የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ቃለ ጽድቅ

“እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል ፥ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል ፥ ሰምታችሁ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ ፥ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ ፤ እርሱም የርስታችን መያዣ ነው ፥ ለእግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እስኪዋጅ ድረስ ፥ ይህም ለክብሩ ምስጋና ይሆናል ።” ኤፌ. 1፡13-14።

የኤፌሶን ሰዎች የእውነትን ቃል ይኸውም የመዳናቸውን ወንጌል ሰምተው በክርስቶስ አምነዋል ። በዋዜማው የደከሙ ሰዎች ብዙ ጊዜ በበዓሉ ድግስ ላይ አይገኙም ። ከልፋቱ እንጂ ከበረከቱ አይታደሙም ። የኤፌሶን ሰዎች ግን ከዋዜማው አልነበሩም ። በመሥዋዕተ ኦሪት አልተለማመኑም ፣ በተስፋ አበው አልጸኑም ፣ በትንቢተ ነቢያት አንጋጠው/አሻግረው አላዩም ፣ በምሳሌ በጥላ አልታመኑም ፣ በሱባዔ አልቆጠሩም ፤ በሌሎች ድካም ግን ገቡ ። በሰኔው አዝመራ ሳይገኙ ፣ በትሣሡ አጨዳ ታደሙ ። እስራኤል ወጥተው እነዚህ መግባታቸው እግዚአብሔር በዓላማው ጨካኝ መሆኑን ያሳያል ። ደግሞም ሁሉን ለእኔ የሚልን ብሉይም ሐዲስም ከእኛ ውጭ ለሌላ አይገባም በሚሉ አይደሰትም ፤ እርሱ የአጽናፈ ዓለም ጌታ ሳለ የአጥቢያ ንጉሥ እንዲያደርጉት ባሕርዩ አይፈቅድም ። ደግሞም እስራኤል እግዚአብሔር ካደረገላቸው እነርሱ ለእግዚአብሔር ያደረጉለት በዝቶ ታይቷቸዋልና አሕዛብን በማየት እንዲሁ ወገን በሚያደርገው ጸጋው እንዲማሩ ለማድረግ ነው ። አሕዛብም እስራኤል እንኳ ወድቀዋልና እኛማ ምን ቦታ አለን ብለው ትሑት እንዲሆኑ ነው ። እግዚአብሔር በአጥፊው ጠፊውን ፣ በጠፊው አጥፊውን ያስተምራል ። አንዱን በትምህርት ፣ አንዱን በፍርድ ያሰለጥናል ።

ያመኑት በእውነት ቃል ፣ በመዳን ወንጌል ፣ በክርስቶስ ነው ። ሁሉም በጠቅላይ ቃል ሲገለጡ በክርስቶስ አምነዋል ። ለማመን ዋዜማው የእውነት ቃል ነው ። ሰው የእውነትን ቃል ሳይሰማ ቢያምንም እምነቱ በድቡሽት መሬት ወይም በአሸዋ ላይ የተመሠረተ ነው ። እግዚአብሔር የሚገለጠው በእግዚአብሔር ቃል ነው ። ስለ እግዚአብሔር ያወቅነው በልቡና ተመርኆ ብቻ ሳይሆን በተገለጠው ቃልም ነው ። የእግዚአብሔር ቃል መገለጥ ከሆነ ከምድር አይደለም ማለታችን ነው ። የመገለጥን ቃል የምንረዳው በመገለጥ ነውና ጸሎትና ትሕትና ትልቁ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ነው ። የእውነትን ቃል የመስማታችን ዓላማው እኛን የአጠቃላይ እውቀት ባለቤት ማድረግ አይደለም ። ፖለቲከኞች የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ተናገሩ የእግዚአብሔር ሰዎች ላይሆኑ ይችላሉ ። የእግዚአብሔር ቃል ንግግር ማሳመሪያ ፣ ሰውን መቆጣጠሪያ ሳይሆን ዓላማው ግለሰቡን ማዳን ነው ። መዳን ትልቅ ትርጉም ያለው ነው ። ቤተ ክርስቲያን ጉዞዋን በተስፋ ጀምራ ፣ በመዳን ፈጽማለች ። ሥጋ ወደሙ የድኅነት ማዕድ ነው ። ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ከድኅነት ጋር የተያያዙ ናቸው ። “በስንቱ ነው የሚዳነው  በጥምቀት ወይስ በቍርባን ግራ ገባን” የሚሉ አጉል ቅንጡዎች ፣ የአይስክሬም ተማሪዎች ይኖራሉ ። ለመኖር ግን እንጀራም ፣ አየርም ፣ ብርሃንም ያስፈልገናል በስንቱ ነው የምንኖረው  ተብሎ ግን አይጠየቅም ። እስላሞች “ከአላህ የለሽ ፣ ወይ ከነቢ” እንዲሉ ከሁሉ የሌሉ ሰዎች ያሳዝናሉ ። ከእውቀቱም ፣ ከእምነቱም አለመሆን ከባድ ነው ።

የወደቀበትን ገደል ያየ መትረፉ ሲገርመው ይኖራል ። አደጋ ስለ መትረፋቸው በየዓመቱ እየደገሱ የሚያበሉ ፣ የሚያዘክሩ ሰዎች አሉ ። የዳኑት አንድ ጊዜ ነው የሚያዘክሩት ግን ዕድሜ ልካቸውን ነው ። ምስጋናቸውን ብቻቸውን መዝለቅ ስላቃታቸው አእላፋትን ሰብስበው ያበላሉ ፣ አመስግኑልኝ ይላሉ ። የዳኑት ግን ከጊዜያዊና ከማይቀረው ሞት ነው ። ከዘላለም ሞት የዳኑ ሰዎች ከብዙዎች ጋር ማመስገን ይገባቸው ነበር ፣ ነገር ግን ሰው ድኅነቱን ማቃለሉ ያሳዝናል ። ሳይንስን ከፍለው የሚማሩ ቃለ እግዚአብሔርን በነጻ መማር አልቻሉም ፣ ሥጋዊ ፈውስን የሚያሳድዱ ድኅነተ ነፍስን ከምንም አይቆጥሩትም ። “ጽድቅና ኵነኔ ቢኖርም ባይኖርም ፣ ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም” የከበደ ሚካኤል ግጥም እንጂ የእግዚአብሔር ቃል አይደለም ። ጽድቅና ኵነኔ በርግጥ አሉ ። ቤተ ክርስቲያን ሃያ አራት ሰዓት የምትደክመው ይህን አምና ነው ። ብዙዎች ጨዋ ክርስቲያን እንጂ አማኝ መሆን አይፈልጉም ። ምክንያቱም ጽድቅና ኵነኔ ቢኖርም ባይኖርም በሚል አሳብ የሚመሩ ስለሆኑ ነው ።

ዜና ክርስቶስ የእውነት ቃል ፣ የመዳን ወንጌል ነው ። ይህ የእውነት ቃል አስቀድሞ በሐዋርያት በቃል የተሰበከ ለእኛ በመጽሐፍ የደረሰ ነው ። ያመኑበት ሁሉ አያድንም ። የሚያድነው በሚያድነው ማመን ነው ። እርሱም ክርስቶስ ነው ። ወንጌል የእውነት ቃል ነው ። እውነት ስለሆነው ስለ ክርስቶስ ይናገራልና ። እውነት ጸንታ ትኖራለች ። ዛሬ በችሎት ብትገፋ ነገ በሚፈርዱት ላይ የምትፈርድ እውነት ናት ። እውነት ጊዜዋን ጠብቃ ትወጣለች ። በዓለም ላይ ኃያላንና እናውቃለን ባዮች መቅበር ያልቻሉት እውነትን ነው ። ሃያና ሠላሳ ዓመት ታስረው ነጻ ናችሁ ሲባሉ የሚደሰቱት ከእስራቱ በላይ እውነት ተሸሽጋባቸው በመኖራቸው ነው ። ሬሳቸው ሳይቀር ነጻ የሚወጣ ብዙ ንጹሕ ሰዎች አሉ ። ከሞቱ ከብዙ ዘመናት በኋላ ንጹሕ ነበሩ ተብሎ የሚነገርላቸውን ስንሰማ እውነትን መቃብር እንደማይችላት ፣ ደግሞም ነጻ እንደምታወጣ ፣ በሌለንበትም እውነት ስለ እኛ እንደምትመሰክር ያሳየናል ። እኛ ዛሬ ለክርስቶስ እንመሰክራለን ፣ ፣ ነገ ክርስቶስ ለእኛ ይመሰክራል ።

የኤፌሶን መልእክት ትርጓሜ /23

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 13 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ