ያ ሰውን ከድንግል መሬት የፈጠረው ራሱ አሁንም ልክ እንደዚያ ያደርጋል
… ልክ በአበባ ጉንጉን ላይ እንዳለው ፣ የራሳችንን ነፍስና ስለ በዓሉ ማድመጥ የሚወዱት ነፍሶች ከወርቃማው አበባ /ከክርስቶስ/ ጋር እናዋህድ ። ከማይጠወልገው የአትክልት ቦታ አክሊልን ለመድፋት እንዘጋጅ። የክርስቶስንም አበባዎች በእጃችን ለማቅረብ እንሰብስባቸው። የሚያበራው ውድ ሉል ወደ ጨለማና ወደ ሞት ጥላ ይሄዱ የነበሩትን ደማቅ ወደሆነው ዘላለማዊ ብርሃን ያወጣቸው ዘንድ ከእርሷ ወጥቷልና እግዚአብሔርን የሚመስለው የቅድስት ድንግል ማሕፀንም እንዲህ ባለ አክሊል ይጌጥ ዘንድ ይገባል ።
መለኮታዊ በሆኑት በክርስቶስ ቃላት ሐሴት አድርገን መልካም የሆነውን ዝማሬ እናቅርብለት ። የሕያውነት ምሥጢር የሆኑትን ፍሬዎች ለመሰብሰብ እንፋጠን ። እግዚአብሔር የተዋሐደውን (መልካም) መዓዛ ለማሽተተ እንፋጠን ። በእኛ ቋንቋ እንደምንለው በመለኮታዊው ጸጋ እንደሰት ፤ የሚከረፋውንም የኃጢአት ሽታ ከራሳችን ለማራቅ እንፋጠን። ከዚህ ይልቅ ጣፋጭ በሆነው በጽድቅ ሥራ ራሳችንን እናልብስ። የእምነትን ጋሻ ይዘን የመልካም ሥራ ልብስንም ለብሰን ፣ ቅዱስና ነቀፋ የሌለበትንም የንጽሕናን ዝናር ታጥቀን እንጹም ። እርሱ ከፍ ያለ ነው መኖሪያውም ከሰላም ጋር ነው። ኦ! ወዳጆቼ ሆይ እኛ ግን በአዳኙ የአትክልት ስፍራ አርፈን በመለኮታዊው ጸጋ ቋንቋ ከመላእክት ጋር ሁነን ቅድስት ድንግልን “ደስ ይበልሽ ሐሴትም አድርጊ” እያልን እናመስግናት ። ከእርሷ መጀመሪያ በመልካምነቱ የሚያበራልን ዘላለማዊው የብርሃን ነፀብራቅ ወጥቷልና።
ቅድስት ድንግል ራሷ የተከበረች የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና የነጻች ሳጥን ፣ ሁሉም የሚቃጠሉት መሥዋዕቶች የሚቀርቡባት የወርቅ መሠዊያ ነች ። እጅግ በላቀውና ልዩ በሆነው ንጽሕናዋ ምክንያት ለፈጣሪ የምትቀርብ ዕጣን ፣ ቅዱስ የሆነው የጸጋ ቅባትና እውነተኛውን ናርዶስ የያዘች ውድ ማሰሮ ፣ የእግዚአብሔርን ደስታ የሚገልጽ ክህነታዊ ወደሆነው የወርቅ አክሊል የምትቀርብ በሥጋና በነፍስ ንጽሕት የሆነችው እርሷ ብቻ ነች ። ወደ ምሥራቅ የዞረችው በር እርሷ ነች ፤ ከእርሷ በወጣው (ብርሃን) ምድር በራ ። መንፈስ ቅዱስ ከእርሷ አዳኙ የተዋሐደውን ሥጋ የወሰደባት የለመለመች የወይራ ዛፍ እርሷ ነች ። እርሷ የደናግላን መመኪያ የእናቶች ደስታ ነች ። “ደስ ይበልሽ ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው” (ሉቃ. 1 ፥ 28) ተብሎ እንደ ተነገረው የመልአክ አዋጅ ፣ በኃጢአት ምውት የነበሩትን ያድስ ዘንድ ከእርሷ ተወለደ ።
ኦ! ጌታ በማሕፀኗ ታድር ዘንድ አስቀድመህ ሊቀ መላእክት እንዲያበሥራት አድርገህ ድንግልና ደስተኛ እንድትሆን ፈቀድህ ። ነገር ግን ከላይ ቅዱሳን ከሆኑት ሰማያዊ አገልጋዮች የሆነውገብርኤል ወደ ማርያም መጣና እንዲህ የሚለውን የምሥራች አበሰራት “ደስ ይበልሽ”እንዲህም ብሎ ጨመረ “ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት ።” (ሉቃ. 1፥28)። ነገር ግን እርሷ በውስጧ ታውካ ይህ እንዴት ያለ የምሥራች ነው ብላ አሰበች ። እርሷ በሁሉም መንገዶች ጠቢብ ፣ ከሴቶችም የሚመስላት የለምና እኔም እንደዚሁ ቅድስት ድንግልን የመረጣትን ጸጋ አስባለሁ ።
በገነት ብቻዋን እንደ ነበረችው ፣ ክፉ የነበረውን የእባቡን ወሬ ሰምታ የልቧን አሳብ እንደ ጣለችው ፣ የቅዱሱን ድካምና ኀዘን እንዳመጣችው እንደ መጀመሪያይቱ ድንግል አይደለችም ። ቅድስት ድንግል ግን እንዲህ ነበረች፤ በእርሷ የቀደመው መተላለፍ ተደመሰሰ። ሣራ እንዳደረገቸውም ልጅ ትወልጃለሽ የሚል የምሥራች ስትሰማ አልሳቀችም ። አሊያም ልክ እንደ ርብቃ አታላይ እንደሆነ ሰው በብስጭት ጌጥ ተቀብላ ለእጮኛዋ ግመሎች ውኃ አልሰጠችም ። እንደ ሌሎች ሴቶችም (የመልአኩን) ሰላምታ ዝም ብላ አልተቀበለችም ፤ ነገር ግን ብሩህ በሆነ አሳብ መርምራ እሺ አለች ፡-
እንዲህ ያለን በረከት ከወዴት ነው ያመጣኸው ? እንዴት ካለ ግምጃ ቤትስ ነው የዓለም ሉል (ክርስቶስ) የተላከው ? ስጦታው ምን እንደሆነ (አካላዊ) ቃልንም የተሸከመው ማን እንደሆነ ማወቅ እፈልጋለሁ ፣ አሊያም ላኪው ማን እንደሆነ ማወቅ እፈልጋለሁ ።
እነዚህን ነገሮች ቅድስት ድንግል በውስጧ በጥርጣሬ ጠየቀች ። ነገር ግን መልአኩ እንዲህ ባሉ ቃላት ጥርጥሯን አራቀው ፡- “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል ።” (ሉቃ. 1 ፥ 35) ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ ።” (ማቴ 1፥21)
ድንግልም ለመልአኩ እንዲህ ብላ መለሰችለት፡- “ዋናተኛ ባሕር ላይ እንደሚዋኘው አሳቤ በተናገርሃቸው ቃላት ውስጥ እየዋኘ ነው ። ይህ እንዴት ይሆንልኛል ? ራሴን ለሰማያዊው ሙሽራ ሰጥቻለሁና ምድር ላይ ወንድን ማወቅ ፈጽሜ አልሻም። ድንግል ሆኖ መኖርን እወዳለሁ ፣ የድንግልናዬንም ክብር ማጥፋት አልፈልግም ።”
እንዲህ ያሉ ቃላትን ብትናገርም መልአኩ ቅድስት ድንግልን እንዲህ ብሎ አረጋገጠላት ፤ ማርያም ሆይ የመጣሁት ላስፈራሽ ሳይሆን ፍርሃትሽን ለማስወገድ ነውና አትፍሪ ። ማርያም ሆይ በእግዚአብሔር ዘንድ ጸጋን አግኝተሻልና አትፍሪ ። ከተፈጥሮ ሕግ በታች አይደለምና (የእግዚአብሔርን) ጸጋ አሳንሰሽ አትመልከቺ። መንፈስ ቅዱስ ባንቺ ላይ ይመጣል ፤ ስለዚህ ካንቺ የሚወለደው የመልኩና የባሕርይው ብሎም የዘላለማዊነቱ ተካፋይ የሆነው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ነው።
ኦ! ማርያም ሆይ የተማርሽው ምሥጢር እጅግ ታላቅ ነው ። ይህም ምሥጢር አሁን ድረስ ከመላእክት የተሰወረ ነው ። አንቺ ነቢያትና አባቶች ያልሰሙትን ሰምተሻል ። አንቺ የእግዚአብሔር መዘምራን እንኳን ሊሰሙ ያልተገባቸውን ሰምተሻል። ዳዊት ፣ ኢሳይያስና ሌሎችም ነቢያት በስብከታቸው ጌታ ሰው እንደሚሆን አስቀድመው ተናገሩ። ኦ! ቅድስት ድንግል አንቺ ብቻ ከእነርሱ የተሰወረውን ምሥጢር ተቀበልሽ ። ስሚ ይህም (ምሥጢር) አንቺ ላይ እንዴት እንደሚፈጸም ግር አይበልሽ ። ያ ሰውን ከድንግል መሬት የፈጠረው ራሱ አሁንም ልክ እንደዚያ ያደርጋል ። ለፍጥረቱ ድኅነት ያደርገዋል ።
የዘላለማዊው ብርሃን ነፀብራቅ በእነዚህ ቃላት አሁን ይበራልናል ። በእርሷ ሁሉም የነፍስ ሀብቶች አሉ ፤ ሕያውም የሆኑ ናቸውና ከሁሉም አስቀድሞ ጥበብ በተሞላበት መልኩ “ደስ ይበልሽ” (ሉቃ. 1 ፥ 28) ብሎ መልአኩ ያመሰገነውን የድንግልን ማንነት ማድነቅ ለእኔ ግድና ተገቢ ነው። ከዓለም/ከሴቶች በሙሉ ወንድ ሳታውቅ ድንግልና እናት የሆነችው ፣ በሥጋም በነፍስም ቅድስት ሁና የተገኘችው እርሷ ብቻ ናት ። ከዓለም/ከሴቶች በሙሉ እግዚአብሔርን ለመውለድ የተገባች እርሷ ናት ። ሁሉንም በቃሉ የሚሸከመውን/ደግፎ የሚይዘውን የተሸከመችው እርሷ ብቻ ናት ።
ቅድስት የሆነችው የአምላክን እናት በውበቷ ብቻ ሳይሆን በመንፈሷ ታላቅነትም ማድነቅ የሚገባ ነው ። “እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው” “ጌታም ካንቺ ይወለዳል” እንዲህ የሚለው ቃል የተነገራት በዚህ ምክንያት ነው ። እንደ መለኮታዊ ምሥጢር መዝገብነትዋ ቅድስት ድንግል ራስዋን አዘጋጀች፣ የሕይወት ሉል ክርስቶስም በሥጋ በውስጥዋ ተሰወረ ። እርሷም ከተፈጥሮ በላይ ታላቅ የሆነው የመለኮታዊ ድኅነት መንበር ሆነች ።