የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ቀራጩ ማቴዎስ

/ማቴ. 9፡9-13/
ቀረጡን ለመክፈል እጁን የዘረጋው እስራኤላዊ ማቴዎስን እንዲህ አለው፡- “በአጭሩ የተቀጨው የመቄዶንያው ጀግና ፣ የእስክንድር መንግሥት ቀጣይ የሆነው በአካል ሳይሆን ልቡናን በሚገዛው የግሪክ ጥበብ ነበር ። ዓለም ተረኛ ታላቅ እንጂ ቋሚ ታላቅ የላትምና የሮም መንግሥት ተተካ ። የሮም መንግሥትም ሰላምን በማስፈኑ ፣ ፍርድን በመስጠቱ ፣ በመላው ዓለም የመዘዋወር መብትን በማስከበሩ ፣ ሰላምን በሚመለከት ለሃይማኖቶች ሥልጣን በመስጠቱ ተወዳጅ ሁኖ ነበር ። እስራኤልም የመጣው ኃይለኛ አገዛዝ አላለፋትም ነበር ። ኢየሩሳሌምን ሳይዙ ትልቅነት የሚያገኙ የማይመስላቸው ብዙ ኃያላን ገዝተዋታል ። የግብጽ ፣ የአሦር ፣ የባቢሎን ፣ የፋርስና ሜዶን ጥምር መንግሥት ፣ የፋርስ ፣ የግሪክ ፣ የሮም የአገዛዝ ቀንበር አላለፋትም ነበር ። ለመከራ የተጻፈች ይመስል እስራኤል ብዙ የመከራ ዓመታትን አሳልፋለች በእግዚአብሔር መወደድ ማለት መከራ የሌለው ሕይወት ማግኘት አይደለም ፣ በእቶን ውስጥ ተፈትኖ ማለፍ ነው ። አጥፊው ሳያጠፋት እስራኤል ዛሬም አለች ።”

ማቴዎስም በጽሞና አዳመጠ ፣ ትዕግሥቱ እውቀት ያለው ስለነበር ውስጡ አይጎዳም ። አስገባሪው የሮም መንግሥት ግብር አነሰብኝ እያለ ይነዘንዘዋል ፣ ግብር የሚከፍሉ እስራኤላውያን በሁለት ወገን በተሳለ የሰይፍ በንግግር ይቆራርጡታል ። ወዲህ ግብሩ በዛ ፣ ወዲህ እንዴት ለሮም መንግሥት ቀረጥ ሰብሳቢ ትሆናለህ ? ይሉታል ።
እልፍዮስ ልጁን በአገር ፍቅር ስሜት ያሳደገ ሰው ነው ። በጣም የሚወዱት ልጅ ብዙ ስም አለውና አንድ ጊዜ “ማቴዎስ” ይለዋል ። ሌላ ጊዜም “ሌዊ” ይለዋል ። የደጅ ሰዎችም “የእልፍዮስ ልጅ” እያሉ ይጠሩታል ። አሁን ግን “ቀራጩ ማቴዎስ” ተብሎ ሲጠራ እልፍዮስ በሰማ ቊጥር ያዝናል ። ልጁ ቅን ቢሆንም ቅንነቱ ከሕዝብ ነቀፋ ነጻ አላደረገውም ። ማቴዎስ ሁሉን በቅንነት የሚያይ ፣ ለነገሮች በጎ ትርጉም በመስጠት የሚደሰት ሰው ቢሆንም ለሮማ መንግሥት ግብር ሰብሳቢ በመሆኑ ወዲህ እንደ አገር ሻጭ/ባንዳ ወዲህ ገንዘብ አምጡ ባይ በመሆኑ የተጠላ ነበር ። እንኳን ለጠላት መንግሥት ይቅርና ለራስ መንግሥትም ግብር የሚሰበስቡ የተወደዱ አይደሉም ። እልፍዮስም ማኅበራዊ ተቀባይነትን እንዳያጣ ልጁን ቢመክርም ልጁ ግን ከቀራጭነት ሥራው መላቀቅ ፈቃደኛ አልነበረም ። በአንዳንድ ወጣቶች ዘንድ የሮማውያን ወዳጅ መሆን እንደ መሰልጠን ይታይ ነበር ። ይህ ብቻ አይደለም ። ከሰባ ዓመት በላይ የሆነውን የሮማ መንግሥት አገዛዝ እነርሱ ሥራ አንሠራም በማለት እንደማይጥሉት ያስቡና ወደ ቀራጭነት ሥራ ይሰማሩ ነበር ። ገንዘብ አምጡ ሲባል ጠላት እንኩ ሲባል ወዳጅ የሚያፈራ ነው ። ቀራጮች አምጡ የሚሉ ነበሩና ተወዳጅ አልነበሩም ። ኃጢአተኛ ለማለትም ሌላኛው መጠሪያ “ቀራጭ” የሚል ነው ። “አምላኬ ሆይ ቀራጭ ስላላደረግኸኝ አመሰግንሃለሁ” የሚል ጸሎት ከእስራኤል ምድር ወደ ሰማይ መንበር በየዕለቱ በአእላፋት ይላክ ነበር ። ማቴዎስ ግን ለዘብተኛ ሁኖ ኑሮውን ይኖራል ። እርሱ ይተኛል ሰዎች ግን በእርሱ ሥራ እንቅልፍ አጥተው ነበር ። እልፍዮስም ልጁ ማቴዎስ ምክሩን እንቢ ባለ ጊዜ ሁለት ነገር ከማጣት ልጁን ልጄ ብሎ ለመኖር ወስኖ ነበር ።
ማቴዎስ የፈካ ፊት አይቶ አያውቅም ። ወዲህ ሮማውያንን ያገኙ የሚመስላቸው ሰዎች ክፉ ፊት ያሳዩታል ፣ ግብር አይገባንምና በዛብን የሚሉም ይገላምጡታል ። ነገር ግን አስገድዶ ግብር ያስከፍላል ። መንግሥት ያለ ግብር ድሀ ነው ። አገር የሚያለማው ፣ ሠራዊት የሚቀልበው ፣ ሰላም የሚያስከብረው በግብር አማካይነት ነው ። ሕዝቡ ግን ሊበሉት ግብር የምከፍለው እያለ ሌቦችን እያሰበ ሌባ ይሆን ነበር ። ግብር ቅድመ ሁኔታ የሚጠየቅበት ሳይሆን ግዴታ ነው ። ይልቁንም የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ፣ ለመንግሥትን ለመንግሥት መስጠት የሁለት ዓለም ዜጋ መሆንን የሚገልጥ ነው ። ለእግዚአብሔርም ለመንግሥትም አልገብርም የሚል የሁለት ዓለም ስደተኛ ነው ። አማኝ መልካም ዜጋ መሆንም ይገባዋል ። የመንግሥት ሥርዓት የእግዚአብሔር ሥርዓት ነውና ግብርን መክፈል እግዚአብሔርን ማክበር ነው ። ማቴዎስ በዚህ ሁሉ አሳብ ልቡ ይንገላታ ነበር ። አሳቡን መቅዘፍ ሲያቅተው በረጅሙ ተንፍሶ ወደ ሌላ አሳብ ይሻገራል ።
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ማቴዎስ እየተቃረበ ሲመጣ ማቴዎስ አላየውም ነበር ። ምንጊዜም በማየት ቀዳሚው እግዚአብሔር ነውና ቀድሞ አየው ። ጴጥሮስም ወደ ቀራጩ ማቴዎስ የሚደረገውን ጉዞ ሲያይ ከቀናት በፊት ከማቴዎስ ጋር በዓሣ ቀረጥ ጉዳይ ያደረገውን ጭቅጭቅ አሰበ ። “ጌታ አጥማጁንም ቀራጩንም ከማረከ የቀረው መንግሥቱ ነው” አለ ። “ትላንት በምድራዊ ኑሮአችን ግብ ግብ ውስጥ የነበርነውን አሁን ሊያወዳጀን ነው” በማለት ልቡ በደስታ ዘለለ ። ይህ ስብስብም ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሮማን መንግሥት ገልብጦ መሢሑ የእስራኤል ገዥ እንደሚሆን ሲያስብ ጴጥሮስ በደስታ ዘለለ ። ቀናተኛው ስምዖን የኋላው ናትናኤልም ማቴዎስን ለመጥራት የሚደረገውን ጉዞ በትንግርት ማየት ጀመረ ። እርሱ እስራኤልን ነጻ ለማውጣት ብቸኛው መንገድ የትጥቅ ትግል ነው ብሎ የሚያምን ሰው ነበር ።ማቴዎስም ለሮማ መንግሥት በማደሩ ከሮማውያን በላይ ይጠላው ነበር ። አሁን ግን በጌታ ጥላ ፣ ሁሉን በሚችለው አምላክ ክንፎች በታች ሊያድሩ ነው ። በክርስቶስ ሁሉ አዲስ ነው ። አሮጌው ነገር አልፏል ።
ማቴዎስ ከነአጀቡ ወደ እርሱ እየመጣ ያለውን ክርስቶስን አላየውም ። በነቀፋ ፣ በጥላቻ ውስጥ የማለፉን ነገር እያሰበ “ለምን ?” በሚል ሙግት ተወጥሮ ነበር ። “ለምን ?” የሚለው ጥያቄ እንደ ገደል ማሚቱ የራስን ድምፅ መልሶ ከመስማት ውጭ ምንም ፋይዳ የለውም ። ክፉ ነገር ባንፈልገውም እንደ ጥላ ይከተለናል ። ባለንበት አለ ። ይህን ዓለም ሳይሰናበቱ ከክፉ መላቀቅ አይቻልም ። ዓለሙ ትጥቅን አጠር አድርጎ የሚዋጉበት ሜዳ እንጂ በዘርፋፋ ቀሚስ የሚዝናኑበት መስክ አይደለም ። የልቡናን ወገን ማጠንከር ፣ የእምነትን መጫሚያ ማጥለቅ ይጠይቃል ። ጌታ ኑሮ አልሞላ ያለውን ጴጥሮስን ብቻ ሳይሆን ሆዱ ሞልቶ ልቡ የጎደለውን ማቴዎስንም ይፈልግ ነበር ። ጉድለቱ ለየራስ ቢሆንም ሁሉን በመልሱ የሚያሳርፈው ግን አንድ አምላክ ብቻ ነው ።
ማቴዎስም አጠገቡ ቁሞ በታላቅ ፍቅርና ስስት የሚያየውን ጌታ ባየ ጊዜ ነፍስ አልቀረለትም ። እንዲህ ባለ ፈገግታ የተቀበለው ሰው ከዚህ በፊት አልነበረም ። ያለበት ድረስ የፈለገው ፣ የመቅረጫው ወንበር ድረስ መጥቶ ያገኘው ክርስቶስ ብቻ ነበር ። ጀማው ስለ እርሱ በሚያወራው ብዙም ያልተደነቀው ፣ በሰው ሚዛን ያልመዘነው እውነተኛ ወዳጁ ክርስቶስ ነበር ። የሰው ዓለም ይሙት ሲባል ይሙት ይላል ፣ ይሾም ሲባል ይሾም ይላል ። ጌታ ግን ከሰው ማኅበር ልዩ ነው ። ታሪክን አጥንቶ ፣ አቅምን ለክቶ ሳይሆን እንዲሁ ወድዶ የሚያስከትል ነው ። ጌታም ብዙ ቃል አልተናገረውም ። ብዙ ፍቅር ያለው ብዙ ወሬ የለውም ። መውደድ የሚችል ሰው ብዙ የፍቅር ቃላትን መደርደር አይፈልግም ። ፍቅር ከቃላት በላይ ነው ። ፍቅር ስሜት ሳይሆን ተግባር ነው ። ፍቅር በራስ ሚዛን መውደድ እንጂ ዙሪያውን አዳምጦ መውደድ አይደለም ። ፍቅር አይቶ እንጂ ሰምቶ የሚያምን አይደለም ። ፍቅር ቀራጩን ለንስሐ ፣ ዘማዊውን ለንጽሕና ይጋብዛል እንጂ ከጻድቃን ጋር ብቻ ጽዋ አይጠጣም ። ጌታችን አጭር መልእክት አስተላለፈለት፡- “ተከተለኝ!”
“ተከተለኝ” አንቀጽም አንድ መስመርም የማይሞላ የአምስት ፊደላት ውቅር ነው ። ይህ ቃል ግን ታንኳን አስጥሎ ተስፋን ያስጨበጠ ፣ አባትን አስትቶ ሰማያዊ አባትን ያስመረጠ ፣ የሚመጣውን አሳስቦ ያለውን ያስናቀ ፣ ከመንግሥት ሥራ አውጥቶ ደቀ መዝሙር ያደረገ ፣ ቀናተኛውን በትዕግሥት ያስጌጠ  ነው ። “ተከተለኝ” እኔን ያዘኝ ማለት ነው ። እንደ ዓይነ ሥውር ፣ እንደሚጠፋ ሕጻን ፣ ከተማን እንደማያውቅ ባላገር እኔን ያዘኝ ፣ የሙጥኝ በለኝ ማለት ነው ። “ተከተለኝ” በራስህ ማስተዋል አትደገፍ ፣ ትንሽ እውቀትህን አታምልክ ፣ ፈቃዴን ድል ነሺ አድርገህ እመን ማለት ነው ። “ተከተለኝ” ያልሁት ብቻ ይሁን ማለትን ተው ፣ የጨበጥከውን ሳይሆን የሚመጣውን እመን ማለት ነው ። “ተከተለኝ” መረጃን ሳይሆን ቃሉን ፣ ማስረጃን ሳይሆን ስርየተ ኃጢአትን እመን ማለት ነው ። “ተከተለኝ” እኔ በቀደምሁበት ውጣ ፣ በሌለሁበትም ጉልበት አታባክን ማለት ነው ። “ተከተለኝ” ከዚህ በኋላ ለምድራዊ መንግሥት ሳይሆን ለሰማያዊ መንግሥት ታድራለህ ማለት ነው ። “ተከተለኝ” ስፍራህን ልቀቅ ፣ የከበበህን የጥላቻ ድምፅ ትተህ በአዲስ ዓለም ለመኖር ተነሥ ማለት ነው ። “ተከተለኝ” ማቄን ጨርቄን ሳትል መንን ፣ ውጤቱን ሳታስብ አምነኸኝ ውጣ ማለት ነው ።
ይቀጥላል
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ