የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ቃለ ውግዘት

 “ከእነዚያም ፥ እንዳይሳደቡ ይማሩ ዘንድ ለሰይጣን አሳልፌ የሰጠኋቸው ፥ ሄሜኔዎስና እስክንድሮስ ናቸው ።” 1ጢሞ. 1፡20
በሕይወት ውስጥ ትልቁ ጸሎት፡- “ጌታ ሆይ ስቶ ከማሳት ፣ ጠፍቶ ከማጥፋት አድነኝ” የሚለው ነው ። እግዚአብሔር ባለማወቅ የጠፉትን በድፍረት ከጠፉት ለይቶ ያያል ። ምንጊዜም ላልማ ብለው ያጠፉትን ላጥፋ ብለው ካጠፉት ሰዎች ለይቶ ማየት ይገባል ። ሁሉን በአንድ መነጽር ማየት በዓለም ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀልን ያመጣል ። በአንድ ክፉ ወንድ ፣ ወንድ ሁሉ ክፉ ነው አይባልም ። በአንዲት የተሳሳተች ሴትም ፣ ሴት ሁሉ መጥፎ ነው አይባልም ። “ዓሣውን ለማጥፋት ባሕሩን ማድረቅ” የሚለው አስተሳሰብ በጣም ጎጂ ነው ። ጠብን በልኩ ካላደረጉት ጉልበት ይጨርሳል ። በዓለም ላይ የተዋረዱ ነገሥታት የሚባሉት ጠብን የማይንቁ ናቸው ። የሰደባቸውን ሁሉ ፈልገው ፣ ያማቸውን ሁሉ አሳድደው የሚጎዱ ክብር ያጣሉ ። አንዳንዱ የሚሳደበው የመጀመሪያውም የመጨረሻውም አቅሙ እርሱ ስለሆነ ነው ። የሚያማውም ፈሪ ስለሆነ ነው ። ጠብን መናቅ የትልልቅ ሰዎች ክብር ነው ። በዚያው ተቃራኒ ደግሞ ክፉ ነገር ትንሽ ቢሆንም የማይናቅና ሳያድግ መፍትሔ ሊበጅለት የሚገባ ነው ። በጣት የሚነቀለው ችግኝ ካደገ በኋላ ለመጥረቢያም ያስቸግራል ።

ሐዋርያው ጳውሎስ ስማቸውን የጠቀሳቸው ሄሜኔዎስና እስክንድሮስ በስህተታቸው የማያፍሩ ወንጌል ትልቅ ናት በምትለዋ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ወንጌል ትንሽ ናት የሚሉ ፤ ክርስቶስን ወልደ እግዚአብሔር ፣ የባሕርይ አምላክ በምትል ማኅበረ ምእመናን ውስጥ ፍጡር ነው እያሉ የሚያስተምሩ ነበሩ ። ሐዋርያው ቃለ ውግዘት ከማስተላለፉ በፊት እንደመከራቸውና ወደ እውነቱ እንዲመለሱ እንደ ደከመላቸው እንረዳለን ። ውግዘት የመጨረሻ ውሳኔ እንጂ የመጀመሪያ ውሳኔ አይደለምና ።
ሠለስቱ ምእት በኒቅያ ጉባዔ የተሰባሰቡት አርዮስን ለማውገዝ ሳይሆን ለመመለስ ነበር ። አርዮስንም፡- “ይህን ነገር አስበኸው ከሆነ አትናገረው ፣ ተናግረህ ከሆነ አትድገመው” በማለት ምክር ሰጥተውታል ። ቢመለስ ብለውም የማሰቢያ ጊዜ እንዲያገኝ አድርገዋል ። ለአርዮስ ማጥፋት ብቻ ሳይሆን ለራሱ መጥፋትም አዝነዋል ። ሠለስቱ ምእት የማሰቢያ ጊዜ መስጠታቸው ፣ ቆስጠንጢኖስ ላግዘው ባለ ጊዜ አይሆንም ማለታቸው መንፈሳዊነታቸውን ያሳያል ። እነዚህ አባቶች በእውቀት ያደጉ ፣ በመንፈሳዊነት የተገለጡ ፣ በሰማዕትነት ውስጥም ያለፉ ናቸው ። አንዳንዶቹም ስለ ክርስቶስ እጅና እግራቸው ተቆርጦ በሸክም የመጡም ነበሩ ። ስለ አንዱ አርዮስ መጥፋት ያሳዝናቸው ነበር ። አርዮስ ግን ይህን ሁሉ ዕድል አግኝቶ በስህተቱ ስለጸና አውግዘው ከማኅበረ ምእመናን ለይተውታል ። ንስሐ ቢገባ ሊቀበሉት በሩንም ክፍት አድርገውለታል ።
በሃይማኖት ህፀፅ የተገኘባቸውን ሰዎች በርኅራኄ ማከም እንጂ በጭካኔ መግፋት የክርስቶስን ደም ከንቱ ማድረግ ነው ። እርሱ የጠፉትን ለማዳን ሰው ሁኗልና ደግሞም በመስቀል ላይ ውሏልና ። ወንድሜ ይዳን ቀርቶ ይጥፋ የሚል የአረሚ መንፈስ የተቆራኘው ሰው ነው ። እንደ እኔ ካላመንህ ብሎ በሰይፍ የሚቀላ ፣ በድንጋይ የሚያናግር አረሚ ነውና ። ሰዎች ሁሉ አውቀው የጠፉ አይደሉም ፣ የብዙዎች መጥፋት እውቀት ከማጣት የተነሣ ነው ። ይህም በነቢይ ቃል ተነግሯል፡- ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል/ሆሴ. 4፡6 / ። የአባቶች ተግባር አስተምሮ ማሳመን እንጂ አውግዞ መለየት አይደለም ። ውግዘት የቤተ ክርስቲያን የመጨረሻ አማራጭ ነው ። “ከሣር ክዳን ቤት አንድ ቢመዘዝ አያፈስም” የሚሉ ወጣቶች ስንቱን ሰው ከቤተ ክርስቲያን ገፍተው አስወጥተውታል ። ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ቤተ ክርስቲያን ከሃያ ሚሊየን በላይ ምእመን አጥታለች ። ሃያ ሚሊየን ሕዝብ አንድ ሣር ነው ብሎ ማሰብ በጣም የሚገርም አረማዊ መንፈስ ነው ። በስህተት ትምህርት ውስጥ ያለ ሰውን በጣም ታላቅ በሆነ ርኅራኄ መጀመሪያ ለብቻ ማናገር ይገባል ። ከዚያ እንደ ጌታችን ቃል ሁለትና ሦስት ሁነው ሊያናግሩት ይገባል ። ይህን ሁሉ ሂደት አልቀበልም ካለ ለቤተ ክርስቲያን ጉባዔ ወይም ለሲኖዶስ ማቅረብ ይገባል ። ከዚህ በኋላ ውግዘት ይደረጋል ። /ማቴ. 18፡15-17/ ። ዛሬ ግን ውግዘት በፖስታ ይላካል ። ለማስተማር የሰነፉ ለማውገዝ የበረቱ እንዳንባል አምላክ ይጠብቀን ። ሳናስተምር ያወገዝነው እርሱም በመሃይም ቃሉ ያወግዘናል ። ውግዘት አባታዊ ቅጣት እንጂ የጠላት በትር አይደለም ።
ቆስጠንጢኖስ ንጉሣዊ ሥልጣኑን መከታ አድርጎ አርዮስን ወደ ግዞት ልስደደው ባለ ጊዜ አባቶች ከልክለዋል ። ምክንያቱም ማመን አምላክ የሰጠው ነጻነት ነውና ። በመጨረሻ ግን ቆስጠንጢኖስ  በአርዮስ አሳብ ተስቦ ነበር ። ይህ የሚያሳየን መፍረድ ፣ ዘራፍ ማለት ፣ ሰውን በሃይማኖት ስም ልቅጣህ ብሎ መነሣት በመጨረሻ እዚያ ስህተት ላይ ይጥላል ። አትፍረድ ይፈረድብሃል የሚለው ለዚህ ነው ።
ከኖኅ መርከብ ውጭ ያለው ጥፋት ብቻ ነበር ። እንዲሁም ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ያለው ጥፋት ነው ። ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “ከእነዚያም ፥ እንዳይሳደቡ ይማሩ ዘንድ ለሰይጣን አሳልፌ የሰጠኋቸው ፥ ሄሜኔዎስና እስክንድሮስ ናቸው” ይላል ። ስድብ የተባለው በአምላክና በአምላክ ቃል ላይ ያደረጉት ንቀት ነው ። ለሰይጣን አሳልፎ መስጠትም በውግዘት ከቤተ ክርስቲያን መለየት ነው ። ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ግዛት ናትና ከቤተ ክርስቲያን የተባረረ ወደ ሰይጣን ግዛት መግባቱ ግድ ነው ። ከኢትዮጵያ የተባረረ የኬንያ ግዛት ውስጥ ይገባል ። ነጻ የሆነ ዓለም የለምና ። አንድ ሰው ከቤተ ክርስቲያን ሲባረር ማኅደረ መንፈስ ቅዱስ መሆኑ ይቀራል ። ስለዚህ ማኅደረ ሰይጣን ሁኗልና ለሰይጣን ተላልፎ ተሰጠ ይባላል ። ከኖኅ መርከብ የወጣ ጥፋት ብቻ እንደሚያገኘው ከክርስቲያን ማኅበር የተለየም ጥፋት ይገጥመዋል ። ትልቁ ቅጣትም በቃሉ አማካይነት የሚገኘውን የመንፈስ ቅዱስ መጽናናትና የወንድሞችን ፍቅር ማጣት ነው ።
ውግዘት በተለያየ መንገድ ሊከናወን ይችላል ። ዳኞች ጉቦ በልተው ፍርድ እንደሚያጣምሙ እንዲሁም ለሰው ያደሩ ሰዎች ሰውን እንደ ቀላል ሊያወግዙ ይችላሉ ። ነገሥታት የጠሉትን የሚያወግዙ ለቤተ መንግሥት ያደሩ መለካውያንም አሉ ። መለካዊ ማለት ሰማያዊውን መንግሥት በምድራዊ መንግሥት የለወጠ ማለት ነው ። እውነተኛ ውግዘት ግን ያስራል ፣ መንፈስ ቅዱስን ያርቃል ። ሂደቱን ያልጠበቀ ውግዘት ግን አውጋዡን ያስራል ።
ሐዋርያው እነዚህን ሰዎች ያወገዘው ከቅጣቱ የተነሣ ተምረው ለንስሐ እንዲበቁና ነፍሳቸው እንድትድን ነው ። /1ቆሮ. 5፡5/ ። በየትኛው ዘመን የቤተ ክርስቲያንን መድረክ የያዙ ሁሉ አማኞች ፣ የተገፉ ሁሉ ሐሰተኞች አይደሉም ። እውነተኛውንና የራሱ የሆኑትን ጌታ ያውቃል ። ዓለም ግን በሐሰተኛ ፍርድ ተሞልቷል ።
ፍርድ በቀል አይደለም ፣ ፍርድ ትምህርት ነው ። ውግዘትም በቀል ሳይሆን ትምህርት ነው ።
ቤዛ ኩሉ ዓለም ክርስቶስ ራሳችንን ለማየት ብርሃኑን ይላክልን ።
1ጢሞቴዎስ /22/
ታኅሣሥ 14 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ