የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሰላም ይሁን !

ይህ ዓለም በሰላም መኖር ብቻ ሳይሆን በሰላም መቀበርም የሚናፈቅበት ዓለም ነው ። በፍጹም እርጅና ላይ የነበረው ስምዖን አረጋዊ እንኳ ጌታን ታቅፎ የለመነው “ጌታ ሆይ ፥ አሁን እንደ ቃልህ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ” ብሎ ነው ። /ሉቃ. 2፡29 ።/ በዚህ ዕድሜ ላይ በሰላም መሰናበት ምን ያሳስባል? ቢሉ የሰው ልጅ እስከ ሞት ከአቋሙ የመውረድ ፣ ከምግባሩ የመዋረድ ፣ በሃይማኖቱ የመወራረድ ጠባይ አለውና ነው ። ስለዚህ በሰላም መሰናበትን ለመነ ። ጌታ አስቀድሞ “በሰላም አሰናብትሃለሁ” ቃል ገብቶለት ነበር ። በርግጥም ጌታን በሥጋዊ ዓይኖቹ አይቶ ፣ በሽምግልና ክንዶቹ ታቅፎ ነበርና ነገር ሳይበላሽ እንዲህ እንዳማረበት መሞትን ለመነ ።

አባቶቻችን፡- “አሟሟቴን አሳምረው ፣ ቀባሪ አታሳጣኝ” የሚለው ጸሎታቸው መጽሐፋዊና በኑሮ የተፈተነ ነው ። አሁንም፡- “ከሞቱ የአሟሟቱ” ይባላል ። የዕብራውያን መልእክት ፀሐፊም ስለ ሃይማኖት አርበኞች በተናገረበት ድርሳኑ፡- “እነዚህ ሁሉ አምነው ሞቱ” ይላል ። /ዕብ. 11 ፡ 13 ።/ ፈያታዊ ዘየማን ክዶ ኖሮ አምኖ እንደ ሞተ ፣ እነ ቀያፋ አምነው ኖረው ክደው ሞተዋል ። ሰማይ ምሥጢር ነው ፤ ወንበዴ ገብቶበት ፣ ሊቀ ካህናት የሚቀርበት ነውና ። ሰማይ ማልደው የተጠሩ ቀርተው ፣ የሠርክ ተጠሪዎች የሚካፈሉት ዋጋ ነው ። ይህን ዓለም ጨረስኩት የሚባለው ከሞትን ከሦስት ቀን በኋላ ፣ ሠልስት ከተለቀሰ ወዲያ ነው ።

እግዚአብሔር አምላክ ጻድቁ አብርሃምን፡- “አንተ ግን ወደ አባቶችህ በሰላም ትሄዳለህ በመልካም ሽምግልና ትቀበራለህ” አለው ። ዘፍ. 15 ፡ 15 ። በሰላም ትሄዳለህ ማለቱ ዘሩ የሆኑት እስራኤል ዘሥጋ በግብጽ ምድር የሚያገኛቸውን መከራ አታይም ሲለው ነው ። በሕፃናት ደም የጡብ ጭቃ ሲቦካ አታይም ሲለው ነው ። ደም እንደ ዝናብ ሲወርድ ፣ በክፉ አገዛዝ ልጆችህ ሲሰቃዩ አታይም ማለቱ ነው ። አለማየትም ለካ በረከት ነው ! “እንኳን ይህን ሳያዩት ሞቱ” የተባለላቸው ብፁዓን ናቸው ። ለአንዳንድ ሰው መኖር ብዙ ሐሣር ያሳየዋል ። የትውልድን ፣ የወገንን ስቃይ ማየት እጅግ ክፉ ነው ።

የዓለም መከራ የጀመረው በልጅ ሞት ነው ። አዳም ተቀምጦ ወጣቱ አቤል ሞተ ። ቃየን ክፉው እያለ ደጉ አቤል ተወገደ ። በሕይወት ውስጥ እጅግ አድካሚው ጥያቄ ፣ መላሽ መምህር ያጣው ሙግት “ለምን?” የሚለው ነው ። አቤል የሞት ማሟሻ ነበር ። የተሟሸ ጀበና ፣ የተሟሸ ወፍጮ ከዚያ በኋላ ሥራ አይፈታም ። ታዲያ ባለ ቅኔው እንዲህ አለ፡-

“ሞት ፊደል ተምሮ ያነባል ስንል፣
እንኳን ሊያነብና ገና ያግዛል ።”

“ሀ” ግእዝ “ሁ” ካዕብ የትምህርት መጀመሪያ ነው ። ሞት ገና ያግዛል ፣ ገና “ሀ” ግእዝ ወይም ሀ መጀመሪያ ፊደል ይላል ማለቱ ነው ። ምሥጢሩ ሞት በአቤል ሥራ ጀምሮ ገና በአዲስ ጉልበት ዛሬም እየሠራ ነው የሚል ይመስላል ። ሟች እየበዛ ነው ማለቱ ነው ። የመጨረሻውን ሟች ባናውቀውም የመጀመሪያውን ሟች ግን እናውቀዋለን ። የምንሞትበትን ቦታ ባናውቀውም የተወለድንበትን ቦታ ግን እናውቀዋለን ። ሰው በሰዎች እርዳታ ተወልዶ ፣ በሰዎች ጥይት መሞቱ ይገርማል ። ሽማግሌው፡- “ሰው አለ እንዳንል ሰው የለም ፣ ሰው የለም እንዳንል ሰው አለ” ያሉት ለካ ለዚህ ነው ።

ጻድቁ አብርሃም፡- “በመልካም ሽምግልና ትቀበራለህ” ተባለ ። ክፉ ሽምግልና የደከሙለት አገር ሲፈርስ ፣ የኖሩለት ራእይ ሲከሰከስ ፣ ያሳደጉት ልጅ ደሙ ሲፈስስ ማየት ነው ። አንዳንድ ልበ ደንዳና ፣ የዕድሜ ሳይሆን የማስተዋል ደሀ የሆኑ ይህ አይገርማቸውም ።

“የወንድሙ ሞት ወንድሙን ካልከፋው ፣
ቅበሩት ከደጁ በድኑ እንዲከረፋው ፤”

ደግሞም እንዲህ ተብሏል፡-

“ከስምንተኛው ሺህ እኛም ደረስንበት ፣
አባት ተቀምጦ ልጅ ከፈረደበት
ምድር እንደ ዳቦ ከተቆረሰበት ።”…

አዎ አዋቂውን ሊቅ ያልተማረ ሲያርመው ፣ አባቶች ዝም ብለው ልጆች ሲለፈልፉ ፣ ምድር ተከፋፍላ የእኔ የእኔ ሲበዛ ስምንተኛው ሺህ መድረሱን ፣ የመጽሐፉ በዓይን መታየቱን ያስረዳል ። ጻድቁ አብርሃም፡- “በመልካም ሽምግልና ትቀበራለህ” ተባለ ። ለመኖር ብቻ ሳይሆን ለመቀበርም ሰላም ያስፈልጋል ። “ተጣልቶ ለመታረቅም አገር ያስፈልጋል” ያሉት አባት በእውነት የመንፈስ ቅዱስ ክስተት መጥቶላቸው ነው ። ሰላም ይሁን ለአገሩ !

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ