የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ስሞት ሳይሆን ስኖር ና

“እንደምትወደኝና እንደምታፈቅረኝ በመቃብሬ ላይ መጥተህ አትንገረኝ ፣ አሁን በቁሜ እያለሁ ንገረኝ።” /አንድ ሰው/

ብዙ ወላጆች ለልጆቻቸው ያደረጉትን በሙሉ እንዲመለስላቸው ቁሳዊ ፍላጎት ላይኖራቸው ይችላል ። ለልጃቸው የሰጡትን ፍቅር ማግኘት ግን ይፈልጋሉ ። አፍቃሪ ዘሪ ነውና የዘራውን ፍቅር ማጨድ ይፈልጋል ። ፍቅርም ተግባር እንጂ የቃላት ጨዋታ አይደለም ። የቃላት ጨዋታ ያለበት ፍቅር ከሸንጋይም ፣ ከበልቶ አዳሪዎችም ይገኛል ። እውነተኛ ፍቅር ራሱን ይፈልጋል ። እውነተኛ ፍቅር ፣ ከሐሰተኛ ፍቅር ይልቅ የተገለጠ ጠብን ያደንቃል ። ወላጆች ከልጆቻቸው የሚፈልጉት ፍቅር ጊዜ ማግኘት ፣ አብሮ ማውራት ፣ በጎዳናው ላይ ከልጆቻቸው ጋር መጓዝ ፣ በሰርግና በልቅሶ ከልጆቻቸው ጋር እንደ ጓደኛ መሄድ ፣ በሕመማቸው ሰዓት እንክብካቤን ማግኘት… ነው ። ልጆችም ብዙ ጊዜ ወላጆቻቸውን በፍቅር ሳይሆን በኃይል እንለውጣለን ብለው ይነሣሉ ። አንዳንድ ደካማ ልጆችም እኔ የምከተለውን ሃይማኖት ካልተከተላችሁ በማለት የገንዘብ ማዕቀብ በድሀ ወላጆቻቸው ላይ ያደርጋሉ ። አንዳንዶችም ለወላጆቻቸው ጊዜ ከመስጠት ገንዘብ መላክን ብቸኛ መንገድ ያደርጋሉ ። ሠራተኛ ቀጥረው በማስቀመጥ ብቻም የልጅነት ግዳጃቸውን የተወጡ ይመስላቸዋል ። ሌሎችም ከገንዘቡም ከአመሉም ድሀ ሁነው የወላጆቻቸውን መጦሪያ ይበዘብዛሉ ። ወላጆቻቸውን እያስፈራሩ የሚኖሩ ብዙ ናቸው ። ዱላ ከሚመዝዙ ጀምሮ ፣ ራሴን አጠፋለሁ እያሉ ወላጆቻቸውን አኮራምተው ያስቀመጡ አያሌ ናቸው ። መውለድ ሁሉ ደስታ ያለው አይደለም ። ወልዶ የሚቀጣ አያሌ ነው ። በቁማቸው የልጆቻቸውን ፍቅር ያገኙ ወላጆች ለሞታቸው ሥነ ሥርዓት ያስባሉ ። እዚህ ቅበሩኝ ፣ ተዝካሬን አውጡልኝ ይላሉ ። በቁም ፍቅር ያላገኙ ደግሞ ስሞት አትቅበሩኝ ፣ ዛሬ ፍቅር ስጡኝ ይላሉ ። አዎ ወላጅ ዋጋው ሊታወቅ የሚገባው መቃብሩ ላይ ሳይሆን በሕይወት ሳለ ነው ። ለጉራ የልቅሶ መሸኛ ከማድረግ ፣ ሀብትን ለማሳየት ተዝካር ከማውጣት በቁም መርዳት የተሻለ ነው ።

እግዚአብሔር ይማርህ ቀርቶ እግዚአብሔር ይግደልህ የሚላቸው ሰው አጥተው ከበሽታ ጋር ብቸኝነት የእሳት ጅራፍ ሁኖባቸው የሚያቃስቱ ወገኖች ፍቅርን ተርበዋል ። ከብዙዎች ጋር በልተው ከጥቂቶች ጋር እንኳ የመከራ ቀንን መግፋት አልቻሉም ። ለሕመማቸው ሳይመቸን ቀርቶ ለቀብራቸው ግን ከየትም ዳር ተጉዘን እንደርሳለን ። ሰው ማለት ሲወድቅ የሚረሳ ፍጡር አይደለም ። የወደቁ ዕቃዎች እንኳ እንደገና ለጥቅም ይውላሉ ። ሰው ቆሞም ፍቅርን ፣ ሞቶም መታሰቢያን ልናደርግለት የሚገባ ትልቅ ፍጡር ነው ። ለቀብሩ የመጡ አምስት መቶ ሰዎች በቀን አንድ ጊዜ ቢጠይቁት ተራው የሚደርሳቸው ባመት ከመንፈቅ ነበር ። የብዙ ብቸኞች ቀብር ሰላማዊ ሰልፍ የሚመስል ፣ የሕዝብ ማዕበል ያለበት ነው ። እነዚህ ሰዎች ግን ብቻቸውን ከሚያቃስቱበት አልጋ ላይ ሁነው ፣ የሰው ኮቴ ናፍቋቸው ፣ ጥዝጣዜአቸውን የሚያስረሳ ጨዋታ ርቋቸው ፣ እንኳን ወዳጅ ጠላት ውል ብሏቸው እያለ “በቁሜ ያልረዳኝ ስሞት አይቅበረኝ” ይሉ ነበር ። በቁማቸው ረግመውንና ገዝተውን ስለ ሞቱ በቀብራቸው ላይ የምናሳየው ትርኢት የሕሊና ዕረፍት አይሆነንም ።

ሐውልት የተሠራላቸው በቁማቸው ራእያቸው ጥፋት ፣ ፍቅራቸው ማስመሰል የሚል ስም የተሰጠው ነው ። ዛሬ የሚደነቁ ደራስያን የሚበሉት አጥተው የገዛ መጽሐፋቸውን እያቃጠሉ እሳት የሞቁ ናቸው ። በቁማቸው ፍቅራችንን ለመስማት አልታደሉም ። የሬሳ እንጂ የቁም ወዳጅ አይደለንም ። የሬሳ ክፉ አይታችሁ ታውቃላችሁ ? ደግ ነበረ ፣ ሁሉን ሰብሳቢ ነበረ እየተባለ ይነገርለታል ። በቁሙ ግን አንድም ሰው ብሎት አያውቅም ። ሲያጎርሰን እየነከስነው ፣ ሲወደን እየራቅነው ኖረን የሕይወት ታሪክ ጽሑፉን ብናስውብለት ጥቅም የለውም ። አስለቃሽ ፣ ሙሾ አውራጅ ፣ ፎካሪ ፣ ሸላይ ብንጠራ ልቅሶውን ሰርግ ብናስመስለው ፣ ዋይ ዋይ ብለን አገሩን ብናደምቀው ፣ እገሌ ዛሬ ሰርጉ ነው ብናስብልለት ይህ ሁሉ አዝኖ የሞተውን ሰው አይክሰውም ። የትላንቱን ጥፋታችንን እየደገምን ከምንኖር ዛሬ ተነሥተን ለተረፉት ፍቅራችንን እንግለጥላቸው ። እያንዳንዱ ቀን በሰማይ ላይ እንዳለ ደመና እየተጓዘ ፣ ነገ ሊሆን እየተጣደፈ ነው ።

በመቃብር ድንጋይ ላይ ለቀብር ቀን የሚመጣው ከመቶ በላይ አበባ ሰውዬው በሕይወት እያለ አንድ ጊዜ ያላገኘው ነው ። ፈረንጅ በቁም አበባ ይሰጣል ፣ እኛ ሲሞት አበባ እንሰጣለን ። በቀብር ቀን የመጣው አበባ ሟች በቁሙ በዓመት ሁለት ጊዜ ቢያገኘው ኖሮ ደስታው የላቀ ነበር ። አበባ መስጠት የእኔ ውበትና መዓዛ ደግሞም ደስታ አንተ ነህ ማለት ነው ። መቃብር ላይ የሚደረጉ ነገሮች ግን ለቋሚ እንጂ ለሟች ምንም አይጠቅሙም ። መቃብር ላይ ያሉ ትርኢቶች በእኛ አገር ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው ይመስላል ። በቁሙ ለብልበን የገደልነውን ሲሞት ዋይ ዋይ እንልለታለን ። የድርሻንን ብንወጣ ያን ያህል አንቆጭም ነበር ። ሞት መቀበል ባንፈልገውም በሰው ታሪክ ውስጥ ያለ ሐቅ ነው ። በቁሙ ረድተነው ሲሞት ነጭ ብንለብስ ክብር ነው ። ከሞት ጋር የሚታገል የለምና ። የዓለማት ፈጣሪ የሕይወት ባለቤት የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳ በለበሰው ሥጋ ሞትን ቀምሷል ። እመቤታችንም ከፍጥረታት ሁሉ የተባረከች ሳለች ሞትን ቀምሳለች ። ሞት የሰው ሁሉ ዕጣ ነው ። ያኛውን ዓለም ለማየት ሞት ድልድይ ነው ። ትንሣኤም የሚኖረው ሞት ሲኖር ነው ። የተወለድን ቀን በውስጥ መስመር እንደምንሞት ተነግሮናል ። የተወለደ ሁሉ ይሞታል ፣ የሞተ ሁሉ ይነሣል ። ያመነ ሁሉ ትንሣኤ ዘለክብርን ያገኛል ።

ፍቅራችን ለመግለጥ መድረኩ በቁም እንጂ በሞት አይደለም ። ወዳጅን መሸኘት ተገቢ ቢሆንም ቀድመን በሕሊናችን የሸኘነውን አሁን በአካል መሸኘት ፋይዳ የለውም ። የምንወዳቸውን እንደምንወዳቸው የቁርጡ ቀን ሞት አይንገረን ። እንደምንወዳቸው በመቃብር አበባ ሳይሆን ቀርበን በማጫወታችን እንንገራቸው ። እንደምንወዳቸው ቀብራቸውን በማስዋብ ሳይሆን ኑሮአቸውን በማስዋብ እንግለጥላቸው ። አዎ የምንቀብረው ለሟች ብለን ሳይሆን ለራሳችን ብለን ነው ። ለሰውዬው ለራሱ ፍቅራችንን የምንገልጠው በቁሙ ነው ። ጊዜውም ዛሬ ፣ ሰዓቱም አሁን ነው ።

“እንደምትወደኝና እንደምታፈቅረኝ በመቃብሬ ላይ መጥተህ አትንገረኝ ፣ አሁን በቁሜ እያለሁ ንገረኝ።”

የብርሃን ጠብታ 20

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 2 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ