እንኳን ለጾመ ፍልሰታ አደረሳችሁ !
ከእርሷ በመልካምነቱ የሚያበራልን ዘላለማዊው የብርሃን ነፀብራቅ ወጥቷልና። ኦ! ወዳጆቼ ሆይ እኛ ግን በአዳኙ የአትክልት ስፍራ አርፈን በመለኮታዊው ጸጋ ቋንቋ ከመላእክት ጋር ሁነን ቅድስት ድንግልን “ደስ ይበልሽ ሐሴትም አድርጊ እያልን እናመስግናት”
የሔዋንን አለመታዘዝ ሳስብ አለቅሳለሁ ። ነገር ግን የማርያምን ፍሬ ስመለከት እንደገና እታደሳለሁ ። በባሕርይህ የማትሞት ፣ ከውበትህ የተነሣ ስውር የሆንህ ፣ ከዘመናት በፊት[1]ከብርሃን የተገኘህ ብርሃን ፣ አንተ ከእግዚአብሔር አብ ተወለድህ ። (አካላዊ) ቃልና የእግዚአብሔር ልጅ ሆነህ ሳለ በተቀደሱ እጆችህ የተበጀውን አዳምን አዲስ አድርገህ ታድሰው ዘንድ ከድንግል ማርያም ሥጋን ነሣህ።
ቅዱስ ፣ የማትሞት ፣ ዘላለማዊ ፣ የማይደረስብህ ፣ የማትቀየር ፣ የማትለወጥ ፣ ከዘመናት በፊት እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጅ የሆንከው አንተ በቅድስት ድንግል ማሕፀን ለመጸነስደስተኛ ነበርህ ። ይህንንም ያደረግኸው በተቀደሱ እጆችህ የተበጀውን ፣ በኃጢአትም የሞተውን ሰው ሕያው ታደረገው ዘንድነው ።
በማይታየው በአባትህ ፈቃድና ስምረት ወደዚህ ዓለም መጣህ ። ስለዚህ ሁላችንም ንጉሣችን ብለን እየጠራን እንለምንሃለን ። ረዳታችን የሆንኸው ፣ ከድንግል የተወለድኸው በመጠቅለያም ተጠቅልለህ በበረት የተኛኸው ፣ የማርያምንም (ጡቶች) የጠባኸው አንተ የመጀመሪያ ሰው የሆነውን በኃጢአትም የሞተውን አዳም ሕያው ታደርገው ዘንድ (ይህን አደረግህ) ።
ከመለኮታዊው እውቀት ፣ እውቀትን ተካፍለን ልክ እንደ ምንጭ ጣፋጭ ሆኖ የሚደመጠውን የምስጋና መዝሙር እናፍልቅ ። ጣፋጭ በሆኑ ትምህርቶች ለመለኮታዊው ጸጋ የሚገባውን ምስጋና እንስጥ ። የእርሱ ኃይልና ግርማ በእኛ መካከል ነበርና በዚህም ምክንያት ምድር ፣ ባሕር ፣ የሚታዩትና የማይታዩት ፍጥረቶች በሙሉ እግዚአብሔር ለሰው ያለውን ፍቅር ያመሰግናሉ ፤ ያከብሩማል ። በፍጻሜው ባለ መታዘዝ ምውት ሆኖ የነበረውን (አዳምን) አዲስ አድርጎ ያድሰው ዘንድ እርሱ አምላክ ሆኖ ሳለ በሥጋ ተገለጠ። ፍጹም የሆነን ትሕትናም ተላብሶ ከቅድስት ድንግል ተወለደ ።
ኦ! እናንተ የአማንያን ጉባኤ ዙሩና ኑ። ከድንግል የተወለደውን እናመስግነው። ከዘመናት በፊት ክብሩና የባሕርይው መልክ የሆነው እርሱ አሁን ከእኛ ጋር በድህነት/በእጦት የሚሰቃይ ሆነ ። የእግዚአብሔር እጅግ አስደናቂ ኃይልና መልክ የሆነው እርሱ የባሪያን መልክ ያዘ ። ያ ብርሃናትን እንደ ልብስ የሚጎናጸፈው እርሱ ባዶ እንደሆነ ከሰዎች ጋር ኅብረት አደረገ ። ያ በኪሩቤልና እልፍ አእላፍ በሆኑት መላእክት የሚዘመርለት በምድር ላይ እንደ ዜጋ ኖረ። ያ ከሁሉም በፊት የነበረው ሁሉንም ሕያው ያደረገው የመጀመሪያውን ሰው ሕያው ያደርግ ዘንድ ከቅድስት ድንግል ተወለደ ።
ክርስቶስ አምላካችን ከእግዚአብሔር አብ የሆነውን መጀመሪያ የሌለውን ሕይወት ተካፋይ ሆኖ ሳለ መጀመሪያ ወደ ሌለው መለኮታዊ መጀመሪያ ከፍ ያደርገው ዘንድ መጀመሪያ ያለውን የሰው ሕይወት ነሣ ።
ከድንግል ማርያም የባሪያን መልክ ነሣ ። የሰማያዊው መልክ ተካፋዮች ያደርገን ዘንድ እርሱ ከአፈር የተሠራውን አካል ተዋሐደ ። በአባቱ ቀኝ በኅብረት እንቀመጥ ዘንድ እርሱ በቅድስት ድንግል እግሮች ላይ ተቀመጠ ። የዘላለማዊ ሕይወት ወራሾች አድርጎ ይገልጠን ዘንድ የተዋረደን አካል ተዋሐደ ፤ በዚህም በማሕፀን አደረ ። በኃጢአት ምክንያት ጠፍቶ የነበረውን አዳም ያድሰው ዘንድ የማይወሰነው እርሱ በቅድስት ድንግል ማሕፀን ተወሰነ።
የአብ ኃይሉ ፣ ሕያውም ምንጭ የሆነው ክርስቶስ አምላካችን በእርሱ ሕያው በሆነው ድምፅ ላመኑት ሕይወትን መልቶ የያዘ ምሥጢር ነው ። በእርሱ ተስፋ በሚያደርጉት ላይ ፍጻሜ የሌለውን ሕይወት በነጻ የሚሰጥ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋም የሚያበራላቸው እርሱ ነው ። በእምነት (ሆነው) የተጠሙ ሕያው፣ ዘወትር ከሚፈሰው ጣፋጭም ከሆነው ከዚህ ምንጭ ይመላሉ ፣ ይረካሉም ።
እርሱ ለወጣትና ለሽማግሌዎች ፣ ለሕፃናትና ለሴቶች የድኅነታቸው አጋዥና ምንጭ ስለሆነ በዚህ ምክንያት በአንድ ድምፅ ሆነን ሥግው ቃልን እናመስግን። ከቃላት በላይ የሆነው መለኮት ምንጭ ከድንግል ማርያም ጸጋንና ነጻ የሆነውን የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ አፈለቀ ። በኃጢአት ምክንያት ሙቶ የነበረውን ሕያው ያደርግ ዘንድ ከአንዷ ቅድስት ድንግል እጅግ ውድ የሆነው ሉል ወጣ/ተወለደ።
እርሱ በምድር ላይ የበራ የጽድቅ ፀሐይ ነው። በሰው መልክ ከእኛ እንዳንዱ ለመሆን ራሱን ዝቅ አደረገ። የመለኮታዊውን ክብር ነፀብራቅ በሰውነቱ ሰውሮ እኛንም በመለኮታዊው በመንፈስ ቅዱስ ሞልቶ አምላካዊ የሆነውን የምስጋና መዝሙር እንድንዘምር የተገባን አደረገን።
ይቀጥላል