የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሰው በረከት ነው

“እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት ፥ ሌሎቹም ነቢያት ፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች ፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ ፤” ኤፌ. 4፡11 ።

ከጌታችን ታላቅ ምሕረት ፣ ከሞቱም ብዙ ፍሬ ፣ ከትንሣኤውም ብርቱ ኃይል ፣ ከዕርገቱም ልዩ ይባቤ ፣ በየማነ አብ ከመቀመጡም ድንቅኛ ክብር የተነሣ ጸጋ ለቤተ ክርስቲያን ፈሰሰ ። ጸጋ ለግለሰብ አልተሰጠም ። አካሉ የሆነች ቤተ ክርስቲያን ትታነጽ ዘንድ ለኅብረቱ ተሰጠ ። ጸጋ አለኝ ብሎ ከኅብረት የሚለይ ፣ ጸጋዬ እንዲህ ነው ብሎም ራሱን የሚያጎላ ከመንፈስ ቅዱስ አሳብ ጋር ይለያያል  ። ጌታችን መሞቱ በተለየ አካሉ በለበሰው ሥጋ ብቻውን የፈጸመው ሲሆን ማዳኑ ግን ከአብና ከወልድ ጋር የሚጋራው የአንድነት ግብሩ ነው ። የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ለቤተ ክርስቲያን ሲልክም በወልድ ሞት መንፈስ ቅዱስ አዳኝ እንደ ተባለ ፣ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋም ወልድ ሰጪ ይባላል ። መስጠቱም ለምኖ ፣ ተማጽኖ ፣ ደጅ ጠንቶ ሳይሆን መስጠት የአንድነታቸው ሥልጣን በመሆኑ ነው ። መስጠትና መንሣት የእግዚአብሔርነት ሥልጣን ነው ። ስለሚሰጠው እግዚአብሔር ብቻ ሳይሆን ስለሚነሣው እግዚአብሔርም ማወቅ አለብን ። እርሱ በመስጠቱ አምላክነቱ እንደሚታወቅ በመንሣቱም መለኮትነቱ ሲነገር ይኖራል ። በመስጠቱ ብቻ ሳይሆን በመንሣቱም ፍቅሩን ይገልጣል ። አዳም ሕይወት ሰጪ የምትሆነውን ዛፍ እንዳይበላ ከገነት መባረሩ ምሕረት ነው ። ዘፍ. 3 ፡ 22 ። በበደለ አካሉ ያቺን ዛፍ ቢበላ ኖሮ ለዘላለም ኃጢአተኛ ሁኖ ይቀር ነበር ። ሰው ለዘላለም ኃጢአተኛ ሁኖ እንዳይቀር እግዚአብሔር ከገነት አስወጣው ። እርሱ መዓት በሚመስል ነገር መማር/ምሕረት ማድረግ ያውቅበታል ።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን የሰጠው ታላቅ በረከት ሰዎች ናቸው ። ሐዋርያትም ፣ ነቢያትም ፣ ወንጌላውያንም ፣ እረኞችም ፣ መምህራንም ሁሉም ሰዎች ናቸው ። ሰዎች ትልቅ ስጦታዎቻችን ናቸው ። ሰዎችን እንደ ስጦታዎቻችን ካልተቀበልን የምድር ኑሮ ከባድ ፣ የልባችን አሳብም ጨለማ ይሆንብናል ። ይልቁንም ወደ እግዚአብሔር ያቀረቡንን ባለሟሎች ትልቅ ስጦታዎቻችን አድርገን መመልከት ይገባናል  ። የእግዚአብሔር ጸጋ ወደ ምድር የሚመጣው ሰዎችን አድራሻ አድርጎ ነው ። እነዚያ ሰዎች ግን ያመኑ ሰዎች ናቸው ። ጸጋው በምድር ላይ ሁለት ዓይነት ሰዎች እንዳሉ ይነግረናል ። እነርሱም በእግዚአብሔር ያመኑና ያላመኑ ናቸው ። አጠቃላይ ጸጋና ልዩ ጸጋ አለ ። አጠቃላይ ጸጋ ለፍጥረት ሁሉ የሚሰጥ ሲሆን ልዩ ጸጋ ግን በእግዚአብሔር ለሚያምኑ የተሰጠ ነው ። ሰዎች በተፈጥሮ የተሰጣቸው ክህሎትና በማመን የሚያገኙት ሀብተ መንፈስ ቅዱስ አለ ። የሁሉም ምንጭ ግን እግዚአብሔር ነው ።

ቤተ ክርስቲያን ሁለት ጽኑ መሠረትና ሦስት ምሰሶዎች አሉአት ካልን ሁለቱ መሠረቶች ሐዋርያትና ነቢያት ናቸው ። “በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል” እንዲል ። ኤፌ. 2 ፡ 20 ። ምሰሶቹም ወንጌላውያን ፣ እረኞችና መምህራን ናቸው ። እስከ ጉልላቱ የሚሰካኩት ጡቦች ደግሞ ምእመናን ናቸው ። ምእመናን የቤተ ክርስቲያን ልብስ ፣ መሸፈኛ ናቸው ። ዛሬ ግን ደፋር አደፋፍሮአቸው አንዳንዶች አባቶቻቸውን የሚያዋርዱ ፣ በዓለም አደባባይ የቤተ ክርስቲያንን ምሥጢር ለጠላት የሚሰጡ ሁነዋል ። መሠረት ሁልጊዜ አይመሠረትም ። እንዲሁም የሐዋርያትና የነቢያት አገልግሎት የመሠረት አገልግሎት ነውና ሁልጊዜ አይኖርም ። የቤተ ክርስቲያን ዕድገት የሚቀጥለው በወንጌላውያን ወይም በሰባክያን ፣ በእረኞች ወይም በጳጳሳትና በቀሳውስት ፣ በመምህራን በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ነው ። የሚታየውን ሕንጻ የማይታየው መሠረት ይሸከመዋል ። እንዲሁም የዛሬዋን ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያትና ነቢያት ደክመውላታል ። መሠረት ያለው ታች ፣ ጨለማ ውስጥ ፣ ጭቃ ላይ ነው ። ሐዋርያትም ዱሩን ዓለም በቃሉ ሰይፍ ሲመነጥሩ ብዙ መከራና ስቃይ ተቀብለዋል ። ዛሬ በነጻነት እየኖርን ከሆነ ስለ እኛ የታሰሩ አሉ ማለት ነው ። ከበደል በኋላ ሕይወት ያለ ቤዛ አትቆምም ። እንስሳት እንኳ በየዕለቱ ይሞታሉ ። ሰው ሥጋ እወዳለሁ ሲል እንስሳት እየሞቱ መሆኑን አያስተውልም ። እኛ በሥጋ እንድንኖር እንስሳት ይታረዳሉ ። በእጃችን ያሉ መልካም ነገሮች የመከራችን ፍሬዎች ወይም ሌሎች ስለ እኛ ዋጋ ከፍለው በነጻ ያገኘናቸው እሴቶች ናቸው ።

አባቶች፡- “ነቢያት መደመዱ ፣ ሐዋርያት ገደገዱ” ይላሉ ። መመድመድ ጫካውን መመንጠር ነው ። መገድገድ ደግሞ ቤት ለመሥራት ምሰሶ ማቆም ፣ ማገር መደርደር ነው ። የነቢያትና የሐዋርያት አገልግሎት ተናባቢ ነው ። ጫካውን ዓለም መንጥሮ ቤት መሥራት ነው ። የተሠራውን ቤት መጠበቅ ፣ መንከባከብ ፣ ሲቆሽሽ ማጽዳት ደግሞ የሰባኪዎች ፣ የእረኞችና የአስተማሪዎች ድርሻ ነው ። በአንድ ቤት ውስጥ ገቢ የሚያመጣ ፣ የሚቆጣጠር ፣ አብስሎ የሚመግብ ሦስት አካላት አሉ ። ሰባኪ እንደ አባት ተባራሪ ነው ። እረኛ እንደ እናት ተቆጣጣሪ ነው ። መምህራን እንደ ሠራተኛ መጋቢ ናቸው ። ቤቱ መሠራቱ ብቻውን ዋጋ አይኖረውም ። ቀጣይ እንዲሆን ሦስቱ አካላት መትጋት አለባቸው ። አባት ሥራ ካቆመ እናት መቆጣጠር ፣ ሠራተኛም መመገብ አይችሉም ። እናት ሥራ ካቆመች አቅርቦቱ ይባክናል ። ለወር የታሰበው በሳምንት ያልቃል ። በዚህ ምክንያት ከአባት ጋር ሰላም ይጠፋል ። አለቀ አምጣ ሲባል ያለ ጊዜው ከሆነ ምን አደረግሽው ? የሚል ቍጣ ይከተላል ። አባት ቢያመጣ ፣ እናት ብትቆጣጠር ሠራተኛ ከሌለ ምግቡ በስሎ ሊቀርብ አይችልም ። ሰባክያንም ፣ እረኞችም መምህራንም ያስፈልጋሉ ። የእገዚአብሔር ደጅ ክፍት እንዲሆን ፣ የቤተ ክርስቲያን በሮችም ለምሕረት እንዲከፈቱ ሰባኪያን ሊበዙ ፣ እረኞች ሊተኩ ፣ መምህራን ወንበራቸውን ሊዘረጉ ይገባል ። ሰባክያን የቤት ውስጥ እስረኞች ከሆኑ ፣ እረኛ ተባርሮ በግ ነጋዴ እረኛ ከተባለ ፣ መምህራን እንጀራ አጥተው ወንበሩ ከተፈታ የቤተ ክርስቲያን ህልውና አደጋ ላይ ነው ። “ያለሽ መስሎሻል ተበልተሽ አልቀሻል” ይባላል ።

ኢትዮጵያ አትፈርስም የሚል የተለመደ ንግግር አለ ። ከተሞች እየተቃጠሉ ፣ ዜጎች በጅምላ እየተቀበሩ ኢትዮጵያ አትፈርስም ማለት እነዚህን ሰዎች ኢትዮጵያውያን አይደላችሁም ማለት ነው ። እየፈረስን ነውና ፈጥነን መንቃት አለብን ። ችግርን በስሙ እስካልጠራነው አንድንም ። በዚያው መንፈስ ቤተ ክርስቲያን ምንም አትሆንም ብለን መናገራችን የሚገርም ነው ። ሰባኪ እየጠፋ ፣ እረኛ እየታጣ ፣ መምህራን ለማኝ እየሆኑ ቤተ ክርስቲያን እየፈረሰች አይደለም ወይ? ብለን መጠየቅ አለብን ። ቤተ ክርስቲያን ማለት ምእመን ወይም ሰው ነው ። መንጋው እየተበተነ ፣ የትላንት አገልጋዮች ሳይቀር የዘመን ወላፈን ሲፈጃቸው ፣ በክህደት ሲጠመቁ እያየን በእውነት እየፈረስን ነውና ማሰብ አለብን ። ቤቱ እየተቃጠለበት ያለ ሰው መቃጠሉን አምኖ ካልጮኸ ተበልቶ ያልቃል ። “የሚነደው የተለመደ ነው ፣ አንዳንድ ጊዜ ቀይ ነገር ማየት መልካም ነው”  ካለ ነዶ ያልቃል ። ሞታችንን ከማቆንጀት ፣ ውድቀታችንን አምነን ንስሐ መግባትና በልካችን መገኘት ይገባናል ።

አቤቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ እባክህን እርዳን !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ጳጕሜን 4 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ