የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ስመ ብዙ ዮሐንስ መጥምቅ

ዮሐንስ ካህን ነው ። በብሉይ ኪዳን የክህነት ሐረግ ቢሄድ ሊቀ ካህናት የሚሆን የአባቱን መንበር የሚወርስ ነው ። እርሱ ግን ሊያድኑ የማይችሉ የብሉይ ኪዳን መሥዋዕትን የሚያሳርግ ሳይሆን የአዲሱን ኪዳን መሥዋዕት ክርስቶስን የሚያስተዋውቅ ሐዲስ ካህን ነው ። ክርስቶስ በግ ሁኖ ቢመጣ እርሱን የሚያሳርግ ካህን ግን አልነበረም ። ስለዚህ ራሱ ካህን ፣ ራሱ መሥዋዕት ፣ ራሱ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር መሥዋዕት ተቀባይ ሁኖ አዳነን ። እንዲህ ያለ ካህን አላየንም ። ምሕረት የሚሰጥ ፣ ለዘመኑ ፍጻሜ የሌለው ፣ ዐረፍተ ዘመን የማይገታው ካህን አላየንም ። ክህነትና ንግሥና በሕግ ተለያይተዋል ። ከሕግ በላይ የሆነው ፣ ሕግን የሰጠው እርሱ ግን ካህንም ንጉሥም ነው ። አንድ ጊዜ የተሠዋው ይህ በግ ወደ ኋላ ተመልሶ ከአዳም ጀምሮ ያሉትን ያዳነ ፣ ወደ ፊት ገሥግሦ እስከ ምጽአት ያሉትን ኃጢአተኞች የሚቀበል ነው ። ዮሐንስ ካህን ነው ። ካህኑ ዮሐንስ ሊቀ ካህኑን አስተዋወቀ ።

ዮሐንስ ባሕታዊ ነው ። ብቸኛ/ባሕታዊ ነው ሲባል ሰው ጠልቶ ገዳም የገባ አይደለም ፣ የጸሎት ዘብ ለመሆን የመነነ ነው ። ወታደር በበረሃ ተቀምጦ አገሩንና ሕዝቡን ይጠብቃል ። ወታደር የሚጠብቀው ከሚታይ ጠላት ነው ። ዮሐንስና የመንፈስ ልጆቹ ግን በብሕትውና ሆነው ሕዝባቸውን በጸሎት ይጠብቃሉ ። የጸሎት መሣሪያም ከሚታይና ከማይታይ ጠላት የሚታደግ ነው ። አገርን በጸሎት የሚጠብቁ ያስፈልጋሉ ። በጸሎት ማማው ላይ ሁነው ከሩቅ የሚመጣውን ጠላት ዓይተው የሚያስጠነቅቁ ጕበኞች/ጠባቆች/ ያሻሉ (ኢሳ. 20 ፡ 11 ።) ጸሎተኞች መኖራቸው ከራሳቸው ይልቅ ለእኛ አስፈላጊ ነው ። ሐዋርያው ሞትን መንገድ አድርጎት “ልሄድ እፈልጋለሁ” አለና፡- “ነገር ግን በሥጋ መኖሬ ስለ እናንተ እጅግ የሚያስፈልግ ነው” አለ ። (ፊልጵ. 1 ፡ 24 ።) የእግዚአብሔር ሰዎች ይበልጥ በዚህ ዘመን መኖራቸው ለእነርሱ ጉዳት ነው ። ለእኛ ግን አስፈላጊ ነው ። “እግዚአብሔር ሆይ ! ያንተን ሰዎች አታሳጣን” ብለን መጸለይ መልካም ነው ።

ዮሐንስ ሐዋርያ ነው ። ከሐዋርያት በፊት የነበረ ሐዋርያ ነው ። ሐዋርያ የክርስቶስ ምስክር ነው ። ዮሐንስም ስለ ክርስቶስ መሥክሯል ። ሐዋርያ ሂያጅ ፣ ገሥጋሽ ነው ። የምሥራቹን ይዞ ማደር የማይሆንለት ነው ። ተአምር ቢያደርግ ፣ በአዲስ ቋንቋ ቢናገር ግቡ ክርስቶስን በሰው ልብ ማንገሥ ነው ። ዮሐንስ ዝቅ ብሎ ክርስቶስን ያሳየ ነው ። ሰባኪው ረጅም ነው አሉ ። ከሰባኪው ጀርባ የክርስቶስ ሥዕል አለ ። እናቱ ይዛው ወደ ቤተ ክርስቲያን የምትሄደው ሕፃን ልጅ፡- “እማማ ይህን ሰባኪ አልወደውም” አላት ። እርስዋም ደንግጣ “ለምን ?” አለችው ። “ቁመቱ ረጅም ስለሆነ ክርስቶስን ይከልለኛል” አላት ። ዛሬም ቁመታቸው ረጅም ሆኖ ክርስቶስን የከለሉ ይኖራሉ ። ምሕረት የለሽ ሆነው እንደ መጋዝ ሲሄዱም ሲመለሱም የሚቆርጡ/ የሚበሉ ፣ የሚነግዱ አይታጡም ። ዮሐንስ ሐዋርያ ያውም ክርስቶስን ያሳየ ነው ። የጌታችን ሐዋርያት አብዛኞቹ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ነበሩ ። ጴጥሮስ ፣ እንድርያስ ፣ ዮሐንስ ፣ ያዕቆብ ፣ ፊልጶስ ናትናኤል እነዚህ ሁሉ የዮሐንስ መጥምቅ ደቀ መዛሙርት ነበሩ ።

ዮሐንስ ካህን ነው ። በሰው ድካም የማይሳለቅ ፣ የሰውን ገመና አደባባይ የማያሰጣ ፣ በሰው ቍስል የማይነግድ ካህን ነበረ ። ግን የካህን ምልክት የሚሆኑ ወርቀ ዘቦ ልብሶች አይታዩበትም ። “ወንበሩ ንጉሥ አያደርግም” ይባላል ። ሰው ዙፋን አሠርቶ በቤቱ ሊቀመጥ ይችላል ። ወንበሩ ግን ንጉሥ አያደርገውም ። ካህንን ካህን የሚያሰኘው የክህነት ወጉ ነው ። “አዋላጅና አዋቂ ያየውን ሁሉ አይናገርም” ይባላል ። የእግዚአብሔር ካህን የክርስቶስ እንደራሴ ነውና የሰውን አበሳ ይሸፍናል ። ሰውዬው ቢጋለጥ እንኳ መሥዋዕት ሆኖ ያስጥለዋል ። ሐኪም በር ዘግቶ ያክማል ፣ የሥነ ልቡና አማካሪም ምሥጢር ጠብቆ ይረዳል ። ዛሬ ግን ቪድዮ እየቀረጹ የሚያናዝዙትን ፣ አገልጋይ ነን የሚሉትን ስናይ ፤ የቤተ ክርስቲያን የበላይ ጠባቂዎች መንጋውን እንደ ተዉት ፣ ክርስቶስን እንደገና በአደባባይ ዕርቃኑን እየሰቀሉት እንደሆነ ምስክር ነው ። ዮሐንስ መጥምቅ በአደባባይ ነገር ግን ወደ ትከሻው እያቀረበ ኑዛዜ ይሰማ ነበር ። በወራጁ መሐል ያሉት ዮሐንስና ያ ምስኪን ኃጢአተኛ የሚነጋገሩት እንዳይሰማ የወንዙ ድምፅ ይከለክል ነበር ።

ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት ይባላል ። ከሁሉ የሚልቀው የማዕረግ ስሙ ይህ ነው ። ደግሞም መንገድ ጠራጊ ይባላል ። ስሙን በሹመት ያገኘው ሳይሆን በተግባር ያገኘው ነው ። ሰውን የሚገልጠው ሹመቱ ሳይሆን ጠባዩ ነው ። ጥምቀት ይህን ሁሉ ምሥጢር ይዟል ።

አቤቱ ሕዝብህን አድን !

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 29 ቀን 2016 ዓ. ም.

ያጋሩ