ውኃ ድንበር የለውም
ውኃ ድንበር ነው ፣ ውኃ ድንበር የለውም ። ከኢትዮጵያ የሚነሡ ወንዞች መረብ ተከዜ በሰሜን ምዕራብ ወደ ጎረቤት አገራት ይፈስሳሉ ። ዋቢ ሸበሌ ወደ ሱማሊያ ይፈስሳል ። የዓባይ ወንዝ ሱዳንና ግብጽን ያዳርሳል ። እኛ ብንጣላም ወንዝ አይቆምም ። ወንዝ የጠብ ደቦ አያውቅም ። ሰው ውኃ ነው ፣ ድንበር የለውም ። ድንበር የአሳብ መስመር እንጂ እግዚአብሔር የሰጠው ምልክት አይደለም ። የሰው ልጆች አንዱን ዓለም የአሳብ መስመር ሰጥተውት ፣ በጉልበት ግዛታቸውን አስፋፍተውት ድንበር ይፈጥራሉ ፣ ለዳር ድንበርም ሲጋደሉ ይኖራሉ ። ዓለማችን ከማለት አገራችን ማለትን ፣ ከዚያም አልፈው መንደራችን ወደ ማለት ደርሰዋል ። ማነስ ገደብ ካልተሰጠው አያልቅም ። ወደ ቤት ቍጥር ዝቅ ይላል ፣ ከቤት ልጆችም ግማሹ ያባት ወገን ፣ ግማሹ የእናት ወገን ሆኖ ይከፋፈላል ። የሰው ልጅ ሰፊውን ዓለም መሰማሪያው ማድረግ ሲችል ወሰኑን ያጠበዋል ፣ መላውን የሰው ልጅ ወገኑ ማድረግ ሲችል በጥቂት ሰዎች ይታጠራል ። ውኃ በሁሉም ዓለም ተፈጥሮው አንድ ነው ። ሰውም የትም ይኑር ምንጩ አንድ አዳም ነው ።
ሰው ውኃ ነው ። ውኃ ድንበር የለውም ። መንገድ የጠፋውን ሰው መንገድ አሳዩኝ ቢል የአገሬ ልጅ አይደለምና አላሳየውም አንልም ። እንደውም ከሩቅ ከመጣ እንረዳዋለን ። ወንጌልም ለአሕዛብ ሁሉ ፣ ለፍጥረት ሁሉ የተላከ መልእክት ነው ። አያልቅምና ልንሰስተው አይገባም ። ከክርስትና ውጭ ላሉትም መራራትና ማዘን ይገባል ። የተቸገረን ሁሉ መርዳት እንጂ ወገን እያየን መመጽወት ምጽዋትን ያረክሳል ። ክህነትና ሕክምና ሰውን አይለይምና አገልጋይ ስንሆን ሁሉን በፍቅር መቀበል ይገባል ። ውኃ ድንበር የለውምና የደቦ ጠብ አያውቅም ። ሰውም የተጣሉትን ማስታረቅ እንጂ ተደርቦ ማኩረፍ ፣ መጣላትና መጎዳዳት አይገባውም ። እንደ አራዊት በደቦ ማሰብና መበየን የሰውነት ጠባይ አይደለም ። ዛሬ ከእናት ጋር ወግኖ አባትን ፣ ከአባት ጋር ወግኖ እናትን መውጋት የልጆች ጠባይ እየሆነ መጥቷል ። “ልጅ ደረሰ ቤት ፈረሰ” የሚባለው ለዚህ ነው። የሚያስታርቅ እንጂ ተደርቦ የጠብ ደቦኛ ሆኖ ጠብን የሚያሰፋ በሰማይና በምድር የተጠላ ነው ። እኔ የተጣላሁትን ሰው እገሌም ይጣላው ማለት ተገቢ አስተሳሰብ አይደለም ። ሁሉ የራሱ የሆነ አስተሳሰብና ነጻነት አለው ። የሥራ ደቦ እንጂ የጠብ ጂጊ ተገቢ አይደለም ።
ውኃ ይታከማል
ውኃ በሄደ ቍጥር እየጠራ ይመጣል ። ሰውም ውኃ ነውና በኖረ ቍጥር እየበሰለ ፣ ዕይታው እየጎላ ፣ አስተሳሰቡ እየነጠረ ፣ አነጋገሩ እየረቀቀ ይመጣል ። መኖር ለለውጥ ነው ። በየቀኑ አንድ ነገር ማወቅና አንድ በጎ ሥራ መሥራት መኖርን ለማሟላት ነው ። ውኃ ሊቆሽሽ ይችላልና ይታከማል ። ውኃ ታክሞ ይድናል ። ቆሻሻ ተብሎ ተሸኝቶ መልሶ ንጹሕ ሆኖ ይመጣል ። ጭቃ ላይ ወድቆ እንደገና ተነሥቶ ሰዎችን ያረካል ። ሰው ውኃ ነው ፣ ሊቆሽሽ ፣ ሊሳሳት ይችላል ። የሰው ውድቀት የሚደንቀው ሰው ያልሆነ ብቻ ነው ። ቄስም መነኵሴም ቢሆን ሰው ነውና ይሳሳታል ። ካህኑና ምእመኑ የጸጋ ልዩነት እንጂ የሰውነት ልዩነት የላቸውም ። ንጉሥና ሚኒስትር መነሻቸው ሰው ነውና ከሰው ውጭ ሊሆኑ አይችሉም ፣ ስለዚህ ሲቆሽሹ ይታጠባሉ ። ካህንና ምእመንም መነሻቸው እምነት ነው ። በእምነትም ወደ መንግሥተ ሰማያት ይገባሉ ። እምነትም እኔ ኃጢአተኛ ነኝ መድኃኒት ያስፈልገኛል ብሎ ማመን ፣ መናዘዝ ፣ መቅረብ ፣ መፈወስ ነው ። ስለዚህ ያመንነው በራሳችን ፍጹም ኃጢአተኝነትና በጌታችን ፍጹም መድኃኒትነት ነው ። ታዲያ ሰው እንደሚቆሽሽ ማመን አለብን ፣ የመጣነው ስለ ቆሸሽን ነውና ። ውኃ ሲቆሽሽ ይነጻል ፣ የሚያነጻው ይነጻል ፣ የሚያክመው ይታከማል ። ሰውም ውኃ ነውና ቢቆሽሽ የሚነጻ ፣ ጭቃ ላይ ቢወድቅ እንደገና የሚቀጥል ተስፋ ሠረገላው የሆነ ፍጡር ነው ። ብዙዎችን ከስህተት ያወጣ ፣ ለብዙዎች ማረፍ ምክንያት የሆነ ሰው አንድ ቀን ስህተት ውስጥ ሊገባ ፣ አንድ ቀን ሁሉም ነገር ጥያቄ ሆኖበት ሊንከራተት ይችላል ። ብድርን መመለስ ይገባልና ልናግዘው ፣ ቀርበን ልንረዳው ይገባል ።
ትላንት ቆሻሻ ብለን የሸኘነው ፣ ላለማየት በውስጥ ለውስጥ መስመር ያባረርነው ውኃ መልሶ ንጹሕ በሌላ መስመር ይመጣል ። የትላንቱ መናፍቅ የዛሬ አማኝ ፣ የትላንቱ ስሑት የዛሬ ሰባኬ ወንጌል ይሆናል ። በሰው መለወጥ የማያምን ሰው አይደለምና ሰዎች እንደገና እንደሚቆሙ ማመን አለብን ። ወርቅን ጭቃ ላይ ወደቀ ብለው አይተዉትም ። ሰውም የሥላሴ ወርቅ ነውና ወደቀ ተብሎ አይተውም ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 26 ቀን 2017 ዓ.ም.