የዘመን ካስማ ፣ የሕይወት ደወል ፣ የዓለም መብራት ፣ የሕይወት ፍቺ ፣ የምድር ጌጥዋ ፣ የሰማይ ድምቀት ፣ ምን ያህል የማትባል ፣ እስከዚህ ተብለህ የማትወሰን ፣ የማያገለግሉህ ጌታ ፣ የምታገለግል ንጉሥ ፣ በሰው ጓዳ የምትመላለስ ፣ በሰው በረት ልብ የምትወለድ ፣ ከኖረኝ ነገር ይልቅ የነበርከኝ ፣ ከሚኖረኝ ነገር ይልቅ የምትኖረኝ ፣ ሠራተኞች ቢለግሙ የማያከስሩህ ባለጠጋ ፣ የፍጡራን ምስጋና ጸጥ ቢል የመቅደስህ ምስጋና የማይጓደል ምስጉን ፣ ስመ መልካሙ ፣ ባለ ዝናው ፣ በወገብህ ወርቅ የታጠቅኸው ፣ የእሳት ሕለተ ወርቅ የያዝኸው አማኑኤል ጌታዬ ሆይ አመሰግንሃለሁ ።
ቅጥሬን ስለምሠራበት ፣ የፈረሰውን ስለምጠግንበት ፣ አስፈሪዎችን ስለምደፍርበት ፣ የራቀውን ክብር ስለምመልስበት ፣ ዘባቾችን ስለምንቅበት ፣ ተሳዳቢዎችን ስለምረሳበት ፣ መሣሪያም መዶሻም ስለሆነው ንጉሣዊ ደብዳቤህ ስለ ቃልህ አመሰግንሃለሁ ። ሰማይ ያለ ምክንያት በዚህ ቃልህ ቆሟል ፣ የእኔም ሕይወት በቃልህ ረቂቅ ምሰሶ ተደግፏል ። የኃይል ቃል ሁኖ ምሽግን ስለሚያፈርሰው ፣ የሥልጣን ቃል ሁኖ ሁሉን ስለሚያዝዘው ፣ የሕይወት ቃል ሁኖ ሙታንን ስለሚቀሰቅሰው ፣ የእምነት ቃል ሁኖ ፈሪዎችን ስለሚያጸናው ፣ የአደራ ቃል ሁኖ ርስትን ስለሚያከፋፍለው ፣ የእውነት ቃል ሁኖ ወደ ፍጻሜ ስለሚቸኩለው ስለ ክቡር ቃልህ እግዚአብሔር ሆይ ምስጋና አቀርባለሁ ። የዋለለው ልቤ መንገድ የሚያገኘው ፣ የተንቀዋለለው ማንነቴ ጉዞ የሚጀምረው ፣ ግራ የተጋባው እኔነቴ ቀኙን የሚጨብጠው ፣ ሊያመልጠኝ የሚታገለኝ ልቤ ዕረፍት የሚያገኘው በቃልህ ነው ። ስለ ቃልህ ብዙ ውለታ አለብኝና አመሰግንሃለሁ ። በቃልህ ፈጠርህ ፣ በቃልህ ደገፍህ ፣ በቃልህ ታኖራለህ ፣ በቃልህ ዘላለማዊ ርስትን ታወርሳለህ ። ወደ ኋላ የሚስበኝን የምኞት ገመድ ፣ የሚጥለኝን የዓለም ትብታብ በቃልህ ሰይፍ ቍረጥልኝ ። ቃል ብቻ ተናገር ባሪያህ ልቤ ይፈወሳል ። አሜን ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 9 ቀን 2014 ዓ.ም.