የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ…. ሰኔ ፲፩/ ፳፻፮ ዓ/ም
ከተራ ሽፍትነት አንሥቶ እስከ ደጃዝማችነት ከዚያም እስከ ዐፄነት ቴዎድሮስን ያልተለዩ፣ በዝቅታና በከፍታ ያልተቀያየሩ፤ ሴትነትን ከጀግንነት፣ ሚስትነትን ከአፍቃሪነት፣ ሠራተኛነትን ከባለሙያነት ጋር አስተባብረው የያዙ እቴጌ ተዋበች ከሞቱ በኋላ ዐፄ ቴዎድሮስ በጭካኔ እየበረቱ፣ በብቸኝነት እየተወጉ መኖራቸው በብዙ ይነገራል፡፡ እቴጌ ተዋበች በጓዳ የንጉሡ አማካሪ፣ በጦርነት የድፍረት ድምፅ ነጋሪ፣ ያልተገባ ምክርንና አመልን ሻሪ ነበሩ፡፡ ንጉሡንም ያረጋጓቸው፣ ወደ በለጠውም ራእይ ይገፏቸው ነበር፡፡ ሰው ቤቱ ከተገዛለት አገር ይገዛለታል፡፡ ይህን የምናየው ከዐፄ ቴዎድሮስ ነው፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ ሚስት ብቻ ሳትሆን እናታቸው የነበረችውን እቴጌ ተዋበችን ካጡ በኋላ በነጻ የሚያፈቅራቸው፣ ከቊጣ የሚያበርዳቸው እንዳጡ ብዙ ተነግሯል፡፡
ሰው የሚወደኝ የለም ብሎ ባሰበ ጊዜ ጥፋቶችን ያበዛል፡፡ ሰውን ከክፉ ሥራው የሚገታው የወዳጁ ልብ በእርሱ ስህተት እንደሚሰበር ባሰበ ጊዜ ነው፡፡ ይልቊንም በሥልጣን ላይ ያሉ እነርሱነታቸውን የሚወድ እውነተኛ አፍቃሪ ለማግኘት ይቸገራሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ከእቴጌ ተዋበች በኋላ የዐፄ ቴዎድሮስ ሚስት የነበሩት እቴጌ ጥሩ ወርቅ ከንጉሡ ጋር የኖሩት በግድና በፍርሐት እንጂ በውድና በፍቅር አልነበረም፡፡ እቴጌ ተዋበች ግን እውነተኛ አፍቃሪ፣ ገመና ከታች ነበሩ፡፡ ታዲያ የሚወዱት ሁልጊዜ አይኖርምና እቴጌ ተዋበች ይህችን ዓለም በሞት ተሰናበቱ /ሞት ለሁሉም አይቀርም ለእነ አመተም ለእነ እቴጌም/፡፡ እቴጌ ተዋበች በመሞታቸው ብርቱ ሀዘን የወጋቸው ዐፄ ቴዎድሮስ እንዲህ በማለት የሀዘን ቅኔ አሰሙ፡-
“እስቲ ጠይቁልኝ ርቃ ሳትሄድ
እቴጌ ተዋበች ሚስት ናት ገረድ”
የሀዘኑ ቅኔ ሰሙ እቴጌ ተዋበች እንደ እኩያ ሚስት ብቻ ሳይሆኑ እንደ ታዛዥ ገረድም ትሑት መሆናቸውን ይገልጣል፡፡ ወርቁ ግን እቴጌ ተዋበች የሦስት ስጦታዎች ባለቤት መሆናቸውን ያብራራል፡፡ ይኸውም፡- ሚስት፣ እናት፣ ገረድ እንደነበሩ ያትታል፡፡ በርግጥም እቴጌይቱ ለዐፄ ቴዎድሮስ ይህን ሁሉ ነበሩ፡፡ ሚስት አካል፣ እናትም ገመና ሸፋኝ፣ ገረድም መጋቢ ናት፡፡ እቴጌ ተዋበች የፍቅር ሰው ስለ ነበሩ ሦስቱንም መሆን አልከበዳቸውም፡፡ ፍቅር ላለው ሁሉም ነገር ቀላል ነው፡፡
የፍቅርን አሻራ በአፍቃሪዎች ላይ እናገኘዋለን፡፡ ፍቅር ረቂቅ ነው፣ በአፍቃሪዎች ላይ ግን ገዝፎ ይታያል፡፡ ራሷ ፍቅር እንደ ሚስት አካል፣ እንደ እናት ገመና ሸፋኝ፣ እንደ ገረድ ትሑትና ታዛዥ ናት፡፡ የሕይወት ሰሌዳ ሁለት ዓይነት ነው፡፡ አንደኛው ገጽ ጥቁር፣ ሁለተኛው ገጽ ነጭ ነው፡፡ በፍቅር የኖርንበት፣ ለፍቅር አልሰማም ብለን የሞትንበት የሕይወት ዘመን አለን፡፡ ፍቅር ለእኛ ብዙ ባለ ውለታችን ናት፡፡ ዕድሜአችን የተቀጠለባት፣ ከቂም ሥቃይ የተፈወስንባት፣ መሥዋዕትነትን የተለማመድንባት፣ ጀግና ተብለን የተጠራንባት፣ እግዚአብሔርን ያየንባት፣ ክርስቲያን የሆንባት፣ ታላላቆቻችንን ያከበርንባት፣ የሌላውን ስምና ንብረት የጠበቅንባት፣ ቅንዓትና ምቀኝነትን ያራቅንባት፣ ኃይለኞችን የማረክንባት፣ ከመጥፎ ውሳኔ የዳንባት፣ የመኖር አምሮታችን የጨመረባት … ናት፡፡ ወደ ኋላ ዞር ብለን ስናይ ትዝታዋ የሚፈውሰን ፍቅር፣ ዘርና ቀለም ሳንለይ ሁሉን የተቀበልንባት መዋደድ ዛሬ ግን ለእኛ ሞታብን እንደ እቴጌ ተዋበች በቃሬዛ እየወጣች ነው፡፡ ቅኔ አልቋልና የዐፄ ቴዎድሮስን ቅኔ፣ የኖረውን ሙሾ ለዛሬ ብናንጎራጉር እንዴት መልካም ነው፡-
“እስኪ ጠይቁልኝ ርቃ ሳትሄድ
እቴጌ ፍቅር ሚስት ናት ገረድ”
ፍቅር ሚስት ናት፡፡ ሚስት አካል ነች፤ እናትና አባት የሚወዱን ስጦታዎቻችን ናቸው፡፡ ሚስት ግን የራስ የሆነች ሀብት ሳትሆን ሰውዬው ሌላኛው እኔ ብሎ የሚጠራት፣ በመንፈሳዊና በአካላዊ እውነት አንድ የሆነች ናት፡፡ ፍቅርም አካል ነች፡፡ የተፈጠርንባት ምክንያት፣ የምንኖርባት ኃይል፣ የምንወርሳት መጪዋ መንግሥት ናት፡፡ ያለ ፍቅር መኖር አይቻልም፡፡ ራስን እንደ ማጣት ነው፡፡ ኑሮና እሴትም ያለ ፍቅር ጣዕም የላቸውም፡፡
ፍቅር ገመናን ሸፋኝ እናት ናት፡፡ እናት ልጃüን እየገሰጸች፣ በደጅ ግን መልካምነቱን እንደምትናገር ደግሞም በመለወጡ ተስፋ እያደረገች ዋጋ የለውም ከሚሉት ሰዎች ጋር እንደምትታገል እንዲሁም ፍቅር እንደ እናት ገመናን ሸፋኝ፣ የማንንም ነውር በማውጣት የማትረካ፣ ለባለቤቱ ስህተቱን ለሌሎች መልካምነቱን የምትናገር ናት፡፡ ዕድሜ የለውጥ ዕድል ነውና ሰው እንደ ትላንቱ ይሆናል ብላ ፍቅር አታምንም፡፡ ከጨለማው በኋላ ጨለማ ይመጣል የሚል አሳብ የላትም፡፡ ከሌሊት በኋላ ቀን፣ ከጭጋግም በኋላ ብርሃን፣ ከጎርፍም በኋላ ፀጥታ እንደሚሆን ፍቅር ታምናለች፡፡
ፍቅር በፈቃዷ ራሷን ባሪያ ታደርጋለች፡፡ ጌታችን የፍቅር መምህር ሳይሆን ራሱ ፍቅር ነበረ፡፡ እርሱ የጌትነት ዙፋኑን ትቶ ከአንዲት ንጽሕት ድንግል መወለዱ፣ ሰማይን ጥሎ በበረት ማደሩ፣ የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠቡ… ፍቅር ባሪያ እንደምታደርግ ያሳያል፡፡ ማንም ሳያስገድደው እንዲህ የሆነው ፍቅር ግድ ብሎት ነው፡፡ ፍቅር በዓለም ላይ ካሉት የጦር መሣሪያዎች ይልቅ የማስገበር አቅም አላት፡፡ ፍቅር በውስጣችን ስትገባም ለወደድነው ሰው ራሳችንን ታማኝ ሎሌ፣ ታማኝ ገረድ እንድናደርግ ግድ ትለናለች፡፡ ፍቅር በጌትነት ደስ ከሚላት ይልቅ በታዛዥነት ደስ ይላታል፡፡ በዙፋን ተቀምጦ ከማዘዝ ዝቅ ብሎ እግር ማጠብ ትወዳለች፡፡ ዘሬ፣ ቀለሜ፣ ቋንቋዬ፣ ትውልዴ፣ ሀብቴ … ከማለት ይልቅ እግዚአብሔርን ታከብራለች፡፡ ለመታረም ዝግጁ፣ ወንድሜ ከእኔ ይሻላል ለማለትም ትሑት ናት፡፡
በእውነት የቀድሞ ነገሥታት መገልገያ ዕቃዎች፣ ያለፈው ዘመን አሻራ ያለባቸው ቊሳቊሶች፣ ብዙ ምሥጢራትን የያዙ የብራና መጻሕፍቶች በሙዝየም መሆናቸው ያስደስታል፡፡ እንጀራ በሙዝየም ሊገባ ነው ቢባል ግን ማን ይደሰታል? የእንጀራን ያህል የሚያስፈልገን ፍቅር ሙዝየም እየገባ፣ የድሮ ፍቅር ተብሎ እየተጠራ ነውና በእውነት በሞት ቀጠና ውስጥ ነን፡፡ የእኛ የሀዘን ቅኔ፡-
“እስኪ ጠይቁልኝ ርቃ ሳትሄድ
እቴጌ ፍቅር ሚስት ናት ገረድ” የሚል ነው፡፡
የምንጨነቀው ራሳችንን ለማሳመን እንጂ እግዚአብሔር ምን ይላል? የሚለውን ለመተግበር አይደለም፡፡ በውስጣችን፡-
– ብቻ መኖር ጥሩ ነው፣ ከሰው ጋር ሲቀላቀሉ ጉዱ ብዙ ነው እያልን ይሆን?
– እኔ ብቻ ጠያቂ መሆን ሰለቸኝ ፍቅር የጋራ ነው በቃኝ እያልን ይሆን?
– እኔ ተቸግሬ ማን ዞር ብሎ አየኝ፣ ስለዚህ ለማንም ደንታ የለኝም እያልን ይሆን ?
– ድሮስ እገሌ ብሎ ዘር መቼ ጥሩ ነው እያልን ይሆን ?
– ትዳርና እጮኝነት ልዩነት አለው፤ ስለዚህ ተለያይቶ መኖር ከመቆሳሰል ይሻላል፡፡ ደግሞም ዘመናዊነት ነው፣ ፍቺውም በ45 ደቂቃ ያልቃል እያልን ይሆን ?
– ለማንም ምንም አልሰጥም፣ ዛሬ የገፈፉኝ ያለበስኳቸው፣ ዛሬ የበሉኝ ያበላኋቸው፣ ዛሬ የካዱኝ ያመንኳቸው ናቸው እያለን ይሆን?
– ለዚህ ዓለም የሚሻለው ክፉ መሆን ነው፡፡ የቤት ሠራተኛ እንኳ ደግ ሲሆኑላት አትወድም፡፡ ስለዚህ ደግነት ለሰው ስለማይገባው ጥቅም የለውም እያልን ይሆን?
የትኛው ያሸንፍ ተፋቀሩ ያለው የእግዚአብሔር አሳብ ወይስ የእኛ የወደቀ ጥናት? አንድ ሰው እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ምድር ፍቅር የተወሰደባት ቀን ሐውልት ትሆናለች፡፡››
እስቲ በየግላችን እግዚአብሔርን ይቅርታ እንጠይቅ፡፡ የተቋረጡ ግንኙነቶችን ለመመለስ፣ እንደ ዘመኑ ሳይሆን እንደ ቃሉ ለማሰብ እንፍቀድ፡፡ እግዚአብሔር ሆይ እባክህ አግዘን፡፡ ይህችን ዓለም ሕይወት አልባ ሐውልት እንዳናደርጋት እባክህ እየጠፋ ያለውን ፍቅር መልስልን፡፡ ስለ ዝናብ ድርቅ የሚጨንቀንን ያህል ስለ ፍቅር ድርቅ እንዲያሳስበን የሕመም ስሜት ስጠን፡፡
ወገኖቼ! ወስኑ፣ እግዚአብሔር በነጻ ወዷችሁ፣ በይቅርታ ተቀብሏችሁ፣ በምሕረቱ ብቻ አቁሟችሁ ሰዎችን ለመውደድና ለመቀበል መስፈርት አታብዙ፡፡ አንድ ሰው ፡- “በእኛና ዓለም በቃኝ እስር ቤት ባለው ሰው መካከል ያለው ልዩነት የእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ ነው” ብሏል፡፡ እግዚአብሔር ቸርነቱን አብዝቶልን እንጂ እኛም ያ የሚገባን ነበርን፡፡ ሁላችንን የሚያገናኘን ማዕከል የእግዚአብሔር ይቅርታ ብቻ ነው፡፡
“እስኪ ጠይቁልኝ ርቃ ሳትሄድ
እቴጌ ፍቅር ሚስት ናት ገረድ”