የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሰቀሉህ !!!

አንተስ ሁሉን ስታውቅልን ለራስህ አላውቅ ብለህ በዳይህን እንዴት ትፈጥራለህ ? እኛን የሚያዋድደን አለማወቅ ፣ አለመተዋወቅ ነው ። አንተ ብቻ አውቀህ ትወደናለህ ። ሰቀሉህ መልኬ ያልካቸው ፣ ዝቅ ብለህ ከአፈር ያነሣሃቸው ፣ ሬሳቸውን በአፍህ እስትንፋስ ሕያው ያደረግህላቸው ፣ ሚሊየን ጊዜ አድርገህላቸው አንድ ምስጋና የማያውቁ እነዚያ የአዳም ዘሮች ሰቀሉህ ። አንተ ለሁሉ እንደ ተሰቀልህ ፣ አንተን ሁሉ ሰቀለህ ። ከነጻነት ጋር የፈጠርሃቸው እነርሱ የግርግሪት አሰሩህ ። ካንተ በርባንን መረጡ ፣ አልጋ ስትሰጣቸው አመድ ላይ ተንከባለሉ ። የማይፈርድ ችሎት ፣ እውነትን የማይሻ ሸንጎ አቋቁመው ፣ ፍርድ ቤት አድርሰነዋል ለማለት አደባባይ አቆሙህ ። ስለመግደልህ ሳይሆን ስለመፈወስህ ሞት በየኑብህ ። አንተም አርፈህ አልቀመጥ ፣ ሲጠሉህ አልጠላችሁም ብለህ ይኸው ሰቀሉህ !

የሚደበድባትን ባል ያፈቅረኛል የምትል ሚስት ፣ የሚለመጥጠውን ንጉሥ ቆራጥ መሪ የሚል ሕዝብ ባለበት ዓለም በትዕግሥትህ ምክንያት ሰቀሉህ ። ገራፊ የለመደው ወገን የምትገረፍለትን አንተን መቀበል አቃተው ፣ ዛሬም አስመሳዮች ጌታን ተቀበልን እያሉ ራሳቸውን በመቀበል ፣ የተሰቀልከውን ሳይሆን ምቾታቸውን በማሳደድ ይሰቅሉሃል ። አንተም እንቢ አልክ ሁለት ሺህ ዓመት ልብ አልገዛም ብለህ በየጓዳው ፣ በየምርጫው ይሰቅሉሃል ። አይሁድ ስለሰቀሉህ የሚያለቅሱ ደጋግመው በክፋታቸው የሚሰቅሉህ ግብዞች ባሉበት ዓለም አንተ ተሰቀልህ ። ለሰቀሉህ ተሰቀልህላቸው ። ለገደሉህ ሞታቸውን ወሰድህላቸው ። የታመመ ቢታመሙለት አይድንም ። የሞተ ቢሞቱለት ቀና አይልም ። አንተ ግን በመገረፍህ ቍስል የምታድን ፣ በሞትህ ሕይወት የምትሰጥ ነህ ። ይገርማል ሥጋዬን ብሉ ስላልህ ላይበሉህ ሰቀሉህ ። አንተ ግን ሰቀሉኝ አላልህም ፣ ተሰቀልሁላቸው አልህ አንጂ ።

ባንተ ምክንያት ከስንቱ ልጣላ ። ከዙፋን በረትን ፣ ከሰማይ አፈርን መርጠህ በመምጣትህ በር ዘጉብኝ አትበል ። ፍጥረተ ዓለሙን አንዱን በእንጀራ ፣ አንዱን በምስጋና እያጠገብህ የምትኖረው የብላቴናዋን የድንግልን ወተት የለመንከው እኮ ምን ቸግሮህ ነው ! ጠላት የሚፋንንብኝ ባልችል ፣ ድህነት የሚጎስመኝ ቢሳነኝ ነው ። አንተ ግን ወዶ ገብ ድሀ ለምን ሆንህ ! እኮ ከመውደድ አያርፍም ፣ በመጥላት ይራቀን ብለው ሰቀሉህ ። አንተ ግን ሞኝ ሆነህ ሳይሆን አፍቅረህ ፣ መላ አጥተህ ሳይሆን መለኛ ሆነህ ሰቀሉህ ! የባለጠጋው ልጅ ድህነትን ፈቅደህ ተቀበልከው ። ሰውን ለማዳን ሰው ልሁን ብለህ መጣህ ። ሰው ሳይሆኑ ሰውን ለማዳን የሚነሡ ብዙዎች አሉና ልታስተምራቸው ፣ ለሰው ከመሰቀል በፊት ሰው መሆን ይቀድማል ልትላቸው ሰው ሆነህ መጣህ ። የክፋት ብርድ ልብሳቸውን በትምህርት ገፈፍካቸውና ተው ስልህ ይኸው ሰቀሉህ !

የአብ ልጅ ፣ የድንግል ልጅ ያንተ ሞት ግሩም ነው ። በአንድ ዓይን እያስለቀሰ ፣ በአንድ ዓይን የሚያስቅ ነው ። በሚኖርበት ዕድሜ የሚሞቱት ቀዘባዎች ፣ መለሎዎች ፣ ሙናዎች በኀዘን ሰብረውን እንዳይኖሩ አንተ በሠላሳ ሦስት ዓመትህ ሰቀሉህ ። ከሞቱ ያሟሟቱ እያሉ በአደባባይ ለሚወድቁት የሚያለቅሱ አሉና አንተ በአደባባይ በመሰቀል ተጽናኑ አልህ ። ሟች ሁሉ ልብስ አይገፉትም ፣ ለመገነዣም አዲስ ልብስ ይሰፋለታል ። አንተን ግን ልብስህን ገፍፈው ሰቀሉህ ። እነርሱ እኮ ምን ያድርጉ ! ብቻቸውን በር ዘግተው የሚበሉ ናቸው ፤ አንተ አምስት ሺህ ሰው ትመግባለህ ። ሐኪም ቤቱን ልታራቁት በነጻ ትፈውሳለህ ። ባንተ ምክንያት ምግብ ቤቶች ፣ ሸክላ የሚያበሉ ጨካኝ ነጋዴዎች ገቢያቸው ቀነሰ ። አዎ ሰቀሉህ ! እንዲሰቅሉህ ስለፈቀድህላቸው ሰቀሉህ ። መስቀል የቻሉ ትንሣኤህን ማገድ አልቻሉም ።

ዛሬም ድሀ እየበደሉ ፣ ፍርድ እያጓደሉ ፣ ለወንድም መርዝ እየበጠበጡ ይሰቅሉሃል ። አንተ ስለሁሉ በሞትህበት ዓለም ሁሉ አንድ ሰውን ተባብረው ይሰቅሉታል ፣ በድንጋይ ይወግሩታል ። የደቦ ፍርድ ይሰጡታል ። ኦ ምንድነው የምትፈልገው ከእኔ ፣ እስቲ ተወኝ ! እኮ ብያለሁ ዛሬም ሰቀሉህ !!!

የእናትህ ዘመዶች ሰቀሉህ ። እኮ እርሷስ ላንተ ታልቅስ ወይስ ዘመድ ትቀየም ! ቅያሜው እንዲቀር በመስቀል ላይ ይቅር አልህ ! ልቅሶው እንዲሻር ከሞት ተነሣህ ። አንተ ብሩህ ኮከብ ፣ ላያጠፉህ የመቱህ አማኑኤል ሆይ ብቻህን አትነሣ ፣ እኛንም ይዘህ ተነሣ ! ማር ኢየሱስ ጣፋጭ ነህ ! ማር ኢየሱስ መሐሪ ነህ ! የአፍሪካ ቀንድ ላይ ተቀምጠን ጦርነት አላጣ ያለን ሕዝቦችህን የተሰቀልኸው እባክህ ሰላም ስጠን !

 

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 25 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ