የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሰው የሆነው

“በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” 1ጢሞ. 2፡5
የሰው ልጅ በየዕለቱ ከእግዚአብሔር ጋር የሚነጋገር ፣ ድምፁንም በመስማት ፍስሐ የሚያደርግ ፍጡር ነበር ። በበደል በወደቀ ጊዜ ግን እግዚአብሔርን ከመቅረብ መሸሽ ፣ ድምፁን ከመናፈቅ መሳቀቅ ጀመረ ። የሚያጽናናው የእግዚአብሔር ድምፅ የሚያስፈራው እንደሆነ አዳም ተናገረ ። አዳም ከእግዚአብሔር ፊት ስደተኛ ሆነ ። የግል ንስሐውም ተስፋን የሚያሰጥ እንጂ ለመዳን የሚያበቃው አልሆነም ። አበው በተስፋ ተሳለሙት እንጂ መዳንን ማየት አልቻሉም ። ስለ እኛ ዘመሩ እንጂ ራሳቸውን ከሞት አላዳኑም ። በሄኖክ ፣ በኖኅ ፣ በአብርሃም ፣ በይስሐቅና በያዕቆብ ቤት ይቀርብ የነበረው መሥዋዕት ፣ ያርግ የነበረው የቤተሰብ አምልኮ ለዓለም ተስፋን እንጂ ፍጻሜን ማምጣት አልሆነለትም ። በሕግ የተቋቋመው የአሮን ክህነትም ምሳሌ የሚሆን እንጂ ክህነቱ ግዳጅ ፈጻሚ ፣ መሥዋዕቱ ምሕረት አምጪ አልነበረም ። ነቢያትም የክርስቶስን መምጣት ቢናገሩም ፣ እነ ኢሳይያስ ቀራንዮ በመንፈስ ተገኝተው ሞቱን ቢተርኩም በትንቢት መነጽር እንጂ በገሀድ አልነበረም ። እነዚህ ሁሉ አንድ ቀን እንደሚያድናቸው አምነው ሞቱ ።

እግዚአብሔርም የሰው ነገር ዕዳው የእርሱ መሆኑን ባወቀ ጊዜ አንድ ልጁን ወደ ዓለም ላከ ። አንድ ልጁም በመልክ የሚመስለው ፣ በባሕርይ የሚተካከለው ሳለ ዝቅ ማለትን እንደ ውርደት አልቆጠረም ። እግዚአብሔር ወልድ ሰው መሆኑ ለእኛ ክብር ቢሆንም ለእርሱ ውርደት ነው ። ለዚህ ሁሉ መነሻው ፍቅር ነበረ ። ፍቅር ከድሀ ቤት የሚያሳድር ፣ ለጠላት ልሙት የሚያሰኝ መሆኑን በክርስቶስ አይተናል ። ጌታችንም ማስተማሩ ፣ ተአምራት ማድረጉ የአገልግሎቱ መገለጫ ቢሆንም ቤዛነቱ ግን የተልእኮው ማሰሪያ ነው ። በትምህርቱ ምድረ እስራኤልን አዳረሰ ፣ በሞቱ ግን መላውን ዓለም ማረከ ። ዓለም በትምህርትና በተአምራት ብቻ የሚድን አይደለም ። ትምህርት ለወደፊቱ መመሪያ ነው ። ወይም ያለፈውን ማወቂያ ነው ። ተአምራት የሥጋ ችግሮችን ማስወገጃ ስለት ነው ። ቤዛነት ግን ዕዳ መክፈያ ነው ።
እግዚአብሔር የራሱን የፍትሕ ጠባይ አርክቶ ሰውን የሚያድንበት መንገዱ ቤዛነት ነበረ ። ስለዚህ ጌታችን ቤዛ ኩሉ ዓለም ሁኖ ወደ ዓለም መጣ ። እርሱም ራሱ መሥዋዕት ፣ ራሱ መሥዋዕት አቅራቢ ካህን ፣ ራሱ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ተወካፌ መሥዋዕት/ መሥዋዕት ተቀባይ/ ሁኖ አድኖናል ። አንድ መካከለኛ መኖሩ እርግጥ ነው ። በአንድ አካል መለኮትና ትስብእት የተዋሐዱት ከክርስቶስ በቀር የለምና አንድ መካከለኛ ነው ። አስታራቂነቱም በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ አንድ ጊዜ የተከናወነ ሲሆን ዘላለም ሕያው ሁኖ ያመኑበትን ሲያድን ይኖራል ። እግዚአብሔር ራሱ ሽማግሌ ፣ ራሱ ታራቂ ፣ ራሱ ካሣ ከፋይ ሁኖ አድኖናል ።
የጌታችን መካከለኛነት ወይም አስታራቂነት ፍጹም ነው ። 1600 ዓመታት የተነሡት አሮናውያን ያላገኙትን ማስታረቅ እርሱ አንዱ ችሎታል ። የቀረቡት ብዙ ሺህ መሥዋዕቶችም ያላስወገዱትን ኃጢአት አንድ ጊዜ ባፈሰሰው ደሙ ለዘላለም አስወግዶታል ። ከዚህ በኋላ ክርስቶስ የሚያቀርበው መሥዋዕት እንደሌለ ሁሉ የሚያቀርበው ልመናም የለም ። ደሙ ራሱ መካከለኛ ሁኖ ይኖራል ። ዛሬ በክብር ያለውን ክርስቶስ በጌቴሴማኒ የደም ላብ እያላበው ይቃትታል ፣ እየወደቀ እየተነሣ ይለምናል ማለት መሥዋዕቱ አልሠመረም ማለት ነው ።
ቅዱሳን የሚያቀርቡት ልመና ከክርስቶስ አስታራቂነት ጋር ልዩነት ያለው ሲሆን ተቃርኖ ግን የለውም ። ምክንያቱም ልመናቸው ኃጢአተኛው ለንስሐ እንዲበቃ ፣ ወደ ክቡር ደሙ እንዲቀርብ ነውና ። እኛ ሁላችን ስለሌላው መጸለይ እንዳለብን እናምናለን ። ይህን ግዳጅ ከእኛ በተሻለ የሚፈጽሙ ቅዱሳንም እንዳሉ መረዳት ያስፈልገናል ። ወደ ሰማይ የምንሄደው ለመላቅ እንጂ ለማነስ አይደለም ። ብቻ በቀራንዮ በፈሰሰው ደም በኩል የማይመጣ ሕይወት የለውም ። በምድር ያለነው ምስክርነት ፣ በሰማይ ያሉት ቅዱሳን ናፍቆት በክርስቶስ ቤዛነት አምኖ ፍጥረት እንዲድን ነው ።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የሆነ ነው ። ግኖስቲካውያን ሰው መምሰሉን ተቀብለዋል ። እርሱ ግን ሰው የሆነ አምላክ ነው ። ሥጋዌው መምሰል ያለበት ሳይሆን እውነት ነው ። በመምሰል ፍቅር ሊገለጥ ፣ ካሣ ሊከፈል አይችልም ። እግዚአብሔር ከእውነት ውጭ አይከብርምና ። ሰው የሆነውም ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በነሣው ሥጋና ነፍስ ነው ። ከድንግል ማርያም ሥጋ ነሣ እንጂ ነፍስ አልነሣም እያሉ ዛሬም የሚናገሩ ሰው መሆኑን አላመኑም ማለት ነው ። ሰው የሚባል ሥጋና ነፍስ የተዋሐዱት ነው ። ክርስቶስ ግማሽ ሰውነትን የተዋሐደ ሳይሆን ፍጹም ሰው የሆነ ነው ። እርሱ ራሱ ነፍሴ ተከዘች ፣ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ በማለቱ ነፍስ እንደነሣ ተናግሯል ። ሥጋን እንጂ ነፍስን አልነሣም የሚሉ የአቡሊናርዮስ ወገኖች የገዛ መለኮቱ ነፍስ ሆነው ይላሉ ። ጌታችን ግን የነፍስ ጠባይያት ታይተውበታል ። ማዘን ፣ መተከዝ ፣ መጨነቅ ፣ መፍራት እነዚህ ሁሉ የነፍስ ጠባያት እንጂ የመለኮት አይደሉም ። መለኮት በባሕርይው አይተክዝምና ። ደግሞም ክርስቶስ ዋነኛዋን በዳይ ነፍስን ካልተዋሐደ እንዴት አዳናት ብለን መናገር እንችላለን ? እርሱ ያልተዋሐደውን አያድነውምና ። ወደ ሲኦል ወረደ የምንለውም በአካለ ነፍስ ነው ። መለኮትማ መውጣትና መውረድ የለበትም ። በሁሉ የሞላ ነው ።
የብሉይ ኪዳን አማኞች እግዚአብሔር አምላክ ነው ብለው ማመን በቂያቸው ነበረ ። እኛ የአዲስ ኪዳን አማኞች ግን ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው መሆኑን ማመን ይገባናል ። ብዙ ጊዜ የሚነገረው ስለ መዳናችን ነው ። መዳን ግን መሐል ላይ የተቀመጠ አስኳል ነው ። የመዳን መግቢያው ነገረ ሥጋዌ ነው ። እርሱም ክርስቶስ ሰው የሆነበት ምሥጢር ነው ። የመዳን ፍጻሜው መቀደስ ነው ። በዳነ ማንነት መገለጥ ነው ። መዳን የእኛ ጥቅም ነው ። እርሱን ይዘን መሮጥ ግን ተገቢ አይደለም ። እንዴት ዳንን ? ስንል ነገረ ሥጋዌ ያስረዳናል ። ለምን ዳንን ? ስንል ዓላማውን ትምህርተ ቅድስና ያብራራልናል ።
1ጢሞቴዎስ /26/
ታኅሣሥ 21 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ