መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ሰው ውኃ ነው » ሰው ውኃ ነው -5

የትምህርቱ ርዕስ | ሰው ውኃ ነው -5

ውኃ መልክን ያሳያል

ውኃ ንጹሕ  ሲሆን መልክን ያሳያል፣ ሲቆሽሽ መልክን ይደብቃል። ንጹሕ ሰዎች፣ የሰከኑ ፣ ለእውነተኛው ነገር ጊዜ ያላቸው፣ ስሜታቸው የተንጠፈጠፈላቸው ፣ የሰዎችን ለውጥ ለማየት የሚኖሩ፣ በጸሎት የተጉ ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ጉዳይ ያላቸው ሰዎች እውነተኛ ማንነታችንን ያሳዩናል። ከሚጋልበው  ይልቅ በእርጋታ የሚጓዘው ፣ ከቆሸሸው ይልቅ ንጹሕ የሆነ ውኃ መልክን ያሳያል። ንጹሕ ውኃ የጠራ ውኃ ይባላል፣  የሚጠራ ተፈትኖ ፣ ተጕዞ፣ ብዙ መደፍረስን አልፎ እዚህ የደረሰ ነው። የሚንቀዠቀዡ ፣ ልባቸው የከዳቸው፣ ጥድፍ ጥድፍ ማለት የሚቀናቸው፣ በጎ ሥራን ለማድነቅ ቅንነት የጎደላቸው፣ በሰዎች ከፍታና መወደድ ታመው አልጋ የሚይዙ፣ በእውቀት ሳይሆን በማስረጃና በመረጃ የተጠቀጠቁ ሰዎች ራሳችንን ከማሳየት ይልቅ ከራሳችን ያለያዩናል።

ይህን ዓለም ሳያልፍባቸው የናቁት፣ ወልደው መሳም ሲችሉ ዘመናቸውን ለጌታ የሰጡት፣ ከጫጫታው ይልቅ ፅሞናን ዘመድ ያደረጉት ፣ የገንዘብ ፍቅር ድል የተነሣላቸው፣ በፍቅር ቢጽ የተባረኩ ፣ የክርስቶስ ሙሽሮች፣ የወንጌል ገበሬዎች፣ የጸሎት አርበኞች ራሳችንን እንድናይ የሚያደርጉን ንጹሕ ውኃ ናቸው። ቤታቸው ደሳሳ ነው፣ ዕረፍት አጥቶ ወደ እነርሱ የሚመጣው ግን ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ የሠራው ነው። ልብሳቸው አይማርክም ፣ ወርቅ የለበሱትን ግን አረጋግተው ይሸኛሉ። አባ እገሌ ጋ ልሂድ፣ መምህር እገሌን ልጠይቅ ማለት መታደል ነው። የሚያንኳኩት ደጅ፣ የሚጠይቁት ሰው ማግኘት ከላይ የሚሰጥ ነው። የሚጠየቅ መምህር፣ የሚመክር አባት፣ የሚቀበል ወዳጅ፣ የሚያርም ሊቅ ፣ የሚታፈር ሽማግሌ አታሳጣን ብሎ መጸለይ ያስፈልጋል።

በዚህ ዓለም ላይ የሚያስቀና ሰው ካለ የተረጋጋ ሰው ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ ከቀረበው ሰው ውጭስ የተረጋጋ ማን ነው? በስሌ ት ሳይሆን በእምነት የሚኖር፣ ሁሉን ፍጥረት እንደ ዘመዱ የሚያይ፣ እግዚአብሔርን የሚወዱትን የሚያከብር፣ ያለኝ ይበቃኛል የለመደ እርሱ የሚያስቀና  ነ ው፡ ፡ ልክ የለሽነታችንን፣ አልጠግብ ባይነታችንን ፣ አልረካም ብለን መንቀዝቀዦችንን በኑሮው ይገሥጸዋል::

ውኃ ሲሰክን መልክን ያሳያል። የሰከነ ሰው ያሰክናል። አሳቡ፣ ቃሉና ተግባሩ ድፍረስ ያልሆነ ሰው የሰከነ ሰው ነው። ውስጡ ፍቅርና ስስት ግጥሚያ የማይከፍቱበት፣ ቃሉ መራራና ጣፋጭ ያልሆኑበት፣ አብልቶ መልሶ የማይበላ እርሱ የሰከነ ሰው ነው። ስክነት የዕድሜ፣ የጸጋ፣ ብዙ የመፈተን ውጤት ነው። ሁሉም ነገር በተሰፈረለት ሰዓት፣ በተዘረጋለት ሀዲድ እየሄደ መሆኑን ያወቀ ፣ ፈቃደ እግዚአብሔር ይህን ዓለም አሁንም የተቆጣጠረው መሆኑን ያስተዋለ ሰው ይሰክናል። እኔ ያልኩት ለምን አልሆነም በማለት በከንቱ ትግል ራሱን አያደክምም። ከሰከነ ሰው የሚያሻግር ምክር፣ ካልሰከነ  ሰው የሚቀብር አሳብ ይወጣል። “የእብድ ገላጋይ ድንጋይ ያቀብላል” እንዲሉ።

የሰከኑ ሰዎችን ቢያንስ በሳምንት አንድ ቀን ማግኘት ዕድሜን ይቀጥላል፣ የት ነው ያለሁት ብሎ ራስን ለመገምገም ይረዳል። ውኃ ሲሰክን ንጹሕ ይሆናል፣ በእርጋታ ይጓዛል፣ መልክን ያሳያል ፣ ይጠጣል :: እኛም ንጽሕናን ገንዘብ እንድናደርግ ፣ ቃሉን እየሰማን በእርጋታ እንድንጓዝ ፣ የሰዎች የበጎነታቸው አድናቂ እንድንሆን፣ ለሌሎች ማረፍም ምክንያት አድርገኝ ብለን እንድንጸልይ ይህ ትምህርት ተዘጋጅቷል። የዚህ ትምህርት ዓላማ የተረጋጉ  ሰዎችን ማድነቅ ሳይሆን የተረጋጋ ሰው  እንድንሆን ነው!

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ሚያዝያ 2 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ