ማክሰኞ፣ ጥር 15 2004 ዓ.ም.
ባለፈው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በጀመርነው ጽሑፋችን የኢትዮጵያ ንጉሥ የነበሩት አፄ ቴዎድሮስ ለመጽሐፍ ቅዱስ ያላቸውን ጽኑ ፍቅርና ክብር በተመለከተ የታሪክ ሰነዳችንን በመፈተሽ አንድ ጽሑፍ አቅርበን ነበር፡፡ በዚህም ብዙ አንባቢዎቻችን እንደተደሰቱና የሚበዙት ነገሥታቶቻችን በታሪክ ረገድ ብዙ የተነገረላቸው የጦርነትና የግዛት ማስፋፋት ታሪካቸው እንጂ ለዕውቀትና ለጥበብ ሥራዎች እንዲሁም ለሥነ ጽሁፍ ያላቸውን ልዩ ዝንባሌና ትኩረት የታሪክ ጸሐፍቶቻችን እምብዛም ትኩረት የሰጡት አይመስሉምና፤ እስቲ ሌሎችም ነገሥታቶቻችንን በተመለከተ የታሪክ ድርሳናትን እየፈተሻችሁ ብታቃምሱን ባሉን መሠረት ለዛሬም ይኸው እስከ 1966 ዓ.ም. የሀገራችን ንጉሥ የነበሩትን ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ለቅዱሳን መጻሕፍት ያላቸውን ፍቅርና አክብሮት እንዲሁም ቅዱሳን መጻሕፍትን ለመመርመርና ሌሎችም እንዲያውቁት በማድረግ ከሀገር ውስጥ አልፈው በውጭ ሀገራት ጉብኝታቸው ጭምር መጽሐፍ ቅዱስን የክብር ስጦታ በማድረግ ለውጭ ሀገራት መሪዎችና ታዋቂ ሰዎች በማበርከት ያደረጉትን አስተዋጽኦ በአጭሩ ልናስቃኛችሁ ወደድን በዚህ ቀጣይ መጣጥፋችን፡፡
በእርግጥ በታሪካችን እንደምናውቀው የሚበዙት የኢትዮጵያ ነገሥታት ከቤተ ክህነት ጋር ካላቸው የላቀ ግንኙነት የተነሣ በማንበብና በመጻፍ ረገድ የሚታሙ አይደሉም፡፡ አንዳንዶቹ ነገሥታቶቻችንም የተለያዩ የሃይማኖት፣ የጥበብ እና የፍልስፍና ድርሰቶችን በማበርከት ለቤተ ክርስቲያናችንና በአጠቃላይም ለሀገራችን ሥነ ጽሑፍ የላቀ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ የታሪክ ድርሳናት እና እስከ ዛሬም ከብዙ ትውልድ በኋላ በእጆቻችን የሚገኙት መጻሕፍቶቻቸው ሕያው ምስክሮች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ይሄ የሥነ ጽሑፍ፣ የዕውቀትና የጥበብ ትሩፋት ወደ ታችኛው ኅብረተሰብ ወርዶ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደረገበትን ሁናቴ ስንመለከት አፋችንን ሞልተን የምንናገርለት አይደለም፡፡
በተለይም ደግሞ የሚበዙት የሃይማኖት ድርሰቶቻችንና ሌሎች የምክር፣ የተግሣጽና የጥበብ መጻሕፍቶቻችን የተጻፉት በግዕዝ ቋንቋ ስለነበር፣ የአማርኛ ቋንቋ የቤተ መንግሥት ቋንቋ ከሆነ በኋላ የሚበዛው የኅብረተሰባችን ክፍል እነዚህን መጻሕፍት ሊረዳ ቀርቶ እስከ ደርግ ዘመነ መንግሥት መባቻ ድረስ የሚበዛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በመሃይምነት ጨለማ ውስጥ የሚማቅቅ ነበር፡፡ የሕዝባቸው መሃይምነትና ድንቁርና ያሳሰባቸው አፄ ቴዎድሮስ ሕዝቡ ቅዱሳት መጻሕፍትን በሚረዳው ቋንቋ ማንበብ ይችል ዘንድ መጽሐፍ ቅዱስ በአማርኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዲሰጥና ካህናቱም ኅብረተሰቡን በማስተማር የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ብዙ ጥረት ያደርጉ እንደነበር ከታሪክ ድርሳናት በመጥቀስ በባለፈው ጽሑፋችን አውስተናል፡፡ ከእሳቸውም በኋላ የነገሡት አፄ ዮሐንስም ለተዋህዶ ሃይማኖት ከነበራቸው ፍቅርና ቅናት የተነሣ ካህናቶቻቸውና ሕዝባቸው በመንፈሳዊ ዕውቀት የበረቱ እንዲሆኑ ብዙ ጥረት ከማድረግ አልፈው ሀገራቸውንና ሃይማኖታቸውን ላለማስደፈር ክቡር ሕይወታቸውን ጭምር ለመሠዋት ወደኋላ ያላሉ ንጉሥ እንደነበሩ ታሪካቸው ይመሰክራል፡፡
ከአፄ ዮሐንስም በኋላ ለዘመናት ሕዝቡን በማስተማር ታላቁን ሚና የተጫወተችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ትልቅ ኃላፊነት በመጋራት ከቤተ ክህነቱ ባህላዊ ትምህርት ባሻገር ዘመናዊ ትምህርት በአገሪቱ እንዲስፋፋ ትልቁን ሚና በመጫወት ረገድ አፄ ምኒልክ በዋናነት የሚጠቀሱ ንጉሥ ናቸው፡፡ ከእሳቸውም በኋላ ኢትዮጵያን ለረጅም ዘመን በንግሥና በመምራት የቆዩት አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመናዊ ትምህርት እንዲስፋፋና ትውልድ በግብረ ገብ የታነጸ እንዲሆን በማሰብ መጽሐፍ ቅዱስ ሕዝቡ በሚግባባበት በአማርኛ ቋንቋ በየቤቱ እንዲዳረስና ሀገራቸው ኢትዮጵያም የዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር አባል እንድትሆን በማድረግ እንዲሁም ዛሬ በብዙዎቻችን እጅ የሚገኘውና የምንጠቀምበት መጽሐፍ ቅዱስ እንዲተረጎም በማድረግ ትልቅ ባለ ውለታ ናቸው፡፡
ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከነበራቸው ትልቅ ተቀባይነትና ክብር የተነሣ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የራሷ የሆነ ቋንቋ፣ ባህል፣ ስልጣኔና አኩሪ ታሪክ ያላት ቀደምት የክርስቲያን ሀገር መሆኗን በውጩ ዓለማት ዘንድ በማሳወቅ ረገድ የተሳካላቸው ታላቅ ዲፕሎማት ሰው እንደነበሩ ብዙ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ታሪክ ጸሐፊዎች ይስማሙበታል፡፡ እኚህ ንጉሥ በሚሄዱበት ሁሉ በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት በእጅ የተፃፈ የብራና መጽሐፍ ቅዱስ ጥራዝ ለዓለማችን ታላላቅ መሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ የታወቁ ሰዎች፣ ታላላቅ ዩኒቨርስቲዎችና የምርምር ማዕከላት ያበረክቱ እንደነበር የታሪክ ጸሐፍት ይናገራሉ፡፡
የአፄ ኃይለ ሥላሴን ዓለም አቀፍ ሰብእና፣ የተዋጣላቸው ዲፕሎማትና ከውጭ ሀገራት ጋር የነበራቸውን የዲፕሎማቲክ ግንኙነት በተለይም ደግሞ ከሀገራቸው ከአሜሪካ ጋር የነበራቸውን ወዳጅነትና ጉብኝታቸውን በሚጥም ቋንቋ ‹‹The Lion of Judah in the New World›› በሚል ርዕስ ይህን ድንቅዬ መጽሐፍ ስለንጉሡ በርካታ መረጃዎችን ያቀረቡልን ቲዮደር ኤም ቬስታል በስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር፣ የኦክላህማ ስቴት ዩኒቨርስቲ በፖለቲካ ሳይንስ ኤምሬት ፕሮፌሰር ሲሆኑ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት አሜሪካውያን የሰላም ጓዶችን በማስተባበር በሀገራችን በቆዩበት ወቅት ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያውያንን ታሪክና የንጉሡን ፖለቲካዊ ሰብእና እንዲሁም ዓለም አቀፍ ግንኙነት በቅርብ ለመረዳት እድሉን አግኝተው ነበር፡፡ ይህ መጽሐፋቸውም የዚሁ የኢትዮጵያ ቆይታቸው አንዱ በረከት ነው፡፡
እኚህ ምሁር ኃይለ ሥላሴ በተለያዩ ጊዜያት በአሜሪካ ያደረጓቸውን ጉብኝቶች በተመለከተ በዚሁ መጽሐፋቸው ብዙ ነገር ይነግሩናል፡፡ ፕሮፌሰር ቬስታል እንደሚነግሩን የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን እ.ኤ.አ በ1954 ዓ.ም በፕሬዝዳንት አይዘንሀወር ጋባዥነት የአሜሪካ ጉብኝታቸውን የጀመሩት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ሴኔት በሕግ የክብር ዶክትሬት በሰጣቸው ጊዜ ለዩኒቨርስቲው ማኅበረሰብ ምስጋናቸውን ካቀረቡ በኋላ ለዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት በእጅ የተፃፈ የብራና የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ በታላቅ አክብሮት ማበርከታቸውን በዚሁ መጽሐፋቸው ፕሮፌሰሩ ዘግበውታል፡፡
በተጨማሪም እ.ኤ.አ በ1967 ዓ.ም በሦስተኛው የአሜሪካ ጉብኝታቸው የካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ ቻንስለር ፍራንክሊን ዲ መርፊ አራት ሺ የሚሆኑ የዩኒቨርስቲው ማኅበረሰብና ታዋቂ ሰዎችና እንግዶች በተገኙበት ለንጉሥ አፄ ኃይለ ሥላሴ በሕግ የክብር ዶክትሬት በሰጧቸው ጊዜ ለዚህ ክብር ለዩኒቨርስቲው ቤተ መጻሕፍት በግዕዝ ቋንቋ የተጻፉ በርካታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የተለያዩ ቅዱሳት መጻሕፍትንና በብራና የተጻፉ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትን አበርክተዋል፡፡
በሴሜቲክ ቋንቋ ጥናት የተከበሩ ፕሮፌሰር የነበሩትና እንግሊዘኛ አማርኛ መዝገበ ቃላት ያበረከቱልን እውቁ የአማርኛና ግዕዝ ቋንቋ ምሁር ፕሮፌሰር ዎልፍ ልስላው በዚሁ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሰቲ መምህርና የሴሜቲክ ቋንቋ ተመራማሪ በነበሩበት ዓመታት እነዚህን የንጉሡን ስጦታ የሆኑ መጻሕፍቶችን ለጥናትና ለምርምር እንደተጠቀሙባቸው በሕይወት በነበሩበት ጊዜ ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም ከአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች መካከል እጅግ ተወዳጅ የነበሩትና በሰው እጅ ሕይወታቸው ያለፈው በጆኔፍ ኬኔዲ ጋባዥነት እ.ኤ.አ በ1963 ዓ.ም አሜሪካን የጎበኙት አፄ ኃይለ ሥላሴ በፕሬዝዳንት ጆኔፍ ኬኔዲ በነጩ ሳሎን (White House) በተደረገላቸው የክብር ግብዣና የስጦታ ልውውጥ ወቅት እጅግ ያከብሯቸው ለነበሩት ለጆኔፍ ኬኔዲ ካበረከቱላቸው ስጦታዎች መካከል ሁለት መቶ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ በግዕዝ ቋንቋ የተፃፈ የብራና መጽሐፍ ቅዱስ ጥራዝና የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት እንደሚገኙበት ፕሮፌሰር ቬስታል በዚሁ መጽሐፋቸው ይገልጻሉ፡፡
በስድስት ዓመታት ውስጥ ለሁለት ጊዜ የዓመቱ ምርጥ ሰው በማለት የለንዶኑ ታይምስ መጽሔት የመረጣቸው አፄ ኃይለ ሥላሴ ከፍ ያለ ሰብእና የነበራቸውና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ ታላቅ መሪና አባት የሚታዩ የተዋጣለቸው ዲፕሎማቲክ፣ እንዲሁም በዓለማችን ከሚገኙ ታላላቅ መሪዎችና ፖለቲከኞች ዘንድ ትልቅ ከበሬታ የነበራቸው ኢትዮጵያዊ ንጉሥ እንደነበሩ ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡ እኚህ ንጉሥ በሄዱበት ሁሉ ቅዱሳት መጻሕፍትን ከእጃቸው የማይለዩና ልዩ ፍቅርና ከበሬታ ለሚሰጧቸው ወዳጆቻቸው ከሚያበረክቷቸው መጻሕፍት መካከል መጽሐፍ ቅዱስ ዋነኛው እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ አዎን መጽሐፍ ቅዱስ ከስጦታዎች ሁሉ በላይ የሆነ ታላቅ ስጦታ ነው! መጽሐፍ ቅዱስ ለዓለማችን ነገሥታትና መሪዎች ሕዝባቸውን የሚያስተዳድሩበትን መልካም ጥበብንና ማስተዋልን የሚለግስ፣ ዘመን የማይሽረው ድንቅዬ መጽሐፍ ነው፡፡ ይህ ልዩ ቅዱስ መጽሐፍ በዘመናት ሁሉ እጅግ ተከብሮና ተወዶ የኖረ፣ የብዙዎችንም ልብና ኅሊና በመግዛት ወደር ያልተገኘለት መጽሐፍ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ለወዳጆቻችን፣ ለትዳር አጋሮቻችን፣ ለሥራ ባልደረቦቻችን፣ ለምናፈቅራቸውና ለምናከብራቸው ሁሉ የምንሰጠው ክቡርና ወድ ስጦታ ዋነኛው መጽሐፍ ቅዱስ ሊሆን ይገባዋል፤ ይህ መጽሐፍ ታላቅ ስጦታና የሕይወት መመሪያ መጽሐፍ ነው፡፡ ዘወትር በጸሎት ሊነበብ የሚገባው የዕውቀትና የጥበብ ምንጭ የሆነ መጽሐፍ ነው፡፡ እኛስ መጽሐፍ ቅዱስን ለመስጠት ያነሰ ስጦታ መስሎ ይሰማን ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ግን የንጉሥ ስጦታ ነው፡፡
እግዚአብሔር በቃሉ ትውልዳችንን ይባርክ!