ምእመን በእንባ እንዲህ አለ…
ጌታዬ ሆይ !
ጊዜ አንዱን ከፍ አንዱን ዝቅ እንደሚያደርግ እናገራለሁ ። “ጊዜ የሰጠው…” እያልሁ እተርታለሁ ። ነቢይት ሃናና እመቤቴ ቅድስት ድንግል ማርያም በነቢይነት ጸሎታቸው፡- ባለጠጋና ደሀን ፣ ልዑልና ትሑትን ቦታ የምታለዋውጥ አንተ መሆንህን ተናግረዋል ። ጊዜ አስቦ ለማንም ምንም አይሰጥም ። መስጠት መንሣት ያንተ ሥልጣን ነው ። ቸርነትን ከጊዜ ሳይሆን ካንተ እንድጠብቅ ፣ የጊዜ ጣዖትን ከማምለክ እንድተርፍ እለምንሃለሁ ። ጊዜ ብዬ ስናገር ውስጤ ይቆጣል ፣ ብስጭትና ቁጭት ያናውጠኛል ። የጊዜ ጌታ ፣ የዓለማት ፈጣሪ ፣ የዘመናት ቀማሪ አንተ መሆንህን በማመን ተስፋ ማግኘትን እሻለሁ ። አንተ ቅዱስ ሆይ ! ከጊዜ በፊት ነህና ጊዜዬ አለፈ አልልም ። ከጊዜ በላይ ነህና ጊዜው ባይደርስም ውኃውን ወይን ታደርጋለህ ። የጊዜ አሳላፊ ፣ ደኃራዊ አምላክ ነህና ጊዜው ክፉ ነው ብዬ አልፈራም ። ሞት ቀርቦኝ ጥላውን ቢያጠላብኝ ፣ ክፉ ሰልጥኖ ቢገዳደረኝ ከነቢዩ ጋር ሁኜ፡- “በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ ፣ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉውን አልፈራም” ብዬ እዘምራለሁ ።
ጌታዬ ሆይ !
ጉጉቴን ካንተ ላይ አንሥቼ መጪና ሂያጅ በሆነ ነገር ላይ እንዳላሳርፍ ፣ ልቤ እንደ ሕፃን በዚህ ዓለም ነገር ላይ ሲጣበቅ እገሥጸዋለሁ ። በዓለማዊ ነገር በመወዳደር የክርስቲያንነትን ክብር እንዳልነካ ፣ በሚታይ ነገር ላይ ብቻ ተተክዬ መንፈሳዊነትን እንዳላጣ ፣ ብቻዬን ላግኝ በማለት የአማኝን ቁመና እንዳልከስር እፈራለሁ ። አቤቱ የሰው ልጅ ዕረፍቱ የትና መቼ ነው ? እንደ ዋተተ ይኖራል ፣ በመዋተት ላይ ሳለም በሞት ይጠራል ። አንተንና ራሴን ሳላውቀው በሞት እንዳልጠራ ፣ ወደማልመለስበት ዓለም ከመሄዴ በፊት ጥቂት ዐርፍ ዘንድ ተወኝ ።
የመድኅን ቃል
ልጄ ሆይ !
ካልተፈተንህ ወርቅነት ፣ ካልተተኮስህ ውበት አይመጣም ። በጊዜ ውስጥ አሳቤን የምፈጽም እኔ ነኝ ። በዚህ ዓለም ላይ የእኔ አባታዊ ስጦታ አለ ። ሰዎች ዘርተው የሚያጭዱት የኑሮ ውጤት አለ ። የደጋጎችና የክፉዎች ፍሬም ይታያል ። ጊዜ እንዳንተ ነው ። ለእኔ ስትገዛ ጊዜው ይገዛልሃል ። እየዘነበ ካለው ክፋት ጋር የእኔ ምሕረት ሊወርድ አይችልም ። ሰው ከመንገዱ ካልተመለሰ እኔ አልመለስም ። ልማዴ ሰውን ማፍቀር ቢሆንም የወጣችዋን ፀሐይ ለመሞቅ ከተደበቁበት ዋሻ መውጣት ያስፈልጋል ። የፍጡራን የበላይ ብቻ ሳልሆን አስገኚም እኔው ነኝ ። የሥልጣንና የሰውነት መገኛህን እኔን ቸል ስትለኝ ይገርመኛል ! ላንተም እየቀናሁልህ ከብዙ ጣዖታት ስናጠቅህ ኑሬአለሁ ። እኔና የእኔ የሆኑት ብቻ ያግኙ ይክበሩ አትበል ። ምድር የሁሉም ናት ። ምድር ሰፊ ናት ። ምድር በቂ ናት ። ስጦታዬ ሕፀፅ የለበትም ። ቀኑን ከነ በረከቱ ሰጥቻለሁ ። ያከበሩኝን አከብራለሁ ፣ የናቁኝ ተንቀው ይወድቃሉ ። ጊዜ ለእነዚያ ሲያልፍ ለእኔ ጸንቶ ይኖራል ብለህ አትሞኝ ። እኔ በፍርዴ የማላደላ ነኝ ። ተወልዶ ብልጫ ፣ አንክሶ ሩጫ የለምና ሁሉም ለእኔ እኩል ነው ። እግዚአብሔር የተለየ አገርና ወገን የለውም ። ግዛቱ በምድር ሁሉ ፣ ፍቅሩም ለሰው ልጆች ሁሉ ነው ። በጠባብ ዓለምህ እኔን አታጥብበኝ ።
ልጄ ሆይ !
አንተን የሚያስፈራህ ሥጋዊ ሞት ነው ። እኔ ግን የማስብልህ ከዘላለም ሞት እንድትድን ነው ። አንድ ነገርን በጣም ስትጓጓው ባታገኘውም ፣ ያገኘኸው እየመሰለህ በራስህ የምስል ክሰታ ትሰክራለህ ። በመጨረሻ አእምሮህን ታጣለህ ። በጣም ያጓጓህ ከሆነ ምግብም ቢሆን ተወዉ ። የእኔን መምጣት እንጂ የስኬትን መምጣት አትናፍቅ ። ሁሉ ቢሟላም ዓለም መጉደል ሕጉ ነውና ጉድለት ይቀጥላል ። ያለ ችግር ለመኖር የምታደርገውን ከንቱ እንቅስቃሴ ተወው ። ችግርህን ወደ እኔ ማደጊያ መሰላል አድርገው ። በመንፈሳዊ ዓለም በሹመት ሳይሆን በጸጋ ለማደግ ትጋ ። አንተ በደጅ ቆመህ ወደ ቤቴ ሰዎችን ለማምጣት መድከምህ ጠፍተህ መፈለግህ ነው ። ዶሮ ሳይነቃ ሌላውን አይቀሰቅስምና እባክህ ንቃ !! ሰዎች በደቂቃ ህልውናቸው እያከተመ ፣ መጣሁ ብለውህ እየቀሩ ባለበት ዘመን ለንስሐ ራስህን አዘጋጅ ። የወንድምህን ስም አጥፍተህ ፣ የወዳጅህን ገበታ ገልብጠህ የደረስክበት ነገር ሁሉ ምንም እርካታ የለውምና ፣ የዘላለሙን መንገድ ሳትጀምር የተጣላኸውን ታረቅ ።
ልጄ ወዳጄ ፣ የመስቀል ሞቴ ትርፍ ሆይ ! በበረከት ተባረክ ! የእኔ ድል ካንተ ጋር ሁና የሚያውክህ ነገር ሁሉ ይቆረጥ ! ሰላሜ ይደርብህ !