የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሰላም የሁሉ ጥማት

“መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን ፥ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ ፤ በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና ።” ኤፌ. 2፡17-18።

ጌታችን የመጣው በመልእክተኛ ፣ በነቢይ በመልአክ አይደለም ። ራሱ በታላቅ ትሕትና መጣ ። ራሱም የመጣው በረድኤት ፣ በተአምራት ፣ በሕልም በራእይ አይደለም ። የመጣው በሥጋ እንግድነት ነው ። ወደሚያስተዳድራትና ወዳልተለያት ዓለም ከዚህ በፊት ያልነበረውን ሰው መሆን ገንዘብ አድርጎ መጣ ። የመጣው በልዕልና ሳይሆን በትሕትና ነው ። የመጣው በባለጠጎች መልክ ሳይሆን በድሀ አምሳል ነው ። ሰው መሆኑንም እንዲመስለን የተደረገ ወይም ምትሐት ሳይሆን እርግጥ ነበረ ። አረማውያን የእኛ አምላክ አይሞትም እያሉ ሊነቅፉን ይሻሉ ። አምላክ አለመሞቱ የታወቀ ሐቅ ነው ። አምላክ ይገድላል መባሉም ተከታዩን ያስደስት ይሆናል ። የእኛ አምላክ ግን መግደል እየቻለ የሞተ ፣ ሞትንም ለሦስት ቀን ቀምሶ የተነሣ ነው ። ሥጋዌው እውነት ነውና ሰው ላይ የሚደርሰውን ሁሉ መቀበል ነበረበት ። መሞት የሰው ሁሉ ዕጣ ነው ። ሰው በመሆኑም ክርስቶስ ሙቷል ። እርሱ ኑ ያለ አምላክ ብቻ ሳይሆን ወደ እኛም የመጣ ነው ። የመጣውም ዘመድ ወገን ሁኖን ነው ። “ጥቂት ሥጋ ከመርፌ ትወጋ” እንዲሉ ስለ እኛ የሚቆረቆር ዘመድ ሁኗል ። “የዘመድ ቄስ እየፈታ ያለቅስ” እንዲሉ በመስቀል ላይ ሙቶ ሕይወትን የሰጠን ነው ። ልቅሶውም ፍትሐቱም አልቀረብንም ። አልዓዛርን ከሞት እንደሚያስነሣው እያወቀ አልቅሷል ። እንቢተኛይቱን ከተማ ኢየሩሳሌምንም ባያት ጊዜ የሚመጣውን ጥፋትዋን አስቦ አልቅሷል ። ሲፈውሰን አብሮን ታሞ ፣ ሲያድነን ሞቶልን መሆኑ ወዳጅነቱን ፣ የአፍቃሪቱን ጥግ ያሳያል ።

እኛ የነበርንበትን ቦታ ሊፈልገን መጣ ። በበረት መወለዱ በመንፈሳዊ ድህነት ፣ በቆሸሸ ታሪክ ፣ በእንስሳነት ግብር ተይዘን ነበርና በልደቱ ሊበዠን ነው ። የእርሱ መላ ሕይወቱ ለቤዛነት የተሰጠ ነውና ። በመስቀል ላይ ሲሞትም ሞት ተፈርዶብን ነበርና ጥልን ገድሎ ሊያድነን ነው ። በዓለም ላይ ያሉ ነገሥታት ጥልን ሳይሆን ጠበኛውን በመግደል ሰላምን ለምጣት ይሞክራሉ ። ጌታችን ግን ጥልን በመስቀል ላይ ገደለ ። በከፋፍለህ ግዛው የታወቁ የምድር ነገሥታት ባሉበት ዓለም ላይ ግድግዳን የሚያፈርሰው ንጉሥ ክርስቶስ በሥጋ ማርያም ተገለጠ ። መስቀል መሞቻ ብቻ ሳይሆን የውርደት ሞት መግለጫም ነው ። ሞታችን እንኳ ክብር ያልነበረው ፣ ተስፋ ሕይወትና ተስፋ ትንሣኤ ያጣ ነበር ። ጌታችን በመስቀል ላይ በመሞት ሞትን መንገደ-ሰማይ አደረገልን ። እኛ የነበርንበት ስፍራ በረትና መስቀል ብቻ አልነበረም ። መቃብር መውረዱን ስናስብ እንዲሁ ከመሬት በታች እንደ ተፈረደብን ያሳያል ። ጌታችን የመጣው ወደ መቃብራችንም ነው ። በመቃብር ላይም ትንሣኤ ሥጋን አወጀ ፣ መቃብርም ጊዜያዊ እንጂ ዘላለማዊ እስር ቤት መሆኑ አበቃ ። መቃብር በር የለውም ተብሎ ሲፎከር ነበር ፣ አሁን ግን መቃብርም በክርስቶስ በር አገኘ ። ከወደቅንበት ስፍራ ላይ የሚመጡ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ናቸው ። እርሱ ግን አደጋችንን የተሸከመ ነው ። ቍስላችንን ወስዶ ፈውስን የሰጠን ነው። የነበርንበት ስፍራ ሲኦል ነበርና ወደ ሲኦል በአካለ ነፍስ ወረደ ። በዚህም ለነፍሶች ነጻነት ሰብኮ ፣ ምርኮና ብዝበዛን አደረገ ።

እርሱ ከሕዝብና ከአሕዛብ በመወለድ በልደቱ አስታረቀን ነው ። ባዕድ አደረገን ብለው አሕዛብ እንዳያኮርፉ እርሱ የእነ ረዓብ ፣ የእነ ሩት ዘር ነው ። ከፀሐይ ርቀው ያሉ በብርድ እንዲጎዱ እንዲሁም ከፀሐይ ክርስቶስ ርቀው የነበሩ ሰላምን አጥተው የሚታወኩ ናቸው ። እርሱ ግን በመምጣቱ ፣ በሥጋዌው የነፍስን ማዕበል ገሠጸ ። ለነፍሳችንም መድኃኒትሽ እኔ ነኝ ብሎ ዕረፍትን ሰበከላት ። እስራኤል በመባ በመሥዋዕት ፣ አረማውያን በጣኦት ቢኖሩም ሁሉም ሰላምን አላገኙም ነበር ። ሰላም ክርስቶስ ነውና ። ምሳሌው ተስፋ ቢሆን እንጂ ምግብ አይሆንም ። የበግ መሥዋዕቱም ወደ ክርስቶስ ቢያመለክት ፣ ጊዜያዊ የቍጣ ማብረድ ሥራ ቢሠራም ከገሀነመ እሳት ግን የሚያድን አልነበረም ። ጌታችን ግን እውነተኛው በግ ሁኖ ሕዝብና አሕዛብን አሳረፈ ። ጌታችን ሰላምን ያወጀው በምድር ላይ ብቻ አልነበረም ። በሲኦል ሆድ ውስጥ ተውጠው ለነበሩትም ሰላምን አወጀላቸው ። ሲኦል ከዚህ በፊትም ከዚህ በኋላም አይታ የማታውቀውን ብርሃን አየች ፣ ሰምታ የማታውቀውን ሰላም ሰማች ። አጋንንት የሚገዙት እያወኩ ፣ ክርስቶስ የሚገዛው ግን ሰላምን እየሰጠ ነው ።

በዚህ ዓለም ላይ ፣ በሕይወት ጉዞ ውስጥ ብዙ የምሥራቾች ሊኖሩ ይችላሉ ። ከሰላም የበለጠ የምሥራች ግን የለም ። መኖሪያው ፣ ማባያው ፣ መሾሚያው ፣ መሞሸሪያው ፣ መውለጃው ፣ መክበጃው ሰላም ነው ። ሰላም ወልደ እግዚአብሔር ለሞት የበቃለት ጉዳይ ነው ። ይህ ሰላምም እንኳ ለምድር ለሲኦል ፣ እንኳን ለቆሙት ለሞቱት የተረፈ ነው ። ዓለም ከዚህ በኋላ ለሰላም ደም ማፍሰስ አይገባትም ነበር ። የፍጡር ደም ቢፈስ ሰላም አይመጣም ። ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ በመሞቱ ግን ሰላም መጣልን ። ሰላም የመለኮት ገንዘብ ናት ።

የተኰነንነው በሙሴ ሕግ ሳይሆን በአዳም በደል ነው ። ኵነኔን ያመጣው የሙሴ ሕግ ቢሆን ኖሮ እስራኤል ተኰንነው አሕዛብ ይድኑ ነበር ። በአንዱ አዳም በመኰነናችን በአንዱ ክርስቶስ ሥራ መዳን ሁኖልናል ። አንዱ አዳም እኛን ለማስኰነን በቂ ከነበረ አንዱ ክርስቶስ እኛን ለማዳን በቂ ነው ። በአዳም መኰነናችንን አምነን በክርስቶስ ድኅነት እንዳገኘን ካላመንን እምነታችን ሙሉ አይደለም ። ኃጢአትን ማመን ብቻውን እምነት አይባልም ፣ ምሕረተ-ሥላሴንም ማመን ይገባል ። ወደ አብ የምንገባው በአንድ መንፈስ ነው ። ሕዝብም አሕዛብም በአንድ ኅብረት ወደ አብ እንድንገባ ተፈቅዷል ። አንዱ ኅብረት የሚገኘውም በክርስቶስ የቤዛነት ግብር በማመን ነው ። ከገነት ተባረን የነበርነው አሁን ወደሚበልጠው ወደ አብ መግባትን አገኘን ። አንድ መንፈስ የሆኑ ወደ አብ መግባት ይችላሉ ። የተለያየ አሳብና ምኞት ያላቸው ግን ወደ አብ መግባት አይችሉም ። ወደ አብ ስንገባ ከፍ አድርገን የምናሳየው መፈክር ወይም ባንዲራ አለን ። እርሱም የጌታችን ንጹሕ ደም ነው ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ