የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሽቅብ ያረገው ጌታህ

“ወደ ምድር ታችኛ ክፍል ደግሞ ወረደ ማለት ካልሆነ ፥ ይህ ወጣ ማለትስ ምን ማለት ነው ? ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው ።” ኤፌ. 4 ፡ 9-10 ።

ወዳጆቻቸውን በሞት አጥተው የመቅበር ዕድል ያላገኙ ሰዎች ኀዘናቸው ድርብ ሁኖ ይሰማቸዋል ። መቼም በሞት የምንጽናናው ሁላችንም የምንሞት በመሆናችን ነው ። መንገደኛ ፊትና ኋላ ነውና እነርሱ ሄዱ ፣ እኛም እንከተላለን ። መቼ እንደምንሞት አናውቅም እንጂ እንደምንሞት እርግጠኞች ነን ። ታዲያ የቀበሩ ሰዎች ልክ ግብአተ መሬት ሲፈጸም ሲያዩ ልባቸው ይቆርጣል ። መቅበር ቃል ኪዳን ነው ቆራጥ ያደርጋል ። ቃል ኪዳን ስናደርግ ይፈልጉን የነበሩ ተስፋ ይቆርጣሉ ፣ እኛም ሌሎችን ለመሻት ተስፋ እንቆርጣለን ። ቃል ኪዳን ለብዙዎች ሞቶ ፣ ለአንዱ መኖር ነው ። ቃል ኪዳን ከሌለ እምነትና አገልግሎት ይፈታል ። ቃል ኪዳን ካለ ግን ቆራጥነት ይከተላል ። ቃል ኪዳን በአደባባይ ሲደረግ ይበልጥ ጽናት ይኖረዋል ። ስለ ራሱ ቢልፈሰፈስ እንኳ የሰሙትን ሰዎች እያፈረ ወደፊት ይገፋል ። መቅበር ቃል ኪዳን ነውና ልብን ያስጨክናል ። ጌታችን በተቀበረ ጊዜም የቀበሩት ሆዳቸው አልቆረጠላቸውም ። ያጸናቸው ትንሣኤው ነው ። እርሱ ከመሞቱ አስቀድሞ ከሞትሁ በኋላ በሦስተኛው ቀን በገሊላ እንገናኝ ብሎ ተስፋ ሰጥቷል ። ከሞት በኋላ ቀጠሮ የሰጠ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው ። በገሊላ እቀድማችኋለሁ ብሎ ነበር ። የቆሙትን የሞተውና የተነሣው ክርስቶስ ቀደማቸው ።

በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ከደረሱት አሳዘኝ ክሰተቶች የተወሰኑትን ብናነሣ መልካም ነው ። በበረት መወለዱ አስገራሚና አሳዛኝ ነው ። በረት ለዓይንና ለአፍንጫ የማይስማማ ነገር ያለበት ነው ። የሚታየው አያምርም ፣ የሚሸተውም መዓዛ የለውም ። በመንገድ ላይ የተወለዱ ፣ አውሮፕላንና መርከብ ላይም የተወለዱ ሰዎች ይኖራሉ ። ጌታችን ግን የተወለደው በበረት ነው ። ይህም ዓለም ከጠዋቱ ለእርሱ የሚሆን ቦታ እንደሌላት ማሳያ ነው ። ሁለተኛው አሳዛኝ ክስተት መሞቱ ነው ። የማይሞተው አምላክ በለበሰው ሥጋ መሞቱ ፣ ለአልዓዛር ትንሣኤን የሰጠ ጌታ መሞቱ ፣ ሙታንን ያድን ዘንድ መሞቱ ፣ መሞትን በሞት ይሽር ዘንድ መሞቱ አስገራሚ ነው ። የማንም ሰው ሞት መርዶ ይሆናል ። የጌታችን ሞት ግን የነገረ መለኮት ሐቅ ነው ። ገና ተመርምሮ ያልተደረሰበት ነው ። ኢመዋቲ ነፍስን የሰጠን ፣ መላእክትን የማይሞቱ  አድርጎ የፈጠረ እርሱ ሞተ ። ሰው በበደሉ የቀመሰውን የሞት ጽዋ እርሱ በፍቅር ቀመሰ ። በበረት በመወለዱ ከሰው ልጆች ሁሉ ያነሰ መሰለ ። መላእክትን የማይሞቱ አድርጎ የፈጠረው እርሱ በመሞቱ ከመላእክት አነሰ ተባለ ። ዓለም በክርስቶስ ሞት በዓይኑ እያለቀሰ ፣ በልቡ ይስቃል ። ማልቀሱ ፍቅሩ ኃያል በመሆኑ ፣ መሳቁ እርሱ ባይሞት ድኅነት ባለመኖሩ ነው ። እሰይ ሞተልን ለማለትም መብት አለን ። በትምህርቱ እስራኤልን የማረከ በሞቱ ዓለምን ማረከ ። ሞት የዓላማ መነሻ እንጂ መጨረሻ አይደለም ። ሰዎች ባለ ራእዩን ሊቀብሩ ይችላሉ ፣ ራእዩን መቅበር ግን አይቻልም ። እውነት ሲያፍኗት ይብስባታል ።

ጌታችን በተውሶ መቃብር መቀበሩ ሌላው አሳዛኝና አስገራሚ ክስተት ነው ። ዕድርም አልነበረውምና የቀበሩት ሁለት ሰዎች ናቸው ። ከመስቀል አውርዶ መቅበር ምን ያህል ከባድ መሆኑን እነዚያ ሁለት ሰዎች ያውቁታል ። አንደኛውም ዮሴፍ ዘአርማትያስ መቃብሩን ለቀቀለት ። በአዲስ መቃብር ተቀበረ ። በድንግል ማኅፀን ያደረው ፣ በድንግል መቃብር ተቀበረ ። ማኅተመ ድንግልናዋን ሳይፈታ ከቅድስት ማርያም የተወለደው መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል ተነሣ ። ልደትና ትንሣኤ ተናባቢ ናቸው ። የትንሣኤ መነሻ ልደት ፣ የልደት ግብም ትንሣኤ ነው ። ጌታችን በእውነት ሞተ ። መቃብሩ በእውነት መሞቱን ይናገራል ። ሞቱ ምትሐት ከሆነ ሰው አልዳነም ማለት ነው ። እውነት ባልሆነ  ነገር መዳን የለምና ። ስምዖን የቀሬናው መስቀሉን አገዘው እንጂ ሞቱን አላገዘውም ። የተነሣው የሞተው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። ትንሣኤ የሚኖረው ከሞት በኋላ ነው ። ያልሞተ ተነሣ አይባልም ። ወደ መቃብር የወረደውና ወደ ላይ ያረገው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። በዚህም ሥጋውን በመቃብር ጥሎ በሌላ ሥጋ ተነሣ የሚሉትን መናፍቃን ድል ነሥቷል ። በእኛ ሥጋ ካልተነሣ ትንሣኤያችን አጠራጣሪ ነው ። ክርስቶስ ካልተነሣ አንነሣም ።

ክርስቶስ ካልተነሣም የሥጋ ዕዳ አልተከፈለም ማለት ነው ፣ ሥጋ እንዳይሞት ሁኖ ተፈጥሮ በአዳም በደል ሞተ ፣ በክርስቶስ ተነሣ ። እርሱ ዳግመኛ የሚመጣው የተዋጋ ጎኑን እያሳየ ነው ። ስለዚህ በሞተበት ሥጋ እንደ ተነሣ ፣ እንዳረገ ፣ በየማነ አብ እንደ ተቀመጠ ፣ ዳግመኛም እንደሚመጣ እናምናለን ።

ጌታችን ከሰማያት በላይ ከፍ ከፍ ያለው ከምድር በታች ተቀብሮ ነው ። ይህም አንደኛ ሥጋ መልበሱን ያሳያል ። ሥጋ ባይለብስ ተቀበረ ፣ ዐረገ አይባልም ነበርና ። መቀበሩ በአማን መሞቱን ያሳያል ። ይህም ጌታችን በሞቱ ትርኢት ያሳየ ሳይሆን ቤዛ የሆነ አዳኝ መሆኑን ይገልጣል ። ዳግመኛም ከመሬት በታች የተቀበሩ ባለ ራእዮች እንደሚነሡ ያበስራቸዋል ። እያንዳንዱ የክርስቶስ እርምጃ ለክርስቲያኖች ትምህርት ፣ ዋስትና እንዲሁም ቤዛነት አለውና ።

ጠላቶች ገደልነው ብለው የፎከሩብህ አንተ ሆይ እባክህ ስማኝ ። ወደ ላይ ለመውጣት ወደ ታች መውረድ አለብህ ። ፎቅ ወደ ላይ የሚያድገው ወደ ታች በወረደ መጠን ነው ። ቀስት ርቆ የሚሄደው ወደ ኋላ በተለጠጠ መጠን ነው ። ጥይትም ዓላማውን የሚመታው ተንበርክከው ሲተኩሱት ነው ። ወደ ላይም የምትወጣው ወደ ታች በወረድከው መጠን ነው ። ሞተህ ካልጠበቅሃቸው በቀር አይገድሉህም ። ራሱን ለገደለ ትንሣኤ የለም ። ሰዎች የገደሉት ግን ይነሣል ፣ ከፍ ከፍም ይላል ።

ጌታዬ ሆይ ! ገዳዮችህ እያዩህ በደብረ ዘይት ሽቅብ ለማረግህ ሰላም እላለሁ !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ጳጕሜን 1 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ