የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሲያስቡን እንዲደሰቱ

 “በጸሎታችን ጊዜ ስለ እናንተ ስናሳስብ፥ የእምነታችሁን ሥራ የፍቅራችሁንም ድካም በጌታችንም በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን የተስፋችሁን መጽናት በአምላካችንና በአባታችን ፊት ሳናቋርጥ እያሰብን ፥ እግዚአብሔርን ሁልጊዜ በሁላችሁ ምክንያት እናመሰግናለን” 1ተሰ. 1፡2-3
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በተሰሎንቄ አማኞች ውስጥ ያገኘውን መልካም ነገር በአድናቆት እየገለጠ ነው ። ሰዎች ክፉ ሥራቸውን ስንገልጥላቸው እንዲተዉት ሲሆን መልካም ሥራቸውን ደግሞ እንዲያበረቱት መንገር ያስፈልጋል ። ሰዎች የጎደላቸውን ነገር ከመናገራችን በፊት ያላቸውን መልካም ነገር መንገር በጣም ወሳኝ ነው ። ክስና ወቀሳ ሁለቱም አንድን ስህተት የሚናገሩ ሲሆን ዓላማቸውና አቀራረባቸው ግን ተለየ ነው ። ስለዚህ ወቀሳ የመንፈስ ቅዱስ ፣ ክስ ደግሞ የሰይጣን ነው እንላለን ። ሐዋርያው ጴጥሮስን ያገኘው መንፈስ ቅዱስ ሲሆን ይሁዳን ግን ሰይጣን አገኘው ። የሰዎችን መልካም ሥራቸውንና ሰብእናቸውን ማድነቅ ውዳሴ ከንቱ አይደለም ። ውዳሴ ከንቱ ተቀባዩ ይገባኛል ብሎ ሲቀበለውና ሰጪው ደግሞ በምስጋና አደንዝዞ ለመዝረፍ ሲጠቀምበት የሚመጣ ስህተት ነው ።
ዴማስን ከጥሪው ባስቀረችው ተሰሎንቄ ክርስቶስ ዛሬ እንደሚመጣ ሁነው የሚኖሩ ምእመናን መገኘታቸው ድንቅ ነው ። አዳም የበደለው በገነት ውስጥ ሲሆን ሎጥ ግን የተቀደሰው በሰዶም ነው ። ደቀ መዝሙሩን ባስቀረችው ተሰሎንቄ ምእመናን ደግሞ አሸነፉባት ። ሐዋርያው የተሰሎንቄን ምእመናን በጸሎት ያስባቸው ነበር ። ያዘመትናቸውን ምእመናን በጸሎት ስናስባቸው ድል የእነርሱ ይሆናል ። ከመድረክ ስንወርድ በጸሎት ማገልገልን መርሳት የለብንም ። ሙሴ ኢያሱንና ጎልማሶችን አማሌቅን ለመውጋት አሰማራና እርሱ ግን በተራራ ላይ ሁኖ ይጸልይ ነበር ። /ዘጸ. 17፡8-13/ ሐዋርያው የተሰሎንቄን አማኞች መልካምነታቸውን እንዲያጸናላቸው በጸሎት ያሳስብ ነበር ። የሰዎችን መልካምነት በጣም እያጋነንን ስናወራ ጠላት እናበዛባቸዋለን ። ስንጸልይላቸው ግን እንከልላቸዋለን ።
የተሰሎንቄ ምእመናን የእምነት ሥራ ነበራቸው ። እምነታቸው የመመጻደቅ ፣ ጸድቄአለሁ ብሎ የመኩራራት አልነበረም ። እምነታቸው ፍሬ ነበረው ። በመቀጠልም “የፍቅራችሁን ድካም” ይላል ። ፍቅር ድካም አለው ። አንድን ሰው ስንወድ ዋጋ እንከፍላለን ። ዋጋ የማይከፍልና ዋጋ ለመክፈል የማይፈልግ አፍቃሪ መሆን አይችልም ። ሐዋርያው በጌታችን በኩል ያለውን የተስፋቸውን መጽናት ያደንቃል ። ምእመናኑ ተስፋቸው ክርስቶስ እንጂ ሌላ አልነበረም ። በዚህም ተስፋ ጸኑ እንጂ አማራጭ አልፈለጉም ። ለሐዋርያው የምስጋና ርእስ ሁነውለት ስለ እነርሱ እግዚአብሔርን ያመሰግናል ። ሕይወታችን በጎ ሲሆን ለብዙዎች ይበልጥ ለመንፈሳውያን አባቶቻችን የምስጋና ርእስ እንሆናለን ።
ያለሁበት አገር ለመንፈሳዊነት አይመችም ካላችሁ የተሰሎንቄ ምእመናንን አስቡ ። አገልጋዩ እየበደለ እኔማ የምትሉ ዴማስ ኮብልሎ የጸኑትን ሰዎች አስቡ ። እምነታችሁ ሥራ የሌለው እንዳይሆን በድን ወይም ሙት እምነትን አስወግዱ ። ፍቅራችሁ ድካም የማይፈልግ ከሆነ የፍቅርን አገር ማግኘት አትችሉም ።
ጌታ ሆይ ልቤን ባንተ ፍቅር ጥመደው ። የሚመሰክር ሕይወት ስጠኝ ። ተስፋን ጥዬ እንዳልባዝን አግዘኝ ። ለዘላለሙ አሜን ።
የሰማይ ድምፅ 1
ሐምሌ 24 ቀን 2011 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.

ያጋሩ