ ሸንጎ ሰባ አባላት ካለው ፍርድ ቤት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ የክርስቶስ ወዳጆች ነበሩ ። ዮሴፍ በአዲስ መቃብር ክርስቶስን ቀበረው ። እርሱ ማንም ባልተቀመጠበት ማኅፀን ያደረ ነው ፣ ማንም ባልተቀበረበት መቃብርም ተቀበረ ። በዚያ ማኅፀን ከዚያ በኋላ ፍጡር አልተቀመጠም ፣ በዚህ መቃብርም ፍጡር አላረፈም ። በእግዚአብሔር ዙፋን ፍጡር አይቀመጥም ። የቁምም የሞትም ወዳጅ መሆን የማይችሉ ምስኪኖች ናቸው ። ትምህርት በከንቱ አይሰጥም ። ኒቆዲሞስና ዮሴፍ በስውር ተምረው በግልጥ መሰከሩ ። የከበበ ሲበተን ተገኙ ። ብቻ ፈሪዎችንም እንደ አቅማቸው በድብቅ አስተምሩ ፣ አንድ ቀን ጎበዝ ሲፈራ እነርሱ ይደፍራሉ ።

ዮሴፍ መቃብሩን ለጌታው ለቀቀ ። ከዚያ በኋላ ወደ መቃብሩ አልተመለሰም ። መግደላዊት ማርያም ግን ሽቱ ይዛ በሦስተኛው ቀን ተመለሰች ። ወንዶች የመጨረሻው ሰዓት ላይ ቢገኙ አስታውሰው መሄድ አይሆንላቸውም ። ሴቶች ግን ሲያስቡ ይኖራሉ ። አካልን እንጂ ትዝታንም መቅበር ፣ ሥጋን እንጂ ሥራን መቅበር አይገባም ። በዚህ ዓለም ላይ ሁሉም ነገር ሲሞት ጥሩ ትዝታ ይኖራል ። የሞቱት ትዝታቸው ያዋራናል ።
የክርስቶስ ትንሣኤ መንግሥት ፈርሶ መንግሥት የጸናበት ነው ። የዲያብሎስ መንግሥት ፈርሶ የእግዚአብሔር መንግሥት በሰው ሥጋና ነፍስ የሰለጠነበት ነው ። መንግሥታት ሲዋጉ ያለውን ትርምስ መግደላዊት ማርያም አታውቅም ነበር ። በምናውቀው ነገር ውስጥ ብዙ የማናውቀው ነገር አለ ። በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ስላለው ምሥጢር እውቀታችን አነስተኛ ነው ። አለማወቃችን ግን የመጠቀም ዕድላችንን አይነፍገንም ። ቴሌቪዥን እንዴት እንደሚሠራ ብዙዎቻችን እውቀቱ የለንም ። አለማወቃችን ግን እንዳንጠቀም አያደርገንም ።
ክርስቶስን መግደል ራስን በፈቃድ ለዲያብሎስ መንግሥት አሳልፎ መስጠት ነው ። ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት ማርያም ግን ያንን ክፉ ኑሮ ስለምታውቅ እንደገና መቀለድ አልፈለገችም ። አዲሱን ሕይወት አክብራ ያዘች ። ፈርዖን ከለቀቀ በኋላ ተከታትሎ ለመያዝ ይመጣል ። በእምነት ካልተሻገርን ይይዘናል ። ከፊተኛው የኋላው ቀንበር ይከብዳል ። ያላዩ በእሳት ለመጫወት ይደፍራሉ ። ሰይጣን ክፉ ገዥ ነው ፣ የሚያመልኩትን እንኳ የሚያስጨንቅ ነው ። አዋርዶ የሚገዛ ክብር የለሽ ነው ።
ጌታችን ሲነሣ የተገነዘበትን ጨርቅ ትቶ ተነሥቷል ፣ ልብሱን ደግሞ በመስቀሉ ሥር ወታደሮች ዕጣ ተጣጥለው ወስደውታል ። በትንሣኤ የለበሰው ልብስ የብርሃን ልብስ ነው ። የብርሃን ልብስ የማይወልቅ ቀሚስ ነው ። እርሱ ብቻውን አልተነሣም ፣ ብዙ ሙታንን ይዞ ተነሣ ። ቤት ለቤት እየሄዱ ትንሣኤን እንዲሰብኩ ክርስቶስ አሥነሣቸው ። ሞትን ያዩ ቍጣን አይፈሩም ።
ወደ መግደላዊት ማርያም እንገሥግስ ። ትንሣኤ በር ዘግቶ ፣ ምሥጢሩ አላሳልፍም አለን ። የክርስቶስ ትንሣኤ ሆይ እባክህን መንገድ ልቀቅልን ። የማታልቅ ትንታኔ ሆይ ፣ ሞትን ያሸነፍህ የእግዚአብሔር ክንድ ሆይ በትንሽ ጭንቅላት ትልቅ ምሥጢርን ማሰስ አንችልምና ለማለፍ ፍቀድልን ።
ከሞታችሁ ከሦስት ቀንም በኋላ የሚወዳጃችሁ ወዳጅ ብታገኙ ደስ ይላችኋል ። መግደላዊት ማርያም ከሦስት ቀንም በኋላ ወዳጅ ነበረች ። ሽቱ ክቡር ነው ፣ ያለ ሰዓቱ ከሆነ ግን የሚጣል ነው ። ሰዓትን ማወቅ ከሽቱ በላይ ነው ። ብዙዎች ሽቱ ይዘዋል ፣ ሰዓቱ ግን አልፏል ። ፍቅራችሁን ለመግለጥ ፣ የተዘረጉላችሁን እጆች ዛሬ ለመሙላት ፣ ያሳደጉአችሁን ለማድነቅ ሰዓቱ አሁን ነው ። ተጠቀሙበት ። ለሽቱ እንጂ ለሰዓት ዋጋ ለምን አትሰጡም ?  ሴቶች ሞቶም እንዲህ የወደዱት ቢነሣ እንዴት ይወዱት ይሆን ? ሞቱን ያመኑ ሴቶች ትንሣኤውን ማመን አልቻሉም ። ሞት የሰው ሁሉ ዕጣ ነው ፣ መሞት ችሎታ አይጠይቅም ። ትንሣኤ ግን ችሎታ ይጠይቃል ። ሞትን አምኖ ትንሣኤን አለማመን ከባድ ነው  ። የሚገርመው እኛ ሞትንም ትንሣኤንም አለማመናችን ነው ። የምንሠራው ክፋት ሞት እንዳለብን የዘነጋን ያስመስልብናል ። ነገሮች ሲሞቱ እግዚአብሔር እንደሌለ ያህል የሚሰማን ትንሣኤን አለማመናችንን ያሳያል ። ክርስቶስ ሲቀበር የእነ መግደላዊት ማርያም ተስፋም አብሮ ተቀብሮ ነበር ። ሞት ፣ ድንጋይ ፣ ወታደሮች ይታሰቡአቸው ነበረ እንጂ ሕይወት ፣ መልአክ ፣ ብሥራት አልታሰባቸውም ነበር ። የእምነታችንን ያህል ሳይሆን የታማኝነቱን ያህል ስለ ሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይገባዋል   ።
የሰው ኀዘን በትንሹ ይረጋጋል ። ቅዱስ ሥጋውን ሽቱ ከቀቡ በኋላ ለመጽናናት ፈልገዋል ። ከስንብት በላይ ትንሣኤ ያረጋጋል ። የእኛ ኀዘንም በትንሹ ይጽናናል ። ድሀው ሲያሳዝነን ፣ እጅ እግሩ የተቆረጠው ሰው ሲያራራን አሥር ሣንቲም ስንጥል እንረጋጋለን ። ኀዘናችን ሰውዬውን አንድ ቦታ አድርሶ ሳይሆን ድቃቂ ሣንቲም ጥሎ ይረጋጋል ። ወትሮም የምንሰጠው ሕሊናችንን ፀጥ ለማሰኘት እንጂ ለወደቀው ሰው አዝነን አይደለም ።
ታሪክ ያለመደው ፣ ምድራዊ ሥልጣንና ሀብት ያልቻለው አንድ ነገር ቢኖር የክርስቶስ ከሞት መነሣት ነው ። እነ ፈርዖን ፣ እነ ናቡከደነፆር ፣ እነ ዳርዮስ ፣ እነ እስክንድር ፣ እነቄሣር እንደ ሞቱ ቀርተዋል ። እነ ሶቅራጥስ ፣ እነ ፕላቶን ፣ እነ አርስቶትል ፣ እን ፊሎ በመቃብር እንደ ተዘጉ ይኖራሉ ። ታሪክ ያለመደውን ነገር እነ መግደላዊት ማርያም መቀበል ፣ ለነገሥታትና ለጠቢባን ያልተቻለውን አማን አማን ማለት ከበዳቸው ።
ድንጋዩን ማን ያንከባልልልናል ? ሲሉ ተንከባሎ አገኙት ። በዚህ አንዱ ጭንቀታቸው ቀለለ ። ክርስቶስ ተነሣ የሚለውን ብሥራት ለመቀበል ከበዳቸው ። ድንጋዩን ማን ያንከባልልልናል ለሚል ልብ ሞትም ተንከባሏል ብሎ መቀበል ከባድ ነው ። የክርስቶስ ሥጋ ተሰርቋል የሚል አሳብ አደረባቸው ። ክፉ ገዥዎች የሚፈሩትን ሰው ከገደሉት በኋላ መቃብሩ ተከታይ እንዳያፈራ ደብዛው እንዲጠፋ ያደርጋሉ ። ሴቶች እንዲህ የሆነ መሰላቸው ። ተሰርቋል የሚለው አሳብ በካህናት አለቆች በእነ መግደላዊት ማርያም አእምሮ ስፍራ አገኘ ። ሰይጣን አሳብ ይዘራል ፣ ሰው ሥጋ ያለብሰዋል ።
ሴቶች ባዶውን መቃብር እንዲጎበኙ በመላእክት አጋፋሪነት ተጠየቁ ። ባዶ መሆኑ አስደነገጣቸው ። ቅዱስ አካሉ ተኝቶ ሊያገኙት ፈልገዋል ። የመሰረቁ አሳብ ልባቸውን ገዛው ። መልአኩ ግን ተነሥቷል ብሎ አወጀላቸው ። መላእክትን እንዳይሞቱ አድርጎ የፈጠረው እርሱ በሥጋ ሞተ ። በሥጋ ሞተ ። በመለኮቱ ቢሞትማ አይነሣም ነበር ። የምንነሣው ከሞት ቀጥሎ ትንሣኤ ስላለ ሳይሆን አምላካችን የማይሞት ስለሆነ ነው ።
ትንሣኤ ማንንም የማሳቀቅ ዓላማ የለውም ፣ ዓላማው የወደቁትን መፈለግ ነው ። ስለዚህ ይህን ዜና አስቀድመው ለጴጥሮስ እንዲነግሩ ፣ ወደ ካደው ሰው ተላኩ ። ትንሣኤ የካደውን ጴጥሮስ ፣ አሳዳጁን ጳውሎስ ገንዘብ ያደረገ ነው ። ክርስቶስ ባይነሣ እነዚህን ሁለት ዕንቁዎችን ቤተ ክርስቲያን አታገኝም ነበር ። የትንሣኤው የምሥራች በመላእክት ፣ በሴቶች ቢሰበክም በሐዋርያት ቀጣይነት ያገኛል ።
መግደላዊት ማርያም መቃብሩ ባዶ መሆኑን ከተናገረች በኋላ  ጌታዬን ወስደውታል እያለች ትጨነቅ ነበር ። ክርስቶስ ተነሥቷል ብለው ከሰበኩ በኋላ ለሚጨነቁ ምሳሌ ናት ። ሰብካችሁ ለምትጨነቁም ክርስቶስ ተነሥቷል ። እንኳን ደስ አላችሁ ። በትንሣኤ የብርታት ድምፅ እንጂ የመፈራረድ ቋንቋ የለም ።
ይቀጥላል
የመስቀሉ ገጽ 8 ሠ
ሚያዝያ 24 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ያጋሩ