የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሰማያዊ ወግ /4

የምእመን ድምፅ

ጌታዬ ሆይ !

አንዳንድ ጊዜ ዓለም በመኝታ ክፍሌ ልክ ትመስለኛለች ። አንተንም በተወሰነ ቦታና ጊዜ ልወስንህ እዳዳለሁ ። ምድሩ ሰፊ ነው ብዬ እንደ አብርሃም ወንድሜን ከመግፋት እርቅ ዘንድ እመኛለሁ ። የሁሉ አምላክ መሆንህን ተረድቼ ማንንም ከመጥላት እንድተርፍ እሻለሁ ። በሁሉ ዘመን አለህና ይሰማኛል ብዬ እንድጸልይ እፈልጋለሁ ። ልጅነትና ሽምግልና ብዬ የምጠራው እኔ ነኝ ፣ አንተ ግን ከጊዜ ውጭ ነህ ። ስለ ጉብዝናህ በጎልማሳ አምሳል ፣ ስለ ጥበብህ በሽማግሌ አርአያ ብትገለጽም ዘላለማዊ ነህ ። በጊዜና በቦታ አትወሰንም ።

ጌታዬ ሆይ !

አገልጋዮችህን መውደድ እፈልጋለሁ ። ንጉሡን ወድዶ አምባሳደሩን መጥላት አይቻልምና ። “ካህናትህ ጽድቅ ይልበሱ ፣ የመረጥሃቸውን በጎነት አሳየኝ” ብዬ እንደ ዳዊት መለመን እሻለሁ ። በሥጋ የሚያክሙኝን ሐኪሞች ፣ የሚያማክሩኝን ባለሙያዎች አከብራለሁ ። ዘላለማዊ ሕይወቴን የሚያገለግሉትን ፣ በልደት በልቅሶ የማይለዩኝን አገልጋዮች ግን እንቃለሁ ። ሥጋዊ አባቴን እያለበስሁ አገልጋዮችን እገፍፋለሁ ። የሥጋ አባቴን ስህተት እየሸፈንሁ የአገልጋዮችን ነውር በአደባባይ አወራለሁ ። ጌታ ሆይ ! አገልጋዮችህን እንድወድድ ፣ ከሰይጣን ጋር ገጥሜ ከማሳደድ እንድተርፍ እለምንሃለሁ ። ሰይጣን አንድ በግ ከሚሰርቅ እረኛውን ቢመታ ሺህ በግ ይበትናል ፤ የሺህ ዋጋ ያለውን እረኛ ከመናቅ ጠብቀኝ ። እረኛውን መትቶ መንጋውን ከሚበትን ሰይጣን ጋር አብሮ ከመዝመት ጠብቀኝ ። እባክህ ጌታ ሆይ አገልጋዮችህን በመውደድ ባርከኝ ።

ጌታ ሆይ !

ትዕግሥት ይጎድለኛል ። እምነት ያልጨበጥሁትን እንደ ጨበጥሁ አድርጌ መደሰት ነው ፤ እኔ ግን ጨብጬም የማላምን ነኝ ። ሳያዩ የሚያምኑ ደስተኞች ናቸው ፣ እኔ ግን አይቼም ማመን ያቃተኝ ብኩን ፍጡርህ ነኝ ። እባክህ በረድኤትህ አቁመኝ ።

የመድኅን ቃል

ልጄ ሆይ !

ስለ መልእክተኛው የማያስብ ፣ ቀለብ የማይሰፍር ፣ ደኅንነቱን የማያስከብር ንገሥ በዓለምም በዘመንም የለም ። በኃጢአት በጨለመው አእምሮአቸው የምድር ገዥዎች ይህን ካሰቡ እኔ ጻድቅ ጌታ አገልጋዮቼን አከብራለሁ ። በነቢዩ ዳዊት፡- “የቀባኋቸውን አትዳስሱ ፥ በነቢያቴም ክፉ አታድርጉ ብሎ ፥ ሰው ግፍ ያደርግባቸው ዘንድ አልፈቀደም ፥ ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ” የተባለልኝ እኔ ነኝ ። ንጉሥ ነኝና መልእክተኛ አለኝ ። በሁሉ ዘመን ንጉሥ ነኝና በሁሉ ዘመን መልእክተኞች አሉኝ ። አገልጋዮቼ ለእናንተ አንድ ቃል ለመናገር ብዙ ቀን በጸሎት ያምጣሉ ፣ በጽሞና አእምሮአቸውን ይጨምቃሉና የቀረበ ማዕድ ስትበሉ ከኋላ ያለውን ልፋት አስቡ ።

ልጄ ሆይ !

ብሉኝ ፣ ብሉኝ የሚሉ ፍሬዎች አገልጋዮቼ የማይገኙበት ዘመን ይመጣል ። አሁንም እየሆነ ነው ። በእግዚአብሔር ቤት ኃጢአትን የሚያገለግሉ ፣ በመስመራቸው ከመሮጥ የቀደማቸውን ጠልፈው የሚጥሉ ፣ ጨለማን ብርሃን ለማለት የሚደፍሩ ሐሳውያን መምህራን የሚመጡበት ዘመን ቀርቧልና ፣ አሁንም እየሆነ ነውና መልእክተኞቼን አክብሩ ።

ልጄ ሆይ !

እኔ የተለየ ሰው ፣ የተለየ አገር የለኝም ። ሁሉንም የአዳም ልጅ እወዳለሁ ። በደቡብ ቢቀመጥ በሰሜን ፣ ያስቀመጥሁት እኔ ነኝ ። ምድርን ሙሉአት የሚለው በረከቴ ደርሶ የምድር ዳርቻ ላይ ያለውን ሰው አትጥሉት ። ከእናንተ ቢርቅም ከእኔ አልራቀምና ውደዱት ። እኔን ካንጀት የሚወደኝ የወደድሁትን ሰው የሚወድድ ነው ። ብዙ የቃላት ወዳጆች አሉኝ ፣ በተግባር ሰውን የሚወድዱ ግን እያጣሁ ነው ። እኔን የት አግኝታችሁ ትቀበሉኛላችሁ ? ስደተኛውን ስትቀበሉ ያን ጊዜ እኔን ተቀበላላችሁ ። በድሀው እጅ ለመቀበል ጎዳና ወጥቼአለሁ ፣ ፍርድ ካጣው ጋር በፍርድ ቤት ተከስሻለሁና መጥታችሁ እዩኝ ።

ዘላለማዊ በረከቴ ከእናንተ ጋር ትሁን !

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ