የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሰማያዊ ወግ /8

የምእመን ድምፅ፡-

ጌታ ሆይ ! አንተ ፍትሕ አጥተህ በተሰቀልህባት ምድር ላይ እኔ ፍትሕ እየፈለግሁ አለቅሳለሁ ። ፍትሕ ማጣትህ ፣ ፍትሕ ላጡት ድምፅ እንደሆነ ፤ “ስለ ድሆች መከራ ፣ ስለ ችግረኞች ጩኸት አሁን እነሣለሁ” የሚለው ቃልህም እውነት እንደሆነ አምናለሁ ። ፍትሕን የምትሰብክ ቤተ ክርስቲያን ፍትሕ ከጠፋባት ፣ አባት ያጸናውን ግብር ንጉሥ ከቀነሰባት ፣ በረቂቅ ዓለም የሚፈርዱትን ካህናት ምድራውያን ዳኞች ከገላገሉ ፣ ዛሬም ከመስቀል አልወረድህም ፣ መከራህ አላበቃም ። በፍቅር ካልሆነ ከሰማይ ወርደህ የደቀ መዛሙርትህን እግር ማጠብ ፣ የዓርብን መከራ መጎንጨት እንደምን ይቻላል ! ፍቅር ስለሌለን ከአልጋችን ወርደን ልንጸልይ ፣ ከመቀመጫችን ተነሥተን የወደቀውን ልናነሣ ፣ ከቤታችን ወጥተን ብቸኞችን ልንጎበኝ አልቻልንም ። ከዙፋን ይልቅ በረትን ፣ ከክብር ይልቅ መስቀልን የሚያስመርጥ ያንተ ፍቅር ይንካን ! ምን ነካቸው? ሲባል “የመለኮት ፍቅር ነካቸው” እስኪባል ድረስ በመሥዋዕትነት የሚረካ ማንነት አድለን ።

በማማው ላይ ሁኖ ወታደር ጠላት መጣ በማለት የማንቂያ ባሩድ ይተኩሳል ። በማማው ላይ ሁኖ ሰው ሞተ በማለት ጡሩንባ ነፊው ያረዳል ። በማማው ላይ ሁኖ እረኛው ስለ ምድራዊ ፍቅር ዋሽንት ይነፋል ። በመስቀል ላይ ሁነው ድኅነትን ያወጅህ ክርስቶስ ሆይ ሰላም እንልሃለን ። በተቃቃረውና በተቀያየመው ዓለም ፊት “አባት ሆይ ይቅር በላቸው” በማለት የድርጊታቸውን መነሻ አለማወቅ ብለህ ያዘንህ አንተ ድንቅ ነህ ። ቤት አልባ ለሆነው ፣ ዱር ቤቴ ላለው ፣ ገድሎ ለሚፈትሸው ወንበዴ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ በማለት ፣ የእናቱ በር ለተዘጋበት የገነትን ደጃፍ ከፈትህለት ። አንተ እንኳን ምድርን ሰማይንም የምታወርስ ነህና ደግነትህ አይጠረጠርም ። በሔዋን ስናዝን ፣ የሞት በር ናት ስንል ኑረን ነበር ። በዳግሚት ሔዋን በኩል መጥተህ አዳንከን ። እናት ብለን እንኮራባት ዘንድ እናትህን፡- “እነኋት እናትህ” ብለህ ሰጠኸን ። ይቅርታን ፣ ገነትን ፣ እናትህን ለሰጠህባት ዓርብ ፣ ሁሉን ሲያሳጡህ ሁሉን ለናኘህበት መስቀልህ መታሰብ ይገባል ።

አምላክ እኔ ነኝ ሊል የከጀለውን አዳምን “አምላኬ አምላኬ” በማለት ሥጋ መልበስህን ፣ የፍጡር ጌጡም አንተን አምላክ ብሎ መገዛት መሆኑን በመስቀል ላይ አስተማርከን ። ከተራራው ስብከትህ ፣ ከመቅደስ ንባብህ ይልቅ የመስቀሉ ጩኸትህ ልብን ይነካል ። ጠላትህን በመውደድ ትምህርትህን ሕያው ያደረግህበት ፣ የመቅደሱን ንባብ የተረጎምህበት ያ ቀን ልዩ ነው ። ምልአተ ኃጢአት ለደረሰበት አዳም ተፈጸመ ብለህ መንገደ ሰማይን ስለከፈትህ ምስጋና ይገባሃል ። ከሰማርያ ውኃ ይልቅ የእኛን መልካምነት መናፈቅ ፣ መልካምነታችንን የምትናፍቅ አባት መሆንህን ይገልጣል ። ነፍስ አድራሻ አጥታ ስትዋትት ፣ ሥጋ መቃብር ፣ ነፍስ ሲኦል ሲፈረድባቸው አንተ ግን፡- “አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” በማለት የነፍስ አድራሻ የአባትህ እቅፍ መሆኑን ነገርከን ። ለዚህ ውለታህ ምስጋና እናቀርባለን ።

የመድኅን ቃል፡-

ውረድ ሳትሉኝ ወረድሁ ፤ ከናፍቆታችሁ በፊት ላድናችሁ የናፈቅሁ ፣ ታስፈልገናለህ ሳትሉኝ አስፈልጋችኋለሁ ብዬ የመጣሁ ፣ በኃይል ስትጠብቁኝ በትሕትና የተገለጥሁ ፣ የጦር መሪ ልታደርጉኝ ስትሹ የሰላም ሰባኪ ሁኜ የመጣሁ ፣ የሚገድልና የሚበቀል አምላክ ስትከጅሉ እኔ ግን በመስቀል ላይ የሞትሁ ነኝ ። ለመፍረድ ኃጢአታችሁ በቂዬ ነበር ። ለማዳን ግን የእኔ ፍቅር ያስፈልጋችኋል ። እኔ ሰው ሁሉ የሚሰማውን ቋንቋ ተናግሬአለሁ ። እርሱም ፍቅር ነው ። ምሎ ለካደኝ ጴጥሮስ ምዬ ሞቼለታለሁ ። የታለሉትን አነጻ ዘንድ ርኵስ ምራቅን ተቀብያለሁ ። እናንተ በመጡት ደስ ሲላችሁ ፣ በሸሹት ትፈርዳላችሁ ፤ እኔ ግን ዛሬም መስቀሌ ናቸውና ላመጣቸው እሄዳለሁ ። ጊዜ ቸርነት እንዲያደርግላችሁ ትጠብቃላችሁ ፣ የደግነት ፍጻሜ ግን ከመስቀል ላይ ይቀዳል ። ልደግፋችሁ መጣሁ ፣ ብዙ ዘመን የሚጥሉአችሁን ተወዳጃችሁ ። በሰው ስቃይ ደስ ሲላችሁ ፣ እኔ ግን ስቃያችሁን ወረስሁ ። ሁሉም ያለውን ያወርሳልና ዕዳችሁን ወስጄ የእኔን ነጻነት ልሰጣችሁ ተዛመድኋችሁ ። ለመጠቀም ስትሹ ለመጥቀም ወደ ኋላ ትላላችሁ ፣ መስቀሌ ዓለት ልባችሁን ይስበረው ። የመስቀሌ ጥላ ሁላችሁን ይሰበስብ ዘንድ ፣ ዋዕዩ ያቃጠላችሁ ትድኑ ዘንድ ወደ እናንተ መጥቻለሁ ። በምድረ በዳው ዓለም ያሰማራኋችሁ የምሰበስባችሁ እኔ ነኝ ።

ሰማያዊ ወግ / 8

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 6 ቀን 2015 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ