ነገሥታት የሕዝቡ ገዥ ሲሆኑ የሃይማኖት ገዥ ግን እግዚአብሔር ነው ። በሁሉ ለነገሥታት መታዘዝ ይገባል ፤ ካዱ ፣ ለኑፋቄ አድሉ ሲሉ ግን መገዛት አይገባም ። የሃይማኖት ንጉሥ እግዚአብሔር ነውና ። ምእመናን በሁሉ ለነገሥታት የሚገዙት ከዚህ ዓለም የሚናፍቁት ምንም ነገር ስለሌለ ነው ። አባቶቻችን እንደ ሰው ሳይሆን እንደ አማኝ ለመኖር ናፍቀዋል ። እንደ ሰው መኖር ድንበርን መጠበቅ ነው ፣ እንደ አማኝ መኖር ግን ለሌላው መቆረስ ነው ። ነገሥታት በአማኞች ላይ ፍርደ ገምድል ሁነው በታሪክ ታይተዋል ፣ ለአማኝነት ሽልማቱ እሳትን ለገላ ፣ ሰይፍን ለአንገት ሰጥተዋል ። የማይሰርቁ ፣ የማይገድሉ ፣ ለንጉሣቸው የሚጸልዩ አማንያን በሰማዕትነት አደባባይ ሲቆሙ ይህች ዓለም ፍርድ የማታውቅ ጭፍን ዓለም መሆኗን ያሳያል ። በዚህች ዓለም የሰረቁና አናሰርቅም ያሉ እኩል በወኅኒ ይወረወራሉ/ይጣላሉ ። ሕግ የለም እንዳይባል ሕግ አለ ፤ ሌባው ታስሯልና ። ሕግ አለ እንዳንል ሕግ የለም ንጹሑ ይማቅቃልና ። በመንፈሳዊው ዓለም የብቃት መዐርግ ላይ የደረሱ እንዳሉ ሁሉ ነገሥታት ራሳቸውን እየካቡ ሲመጡ አምላክነት ይሰማቸዋል ። አምልኮ ግን አምላክነት ያሻዋል ። በሕይወት እያሉ ምስላቸውን ምሉዕ በኩለሄ አድርገው እንዲሰገድለት እንዲታጠንለት አዋጅ ብለው ያዝዛሉ ።
ከመጀመሪያው እስከ ሦስተኛው ክፍለ ዘመን በታወቁ የሮም የቅኝ ግዛት አውራጃዎች ላይ የቄሣር ምስል ቆሞ ሰጋጁ ወገን “ቄሣር ጌታ ነው” ብሎ መስክሮ ይሰግድ ነበረ ። ክርስቲያኖች ግን ይህን ግብዝነት ፣ ነገ በመቃብር የሚጠቃለለውን የነገሥታትን ህልውና እያሰቡ ይተቹ ነበር ። ንጉሥ ሕዝብን መውቀስ መክሰስ ያለበት ሕግን ፣ ሥርዓት ፣ ግብርን አክብሩ በማለት እንጂ አምላክነትን በመከጀል ሊሆን አይገባውም ብለው ያምኑ ነበር ። ንጉሥነትም ሎሌነትም የሥራ ድርሻ እንጂ የሰውነት መበላለጥ አይደለም ። ሰው ሁሉ በባሕርይው አንድ ነውና አንዱ አሰጋጅ ሌላው ሰጋጅ እንዲሆን አልተፈቀደም ። ነገሥታት መከበር በቂያቸው ነው ፣ አምልኮ ግን የባሕርይ ገንዘብነቱ ለእግዚአብሔር ነው ብለው አማንያን ያምኑ ነበር ። በዚህም ተይዘው የመጨረሻ ዕድል እንዲያገኙ በቄሣር ምስል ፊት ይቆማሉ ። “ቄሣር ጌታ ነው” ብላችሁ ስገዱ ተብለው በወታደር ይገደዳሉ ። እነርሱም በጥብዓት ያለ ፍርሃት “ኢየሱስ ጌታ ነው” ብለው ይመሰክራሉ ። በዚህ ጊዜ በአሰቃቂ ፍርድ እንዲሞቱ ይደረጋል ። ዛሬ “ኢየሱስ ጌታ ነው” የሚለው ስብከት ኢየሱስ አምላክ ነው ብለን ለምናምን ወገኖች መነገሩ ይደንቃል ። ይህ ብቻ አይደለም ፣ የአዳራሽ ማሞቂያ ፣ የመዘላለፊያ ርእስ የተደረገው “ኢየሱስ ጌታ ነው” የሚለው ምስክርነት የአንገት ዋጋ የተከፈለበት እንደሆነ ማሰብ ይገዳል ። ኢየሱስ ጠበቆችን ሳይሆን ምስክሮችን ይፈልጋል ። መከራከር ጥብቅና ነው ። ጠበቃ ለከፈለው ይሠራል ። ምስክር ግን ለነፍሱ ይመሰክራል ።
ሰማዕትነት የጀመረው በአቤል ነው ። ከፍጥረት እስከ ምጽአት ሰማዕትነት እንደ ቀጠለ ነው ። ሰማዕትነት የቆመበት ዘመን የለም ። አንዳንድ ዘመን ሕሊናን በመሰየፍ ፣ በማሸማቀቅ ፣ ስምና ክብርን በመንሣት ፣ የሥራ ዕድልና ዕድገትን በመከልከል ፣ የቤት ኪራይ በማሳጣት ፣ ከዕቍብና ከዕድር በማስወጣት ፣ ኢኮኖሚያዊ ጫና በማሳደር ይፈጸማል ። ይህ ሁሉ የሰማዕትነት አካል ነው ። ሰማዕትነት ግን በሁሉ ዘመን ያለና የሚኖር ነው ። እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመሰከርን እንደ እርሱ መከራ መቀበላችን አይቀርም ። ሠለስቱ ደቂቅን /ሦስቱ ወጣቶችን ከመሰልን ናቡከደነፆር በግድ ይኖራል ። ሰማዕት የለም እንጂ ሰማዕትነትስ ቆሞ አያውቅም ። ታዲያ ብሉይ ኪዳንም አዲስ ኪዳንም ገደለ ሰማዕታት ነው ብንል አንዋሽም ።
ትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ ሦስት ናቡከደነፆርና ሠለስቱ ደቂቅ ፣ ጣዖትና የእግዚአብሔር ትድግና የሚነበብበት ክፍል ነው ። ለማስካድ የወጣው ንጉሥ አማኝ ሆነ ። ለመግደል የተቀጣጠለው እሳት ቀይ መናፈሻ ሆነ ። ታኅሣሥ 19 ቀን የሚከበረው በዓል እግዚአብሔር ሰማዕታት የሆኑ ወጣቶችን ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ እንዳዳናቸው ለማሰብ ነው ። ዛሬም እውነተኛ ወጣቶች ከዘመን እሳት እንደሚድኑ ለመስበክም ነው ። በዓላት የሃይማኖት አትሮኖስ/መስበኪያ ናቸውና ። ሃይማኖት ትኩስ ሁኖ እንዲኖር በዓላት አስፈላጊ ናቸው ። በትንቢተ ዳንኤል ላይ በመገለጥ የሚታወቀው ቅዱስ ገብርኤል በዳንኤል 3 ላይም ተገልጦ እግዚአብሔር አምላክ መሆኑን መስክሯል ብላ ቤተ ክርስቲያን ታከብራለች ። በዚህም ምእመናን ለሰማዕትነት ጨካኝ እንዲሆኑ ታበረታታለች ፣ የቅዱሳን መላእክትን ክብርና ወዳጅነትም ታሳውቃለች ።
በዚህ በዓል ብዙ ትምህርት ይገኛል ። ነገሥታት የጣዖትነት ስሜት ሲሰማቸው ፣ አባ ጠቅል ነን ሲሉ ተዉ የሚላቸው ያስፈልጋል ። ሽማግሌ ፈርቶ ወጣት ተዉ ማለቱ ግን ያለና የሚኖር ነው። ወጣቶች የሚያምርባቸው ሰማዕትነት እንጂ ገዳይነት አይደለም ። እግዚአብሔር የሚያድነው ሁልጊዜ እሳቱን በማጥፋት ሳይሆን እሳቱ እያለም እንዳይጎዳ በማድረግም ነው ። ቅዱሳን መላእክት በተራዳኢነት በምልጃ ፣ ከእግዚአብሔር በሚሰጥ ተልእኮ አስፈጻሚነት በብሉይም በአዲስም ሲያበሩ ይኖራሉ ። ዛሬም አላስተዋልነውም እንጂ በየዕለቱ የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት አልተለየንም ።
በእውነት አሁንም ቅዱስ መልአኩን ልኩ የነደደውን እሳት ያጥፋልን ። የመልአኩ ከቅዱስ ገብርኤል ረድኤት በረከት ፣ የጸሎቱ ትድግና ትድረሰን ! አሜን !