የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ርስተ መንግሥተ ሰማያት

“እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ እንደ እርሱ አሳብ ፥ አስቀድመን የተወሰንን በክርስቶስ ደግሞ ርስትን ተቀበልን ።” ኤፌ. 1፡10 ።

የፈቃዱ ምሥጢርነት ሁሉን የፈጠረው የሁሉ አዳኝ ተብሎ የሚጠራበት ነው ። ሁሉን ያዳነው ሁሉን ምስጋናና ክብር ጠቅልሎ የሚመሰገንበት ነው ። የፈቃዱ ምሥጢር ለሚያምኑ የተገለጠ ደግሞም የሚያስደንቅ ነው ። ላላመኑ ግን ግልጽ የሚመስል ነገር ግን ስውር የሆነ ነው ። ያመኑትም ሁልጊዜ በመደነቅ የአምልኮ ግብር የሚያቀርቡበት ነው ። ለምድር ነገሥታት ግብር ሲቀርብ አስጨናቂ ነው ፤ በመደነቅ የሚገበርለት ግን እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ግብሩም ከየት አመጣዋለሁ የማይባል ሁሉም ሰው ሊያቀርበው የሚችል የልብ እምነትና የአንደበት ምስክርነት ነው ። የምላስ ምስጋና ፣ የጉልበት መንበርከክ ግብሩ ነው ። እግዚአብሔር የገዛ አካላችንን የአምልኮ መሣሪያ አድርጎ ሰጥቶናል ። ሰው ለማምለክ አቅም የለኝም ማለት አይችልም ። ለማምለክም ፈተና አለብኝ ማለት ተቀባይነት የለውም ። ሰው አምልኮን የሚያስቀረው በዓመፃ መሆኑን መገንዘብ አለበት ። በዚህ ምክንያት ከኃጢአት ሁሉ የሚከፋው ኃጢአት እግዚአብሔርን አለማምለክ ነው ። የፈቃዱን ምሥጢር ሁልጊዜ ማስተዋል ይገባናል ። ቀራንዮ ለአማንያን የኀዘን ብቻ ሳይሆን የደስታም ኮረብታ ነው ። ያለ በደላቸው የሞቱ ሰዎችን ዜና ስንሰማ ልባችን ያዝናል ። የንጹሖች ንጹሕ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመዋሉ እናዝናለን ። ደግሞም ሞቱ ባለ ፍሬ ነውና በትንሣኤው እንደሰታለን ። የተነሣው እኛን ይዞ ነውና ። ሞታችንን ሰጠነው ፣ ትንሣኤውን ሰጠን ። ዕፀ በለስ በልተን ሞትን ኅብስተ ሕይወት ክርስቶስን በልተን እንድናለን ። በእባብ ሥጋ በተሰወረ ሰይጣን ወደቅን ፣ የሰውን ሥጋ በለበሰ ክርስቶስ ዳንን ። እርሱ ከእኛ ጋር ለመሞት ፈቀደ ፣ ከእርሱ ጋር ለመነሣት የበቃን ሆንን ። አንድ ንጉሥ እደሀ ሰፈር ወርዶ ሲወጣ እነዚያን ድሆች ባለጠጋ አድርጎ ነው ። እስር ቤትም ሲወርድ ብዙ ሰዎችን ፈትቶ ይመለሳል ። ክርስቶስም ሲኦልን በዝብዟል ።

እናታችን ባታምጥ ኖሮ አንወለድም ነበር ። የመስቀል ምጥ ባይኖርም ክርስቲያን አንሆንም ነበር ። ብቻ ቀራንዮ የሌለው ጎልጎታ ፣ ጎልጎታ የሌለው ቀራንዮ የለም ። ቀራንዮ ሞት ፣ ጎልጎታ ትንሣኤ ነው ። ቀራንዮ ጎልጎታ ያስፈልገዋል ። በሰውነቱ ሞተ ፣ በአምላክነቱ ተነሣ እንላለንና ። ከእኛ እንደ አንዱ ሆነና ሞተ ፣ ከሥላሴ እንደ አንዱ ነውና ተነሣ ። መለኮት በሥጋ ባይሞት ሞቱ ድንቅ አይባልም ፣ ሰው መሞቱ እርግጥ ነውና ። ሥጋም በመለኮት ባይነሣ ትንሣኤው ለእኛ አይተርፍም ነበር ። የሞተውም እርሱ የተነሣውም እርሱ ነው ። በአገራችን አንድ ንጉሥ ሲሞት ወዲያው አልጋ ወራሹ ይሰየማል ። በአንድ ጊዜም ሞትና ንግሥና ይታወጃል ። “የሞትነውም እኛ ፣ ያለነውም እኛ ባለህበት ዕርጋ” ይባላል ። የሞተውም ያለውም አንዱ ክርስቶስ ነው ። ቀራንዮ ጎልጎታ ያስፈልገዋል ፣ አሊያ አዝኖ መቅረት ይሆናል ። ጎልጎታም ቀራንዮ ያስፈልገዋል ፤ ይህም መዳን ቀላል መስሎ እንዳይታይ ያግዛል ።

“እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ” ይላል ። እግዚአብሔር ሁሉን የሚሠራ ብቻ ሳይሆን በሁሉ የሚሠራም ነው ። ሁሉን የሚሠራ ሲባል የሁሉም ነገር መነሻ ነው ማለት ነው ። በዚህም የአልፋነቱ ምስጋና ጸንቶ ይኖራል ። በሁሉ የሚሠራ ስንም ሀብታም ድሀ ፣ ሊቅ ደቂቅ ሳይል በሁሉ ራሱን ይገልጣል ማለት ነው ። ሁሉን የሚሠራ መሆኑን ማመን በእርሱ ለማረፍ ይረዳል ። በሁሉ የሚሠራ መሆኑን መቀበል ሰዎችን ለማክበር ይረዳናል ። አህያንም እናከብር ዘንድ አህያ በለዓምን ገሥጻለች ። ድንጋዮችም አመስግነዋልና ፍጥረትን ማክበርና መንከባከብ ይገባናል ። አህያ ብሎ የሚሳደብ አህያ ጌታን የተሸከመች መሆኗን የማያውቅ ኢክርስቲያን ብቻ ነው ።

“ፈቃዱ” ይላል ፣ ፈቃዱ ውሳኔው ሲሆን ምክሩ ግን መነሻው ነው ። ምክረ ሥላሴ ዕፁብ ነው ። መጀመሪያ ላይ ሆኖ መጨረሻን የሚያውቅ ፣ ትላንት የሚባል ያለፈ ቀን ፣ ነገ የሚባል መጪ ቀን የማይቀጸልለት እግዚአብሔር ይመክራል ስንል ለእኛ ያለውን ዘላለማዊና የከበረ አሳብ ለመግለጥ ነው ። በትላንት ስህተት ፣ በነገ ሰቀቀን ውስጥ የምንኖር እኛማ ምክር ያስፈልገናል ። ከእግዚአብሔር ጋር ፣ ከራሳችን ጋር ፣ ከወዳጆችና ከአባቶች ጋር መምከር ያስፈልገናል ። አለመመካከር የሚያጸጽተውን ያህል መመካከር አያጸጽትም ። በመመካከር ውስጥ ነገሮች ቢበላሹ እንኳ ውድቀቱ አጽናኝ አለው ።

የተማከሩት ነገር ድጋፍ አለው ። እኛ እግዚአብሔርን ከማሰባችን በፊት እግዚአብሔር እኛን አስቦናል ። እግዚአብሔር ማንንም ለኵነኔ ወሰነ ተብሎ አንድም ቦታ አልተጻፈም ። ለጽድቅ እንደ ወሰነን ግን ተጽፎአል ። መረጠን የሚል ቃል ስናገኝ ያልተመረጡ አሉ ብለን በሥጋዊነትና በግራ ዘመም አስተሳሰብ ስለምናስብ ነው ። እግዚአብሔር መረጠ ስንል ሁሉንም መርጦአል ፣ ሰው ግን በፈቃዱ ሊቀር ይችላል ማለት ነው ።

እኛን ለጽድቅ መወሰኑ ከዘላለም ነው ። በዚህም ርስተ መንግሥተ ሰማያትን ፣ ሀገረ ሕይወትን አግኝተናል ። ርስትን ለማግኘት የሚያስፈልገው ልጅ መሆን ነው ። ውሉደ እግዚአብሔር መሆን ለርስቱ ያበቃናል ። መንግሥተ ሰማያትን በልጅነት የምትገኝ ርስት አድርጎ የሰጠን ድካማችንን ያየ አምላክ ነው ። በምድር ላይ ርስት ባይኖረን እንኳ በሰማይ ግን ርስት ተዘጋጅቶልናል !

የኤፌሶን መልእክት ትርጓሜ /20

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 7 ቀን 2014 ዓ.ም.

ያጋሩ