የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሳልሄድ

“ወደማልመለስበት ሳልሄድ ዐረፍ ዘንድ ተወኝ” መዝ. 38፡13 ።

ስወለድ ለራሴ አልቅሼአለሁ ፣ ስሞት ደግሞ ሰዎች ለእኔ ያለቅሳሉ ። በልቅሶ የጀመርኩትን ዓለም በልቅሶ እጨርሳለሁ ። ስወለድ በደመ ነፍስ ፣ ዓለም ክፉ መሆኑን አውቄ ለራሴ አለቀስኩ ፣ ስሞት ዓለም የቀረብኝ መስሎአቸው ሰዎች ባለማወቅ ያለቅሳሉ ። የሕፃንነቴ እውቀት ፣ የአዋቂዎችን ማስተዋል በለጠ ። እንባ ማጠራቀሚያ ቢኖረው እስከ ዛሬ የፈሰሰው የዘረ አዳም ልቅሶ ውቅያኖስ በሆነ ነበር ። ጌታ ሆይ ! ያልከፋውና ያላዘነ ማነው ? ካንተ በቀርስ እንባን የሚያብስ ፣ የራቀውን ደስታ የሚያቀርብ ማነው ? አሳባችን አሳባችን ላይ ያስለቅሰናል ። “እንዴት እኔ ይህን አስባለሁ?” የሚለው ሙግት ያናውጠናል ። የማይታየውን ልባችንን እያየህ ሳትገልጠን ታልፈናለህ ። ልባችን ላይ የሌለውን ደግነት በአፋችን ስናንጸባርቅ ትገረማለህ ። ልባችን ላይ ክፋት ሳይኖር በአፋችን ስናበላሸው ታዝንልናለህ ። ደግ እንዳንባል ክፉ ፣ ክፉ እንዳንባል ደግ ሁነን ሚና የለሽነታችን ያሳዝንሃል ።

እውቀት የሌለበት ጉዞአችን ክለሳ እያበዛ ዕድሜአችንን በላብን ። የክፋት ሥራችን መልሶ እኛን እየጎዳን እግራችንን በእሾህ አደማብን ። ብንራመድም የምናነክስ ፣ ብንጎርስም የማንጠግብ ነን ። የተለወጠ ጉዳይ እንጂ ጉዳይ ያልቀረልን ተወዛዋዥ ሬሳ ነን ። ስንቱን ቀረብን ፣ ስንቱን ራቅነው ። ለማይሞላ ኑሮ ስንቱን ሆንነው ። ተመልሰን ወደዚህ ምድር አንመጣም ። ያበላሸነውን ለማረም ፣ የምንወዳቸውን ለማግኘት አንመለስም ። መንገዱ አንድ ነው ። መሄጃ እንጂ መመለሻ የለውም ።
ሞትም የሰው ልጅ ዕጣ ሁኗል ። ያልሞቱት ሄኖክ ኤልያስም ሊሞቱ ይመጣሉ ። አንተ መድኃኔ ዓለምም ሥጋ ለብሰህ ሞተሃል ። እኮ ማን ይቀራል? እባክህን ወደማንመለስበት ሳንሄድ ፣ የሞት ጉዞን ሳንጀምር እናርፍ ዘንድ ተወን ። በማኅፀን እያለን የምንሰማው የጥይት ድምፅ ሸብተንም እንሰማዋለን ። ሰንሰለታማው ችግር ፣ በራስ ወገን ሲገረፉ መኖር ደክሞናል ፤ እባክህ ወደማንመለስበት ሳንሄድ እናርፍ ዘንድ ፍቀድልን ። የዓመት ፈቃድ ሳይሆን የዕድሜ ፈቃድ ስጠንና አሳራፊው ሆይ እባክህ አሳርፈን ! አሜን ጽናትህን ደጅ እንጠናለን !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ